ኑሮን ለማሸነፍ ማሕፀናቸውን የሚያከራዩት ድሃ እናቶች

ነፍሰ ጡር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኮሎምቢያ ውስጥ የሚከራይ ማሕፀን ማግኘት የተገለገሉበትን መኪና የመሸጥ ያህል ቀላል ነው።

ብዙ የአገሪቱ ወጣት ሴቶች ራሳቸውን ለማስተዳደር ማሕፀናቸውን ከማከራየት ውጪ አማራጭ የላቸውም።

በአንድ የፌስቡክ ገጽ ላይ የተለጠፈ ማስታወቂያ “የምኖረው ቦጎታ ነው፣ ማሕፀኔን አከራያለሁ” ይላል።

እንዲህ ያለ ማስታወቂያ ማየት የተለመደ ነው።

ኮሎምቢያ የምትኖረው የ22 ዓመቷ ቬንዝዌላዊት ሜሪ ማሕፀናቸውን ከሚያከራዩት አንዷ ናት። በምታገኘው ገንዘብ ቤተሰቧን ከደቡብ አሜሪካ ማሻገር ነው ፍላጎቷ።

“የጀመርኩት ከፍቅር አጋሬ ጋር ከተነጣጠልኩ በኋላ ነው። አምስት ዓመት አብረን ነበርን። ሁለት ልጆች አሉን። ማሕፀኔን የማከራየው ልጅ የሌላቸውን ጥንዶች ለማገዝ እና ገንዘብ ለማግኘትም ጭምር ነው” ትላለች።

አንድ ፕሮግራም ላይ ስለ ማሕፀን ኪራይ ሰምታ ነበር። አሁን ያለችበት ሁኔታ ውስጥ እስከምትገባ ግን ማሕፀኗን ለማከራየት አስባ አታውቅም።

የኑሮ ውድነት ሲባባስ ግን ከዚህ ሌላ አማራጭ አጣች።

አንዳንድ ሴቶች እስከ 12,000 ዶላር ያስከፍላሉ። ኪራዩ እስከ 4,000 ዶላርም ሊቀንስ ይችላል።

ሜሪ የምታስከፍለው ከ10,000 እስከ 12,000 ዶላር ነው።

የማሕፀን ኪራይ

ሉሲያ ፍራንኮ ጋዜጠኛ ናት። ኮሎምቢያ ውስጥ እየተስፋፋ የመጣውን የማሕፀን ኪራን በተመለከተ ምርመራ አድርጋለች።

ማሕፀናቸውን ለማከራየት የፈቀዱ ሴቶችን ማግኘት በጣም ቀላል መሆኑ አስገርሟታል።

“እንዲህ በአደባባይ ይደረጋል ብዬ አላሰብኩም ነበር። ግን ፌስቡክ ላይ ሴቶቹ ማስታወቂያ ይለጥፋሉ። ድሃ ስለሆኑ ማሕፀናቸውን ከማከራየት ውጪ ምርጫ የላቸውም። የኪራይ ዋጋው አነስተኛ ነው” ትላለች።

የማሕፀን ኪራይ በሕግ ቢፈቀድም፣ አሠራሩን የሚመራ ደንብ ስላልወጣ ብዙ ሕገ ወጥ ክንውኖች ይስተዋላሉ።

የኮሎምቢያ የጤና እና ማኅበራዊ ጥበቃ ሚኒስቴር የሕግ ክፍተት እንዳለ ለቢቢሲ በላከው የጽሑፍ ምላሽ አስታውቋል።

“መንግሥት የማሕፀን ኪራይን በተመለከተ አዲስ ረቂቅ ሕግ እያዘጋጀ ነው” ይላል ምላሹ።

ነፍሰ ጡር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቁጥጥር ባለመኖሩ የሚከፈለውን ገንዘብ እና ሂደቱ ምን እንደሚመስል እየወሰኑ ያሉት ማዋለጃ ክሊኒኮች እንደሆኑ ከምላሻቸው መረዳት ተችሏል።

ምን ያህል ማሕፀናቸውን ያከራዩ ሴቶች እንዳሉ እና ስንት ጊዜ እንዳከራዩ መረጃ አልተመዘገበም።

ጋዜጠኛዋ እንደምትለው መረጃ አለመያዙ ለእናቶች እና ለልጆቹ ጤና አደጋ ነው። ማሕፀናቸውን የሚያከራዩ ሴቶችን ለሰብአዊ መብት ጥሰት እንደሚያጋልጥም ታክላለች።

ኤል ፔይስ ከተባለ ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቀድሞው የኮንግረስ አባል ሳንድያጎ ቫሌንስያ እንዳሉት፣ ማሕፀናቸውን የሚያከራዩ ሴቶች ብዙውን ጊዜ ለብዝበዛ ይጋለጣሉ። ነፍሰ ጡር ሳሉ ቁጥጥር ለማድረግ ሲባል ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው እንደሚቆዩ ተናግረዋል።

ማሕፀናቸውን የሚያከራዩ ሴቶችን ከተከራዮች ጋር የሚያገናኙና ሂደቱን የሚያሳልጡ ክሊኒኮችን ቢቢሲ ጥያቄ ቢልክላቸውም መልስ አልሰጡም።

ነፍሰ ጡር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በብዙ የአውሮፓ አገራት የማሕፀን ኪራይ ክልክል ስለሆነ ጥንዶች ወደ ኮሎምቢያ ያቀናሉ።

