ከካንሰር ህመም ተርፋ የሴቶች የዓለም ዋንጫ ኮከብ የሆነችው ሊንዳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሊንዳ ካይሴዶ በዓለም ምርጥ ከተባሉት ክለቦች ውስጥ አንዱ ለሆነው ሪያል ማድሪድ የካቲት ወር ላይ ፈረመች።
ለሪያል ማድሪድ መፈረም የበርካታ እግር ኳስ ተጫዋቾች ህልም ቢሆንም ለሊንዳ በወቅቱ ደስታዋ ሙሉ አልነበረም።
በዚያች ዕለትም ከቤተሰቦቿ እና ከጓደኞቿ ጋር ደስታዋን ለመጋራትም አልቻለችም።
የ18 ዓመቷ ኮሎምቢያዊት በአገሯ ቀዶ ህክምና የምታደርግ ታዳጊ የካንሰር ህመምተኛ ጉዳይ አሳስቧት ቀኑን ያሳለፈችው ስልክ በመደወል እና ጉዳይዋን በመከታተል ነበር።
ሊንዳ በሕይወቷ ትልቅ በምትባለውም ዕለት ቅድሚያ የምትሰጣቸው ጉዳዮች እንዳሉ ይህ ማሳያ ነው።
ሊንዳ በዘንድሮው 2023 የፊፋ የሴቶች የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ከታዩ ኮከቦች አንዷ ናት።
ሆኖም እዚህ ለመድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፋለች። የሕይወት ጉዟዋም ቀላል አይደለም።
ገና በታዳጊነቷ በ14 ዓመቷ ነው ወደ ፕሮፌሽናል እና ዓለም አቀፍ እግር ኳስ የገባችው። በ15 ዓመቷም ካንሰር እንዳለባት በምርመራ ታወቀ። ከካንሰር አገግማ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በዓለም ላይ በጣም ታዋቂ ከሆኑ ክለቦች ውስጥ አንዱን ተቀላቅላለች።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሲድኒ በሚደረገው የሴቶች ዓለም ዋንጫ አገሯን ኮሎምቢያን ወክላ በእግር ኳስ ሜዳው እያንጸባረቀች ትገኛለች።
ኮሎምቢያ በዓለም ዋንጫ መክፈቻ ጨዋታ ደቡብ ኮሪያን ስታሸንፍም ሊንዳ ጎል አስቆጥራለች።
የ18 ዓመቷ ሊንዳ በዓለም ዋንጫ ውድድር ታሪክ በትንሽ ዕድሜዋ ጎል ያስቆጠረች ሁለተኛዋ ደቡብ አሜሪካዊት ተጫዋች ሆናለች።
ከዚህ ቀደም በለጋ ዕድሜዋ ይህንን ማሳካት የቻለችው ታዋቂዋ የብራዚል እግር ኳስ ተጫዋች ማርታ ቪየራ ደ ሲልቫ ናት።
ምንም እንኳን የሴቶች እግር ኳስ ተጫዋች የምንጊዜም ኮከብ ከሆነችው ማርታን ከሊንዳ ጋር ማወዳደር ከባድ ቢሆንም፣ ሊንዳ በሜዳው ኮከብ ለመሆኗ የአሁኑ የዓለም ዋንጫ ማሳያ ነው።
በቅርቡም ኮሎምቢያ የሁለት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮና የሆነችውን ጀርመንን 2 ለ1 አሸናፊ ያደረገቻትም ሊንዳ ናት። በዚህም አገሯን ለቀጣይ ዙር እንድታልፍ አድርጋለች።
ሊንዳ በኮሎምቢያ የሴቶች እግር ኳስ መለያ ሆናለች።
ሊንዳ የተወለደችው በኮሎምቢያዋ ካንደሊሪያ ነው። ቤተሰቦቿም ይህ ነው የሚባል ገቢ ያልነበራቸው ሲሆን፣ ልጅነቷንም ያሳለፈችው በድህነት ነው።
የእግር ኳስ ኮከቧ የመጣችበትን አሁንም አልረሳችም። በቅርቡም ወደ ትውልድ መንደሯ አቅንታ ለበርካቶች ምግብ እና የሚያስፈልጋቸውን ቁሶች ይዛ ሄዳለች።
ይህንን በጎ ነገር ስታከናውንም ሚዲያ እንዲኖር አልፈቀደችም።
እግር ኳስ ተጫዋችዋ ከአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ የኮሎምቢያ ብሔራዊ ቡድን ሲመሩ ከነበሩት ሥራ አስኪያጁ ኔልሰን አባዲያ ጋር የቅርብ ግንኙነት አላች።
“በ2016 (እአአ) ታዳጊዎችን አሠለጥን ነበር። ሊንዳ በታዳጊዎች ቡድን ውስጥ ነበረች። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ስወስዳት 12 ዓመቷ ነበር። ከዚያም ነው እያደገች የመጣችው” በማለት ኔልሰን አባዲያ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“ከካንሰር ድኖ እዚህ መድረስ ይቻላል”
ሊንዳ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ሕይወትን የተቀላቀለችው ገና በ14 ዓመቷ ነው። በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2019 የኮሎምቢያው ክለብ አሜሪካ ደ ካሊን ተቀላቀለች። በዚያው ዓመት ኅዳር ወር ላይ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ጥሪ ደረሳት።
ሆኖም ይህ ማንሰራራት ሆዷ ላይ በሚሰማት ህመም ተገታ። በ2020 የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓለምን እየረበሻት በነበረበት ወቅት፣ እሷም ህመሟ እየጠና ሄደ። ስትመረመርም የእንቁላል ማኩረቻ ካንሰር (Ovarian cancer) እንዳለባት ተነገራት።
ምርመራው ከተካሄደ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ዕጢ ለማስወገድ ቀዶ ህክምና የተደረገላት ሲሆን፣ በዚህም አንደኛው የእንቁላል ማኩረቻ (ኦቫሪ) እንዲወገድ ተደረገ።
ሊንዳ ከካንሰር ህመሟ ማገገም ቻለች። ለዚህም ቤተሰቧ እንዲሁም የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ አባዲያ ያደረጉላትን ድጋፍ ረድቶታል።
“አስቸጋሪ ወቅት ነበር። አምላክ ይመስገን ያንን ማለፍ ችያለሁ” የምትለው ሊንዳ “ቤተሰቦቼም ሁልጊዜ ከጎኔ ነበሩ እና እንዲሁም አሠልጣኜ አልተለየኝም” ትላለች።
“አሠልጣኜ [አባዲያ] በርካታ ጊዜ ይደውልልኝ ነበር። አንድ ቀን ቀዶ ህክምና እየሄድኩ በጣም ከፋኝ። ከዚህ በኋላ በደንብ እግር ኳስ መጫወት እንደማልችል ተሰማኝ። እሱም ዘና በይ። አይዞሽ ትመለሻለሽ አለኝ። ስለዚህ አሠልጣኜን ማመስገን እፈልጋለሁ” ብላለች።
“እንደ እኔ በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ለሚያልፉ ሰዎች ይህንን ማሸነፍ እንደሚቻል ምሳሌ ነኝ” ትላለች።
ሊንዳ ከቀዶ ህክምናዋ በኋላ ለስድስት ወራት የኬሞቴራፒ (የካንሰር የጨረር ህክምና) አደርጋለች። ህክምናዋን ከጨረሰች ከቀናት በኋላም ከካንሰር ነጻ መሆኗ ተነገራት። ከዚያም ወደምትወደው የእግር ኳስ ሥልጠናዋ ተመለሰች።
ከተመለሰች በኋላም ዲፖርቲቮ ካሊ ከተሰኘው የእግር ኳስ ክለብ እና በብሔራዊ ቡድኑ መጫወትን ቀጠለች። ሊንዳ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ተሳትፋለች። በ2022 ሊንዳ በሚያስደንቅ ሁኔታ በአራት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ተጫውታለች።
እነዚህም ውድድሮች የደቡብ አሜሪካ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ሻምፒዮና፣ በኮስታሪካ ከ20 ዓመታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ፣ በሕንድ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ እና ኮፓ አሜሪካ ፌሚኒና ናቸው።
በእነዚህም ውድድሮች ዓለም ስለ ሊንዳ ድንቅ ችሎታ ለመረዳት ቻለች። በወቅቱ የኮፓ አሜሪካ አዘጋጅ የነበረችው ኮሎምቢያን ለፍጻሜ ስትደርስ የ17 ዓመቷ ሊንዳ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሆና ተመረጠች። ኮሎምቢያ በብራዚል 1 ለ 0 ብትረታም ለ2023 የዓለም ዋንጫ ማለፍ ቻለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“ገና ወጣት ነኝ፤ አሁንም መማር አለብኝ”
በዚህ ዓመት የካቲት ሊንዳ 18 ዓመት ደፍናለች። ልደቷን ካከበረች ከጥቂት ቀናት በኋላም ለሪያል ማድሪድ ፈርማለች። በኮሎምቢያው የዓለም ዋንጫ ቡድን ውስጥ ለስፔን ክለቦች ከሚጫወቱ ሰባት እግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል አንዷ ሆናለች።
“ለመሻሻል እና ለማደግ ከአገርሽ መውጣት አለብሽ። በተጨማሪም የደጋፊዎች እና የአሠልጣኞች ድጋፍ አግዞኛል” ስትል የምታስረዳው ሊንዳ “በሪያል ማድሪድ ቦታዬን ያረጋገጥኩት በዚሁ መንገድ ነው” ብላለች።
“ከአስራ ሰባት ዓመት በታች፣ ከ20 ዓመት በታች ተጫውቻለሁ። በአሁኑ ወቅት ብዙ ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች ጋር በዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ከዚህ ቀደም ያደረግኳቸው ጨዋታዎች ረድተውኛል። በዚህም የዓለም ዋንጫ ላይ ከዚህ ቀደም ያገኘሁት ልምድ እንደሚረዳኝ ይሰማኛል” ስትልም ታስረዳለች።
“ገና አሁንም በጣም ወጣት ነኝ። አሁንም ብዙ መማር አለብኝ። በዚህ ቡድን ውስጥ በየቀኑ ልምድ አገኛለሁ። ይህ የመጀመሪያዬ የዓለም ዋንጫ ነው። በዚህም መደሰት እፈልጋለሁ። ብዙ ጊዜ አለኝ” ብላለች ሊንዳ።
የኮሎምቢያ ብሔራዊ ቡድን ረዳት አንጀሎ ማርሲግሊያ ሊንዳን “ምርጥ ችሎታ” ያላት ሲሉ ነው የሚገልጿት።
“ኳሱን ትፈልጋለች። በጭራሸ አትደብቅም። ከሌላ ፕላኔት የመጣች ናት። በጣም ልዩ ናት” ሲሉም ያክላሉ።