በኮሎምቢያ ሁለት የማሕፀን ኪራይ አማራጮች አሉ። አንደኛው ሴቶች እንቁላል በመለገስ በሰው ሠራሽ መንገድ የሚያረግዙበት ሲሆን ሌላኛው በሌላ ሴት እንቁላል የሚያረግዙበት ነው።

በኮሎምቢያ ልጅ ሲወለድ የእናት ስም በልደት ምስክር ወረቀት እንዲጻፍ ሕግ ቢያስገድድም፣ ለሐኪሞች ጉቦ በመስጠት ማሕፀኗን ያከራየችው ሴት ሳይሆን የተከራየችው ሴት ቤተሰብ ስም እንዲጻፍ ይደረጋል።

“የልደት ምስክር ወረቀት ላይ መጻፍ ያለበት የወለደችው ሴት ስም ነው” ሲል የአገሪቱ የጤና እና ማኅበራዊ ጥበቃ ለቢቢሲ ገልጿል።

ሜሪም ጉቦ በመስጠት ማሕፀኗን የተከራዩ ጥንዶች ስም በልደት ምስክር ወረቀቱ ላይ እንዲጻፍ ለማድረግ አስባለች።

እንደዚህ ካልሆነ ጥንዶቹ ከአገር ለመውጣት ይቸገራሉ።

ሜሪ ማሕፀኗን የሚከራዩ ጥንዶች ከየትም አገር ቢመጡ ግድ አይሰጣትም፣ ሆኖም ግን ጥንዶቹ “ልጅ ለማግኘት ብዙ የደከሙና የታገሉ” ቢሆኑ ትመርጣለች።

ኑሮን ለመግፋት ማሕፀን ማከራየት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“22 ዓመቴ ነው። ማሕፀኔ አከራያለሁ። ልጅ የለኝም” “ጤነኛ ነኝ። ቤተሰቤን መደገፍ እፈልጋለሁ”

“ከኢኳዶር ማሕፀን የምትከራዩ በውስጥ መስመር መልዕክት ጻፉልኝ። ወደአሜሪካ የምትጓዙ ከሆነ የበለጠ ተመራጭ ነው”

እነዚህን የመሰሉ ማስታወቂያዎች ፌስቡክ ላይ በብዛት ይታያሉ።

አንዳንዶች የልጆቻቸውን ፎቶ በመለጠፍ ማሕፀን ለሚከራዩ ሰዎች ያስተዋውቃሉ።

“ልጆቼ ሰማያዊ ዐይን አላቸው። ተጨማሪ ፎቶዎች ተመልከቱ” የሚል ማስታወቂያ የለጠፉ እንደምሳሌ ይጠቀሳሉ።

በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉ የኮንግረስ አባላት ዘርፉ ሕግ እንዲወጣለት ጫና እያሳደሩ ነው።

ለምሳሌ ዴሞክራቲክ ሴንተር የተባለው ፓርቲ በአጠቃላይ 16 ደንቦች አቅርቧል። የማሕፀን ኪራይን ሕጋዊ በማድረግ የተሻለ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ይገልጻሉ።

አምና መስከረም ላይ የኮሎምቢያ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ኮንግረስ በስድስት ወራት ለማሕፀን ኪራይ ሕግ እንዲያወጣ ትዕዛዝ አስተላልፏል። እስካሁን ግን ረቂቅ ተዘጋጀ እንጂ ሕግ አልወጣም።

“የማሕፀን ኪራይን በተመለከተ ሕግ ያስፈልጋል። ምን ዓይነት የክሊኒክ ሂደት ይፈልጋል፣ አከራይ እና ተከራይ ምን ላይ ይስማማሉ፣ የአከራዮች መብት እንዴት ይከበራል የሚለውን ይወስናል” ተብሏል።

ጋዜጠኛዋ እንደምትለው ሕግ ከወጣ ሴቶች እንዳይበዘበዙ ይከላከላል።

የማሕፀን ኪራይ በኮሎምቢያ ወይም በደቡብ አሜሪካ ብቻ የተገደበ አይደለም። በአንዳንድ አገሮች ክልክል ነው።

ኪራዩን በሚፈቅዱ አገሮች ውስጥ ደግሞ ቢሮክራሲው ይበዛል። ለዚህ ነው ጥንዶች ወደሌላ አገር ሄደው ማሕፀን የሚከራዩት።

በኮሎምቢያ ግን እምብዛም ከሕግ ጋር የተያያዘ መሰናክል አይገጥምም።

ልጆች የሌላቸው ጥንዶች ለመርዳት ሲሉ ማሕፀናቸውን የሚያከራዩ ሴቶች አሉ። ሌሎች ደግሞ ከሚያስገኘው የገንዘብ ጥቅም አንጻር ነው እዚህ ውስጥ የሚገቡት።

ቺሊ የምትኖረው ዳንኤላ ማሕፀኗን የምታከራው “ልጅ የሚፈልጉ ጥንዶችን ለመርዳት” እንደሆነ ትናገራለች።

“እናትነት ልዩ ነው። ይህን ልዩ ነገር ማድረግ እፈልጋለሁ” ትላለች።

ከዚህ በተቃራኒው ኮሎምቢያ ለምትኖረው ሜሪ እና ሌሎች በርካታ ሴቶችም የማሕፀን ኪራይ ኑሮን መግፊያ መንገድ ነው።