ኤሊየን፡ የማናውቃቸው ፍጥረታት ምድራችንን እየጎበኟት ይሆን?

ኤሊየንና የማይታወቅ በራሪ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሌክስ ዲየትሪኽ እንደተለመደው የበረራ ሥልጠናዋ እንጂ ሌላ የሚያሳስባት ነገር አልነበረም።

የዩናይትድ ስቴትስ ባሕር ኃይል አባል የሆነችው አሌክስ፣ ሳን ዲዬጎ አቅራቢያ በሚገኘው የፓሲፊክ ውቅያኖስ ሰማይ ላይ ሽር ብትን ትላለች።

ኤፍኤ 18፣ ኤፍ ሱፐር ሆርኔት የተባለችው ተዋጊ ጄትን ይዛ ተመሳሳይ የጦር አውሮፕላን የያዘ የሥራ አጋሯን በመስኮት አሻግራ እያየች ትበራለች።

አሌክስ እና የሥራ አጋሯ አገር ሰላም ብለው ሥልጠናቸውን እያጧጧፉት ሳለ አንድ ድምፅ በራድዮ መልዕክት መስጫቸው መጣ።

ዩኤስኤስ ፕሪንስተን ከተሰኘችው የጦር መርከብ የመጣው ድምፅ፣ አንድ አጠራጣሪ በራሪ አካል ታይቷልና እሱን አጣሩ የሚል ነው።

ይህ ምንነቱ ያልታወቀ በራሪ አካል 80 ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ (24.2 ኪሎ ሜትር ርቀት) ታይቷል። ነገር ግን ድንገት ልብ በሚያርድ ፍጥነት ዝቅ ብሎ ወደ ውቅያኖሱ ከወረደ በኋላ እልም ብሎ ይጠፋል።

ይህ በራሪ ቁስ መጨረሻ የታየበት ሥፍራ ሁለቱ ጄቶች ሲመጡ የውቅያኖሱ ውሃ ልክ እሣት ላይ የተጣደ ይመስል ይፍለቀለቃል።

ትንሽ ቆይቶ አሌክስ አንድ ነገር ተመለከተች። በግምት 12 ሜትር ርዝመት ያለው ነጭ በራሪ ቁስ የውቅያኖሱ ላይ ይንሳፈፋል።

አሌክስ ይህን ቁስ ስትገልጸው ልክ ቲክ ታክ የተባለውን ከረሜላ ይመስላል ትላለች።

ይህን የክኒና ቅርፅ ያለው ቁስ ቀረብ ብለው ለመመልከት አብራሪዎቹ ጠጋ ሲሉ በራሪው አካል በብርሃን ፍጥነት ወደ ሰማይ ወጥቶ ይሰወራል።

ይህ የሆነው በፈረንጆቹ 2004 ነው። ኒው ዮርክ ታይምስ የተባለው ጋዜጣ ከጄቶቹ አንዱ በካሜራው ያስቀረውን ምስል ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል።

ይህ ምስል እውነተኛ ስለመሆኑ የአሜሪካ መከላካይ መሥሩያ ቤት - ፔንታገን ቆይቶም ቢሆን አረጋግጧል።

ይህ ክስተት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ተመሳሳይ ክስተቶች መካከል አንዱ ቢሆንም፣ በአሜሪካ ባለሥልጣናት ትኩረት ይሰጠው የጀመረው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነው።

የአሜሪካ መንግሥት በ2021 (እአአ) ዩፎ አሊያም unidentified flying object (ምንነታቸው ያልታወቀ በራሪዎች አካላት) የሚለውን መጠሪያ ቀይሯል።

አዲሱ ስማቸው ዩኤፒ ነው (Unidentified Aerial Phenomena) ይህም ምንንቱ ያልታወቀ የአየር ላይ ክስተት እንደማለት ነው።

የአሜሪካ የህዋ ምርምር ተቋም ናሳ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን መረጃ ለአሜሪካ ኮንግረስ እንዲያቀርብ ጥሪ ተደርጎለታል።

አሜሪካ ‘ኤሊየንስ’ ከሚባሉት እንግዳ ፍጥረታት ጋር ውስብስብ ግንኙነት የጀመረችው ከ76 ዓመታት በፊት ነው። በራሪ አካላት፣ ታይተው የማይታወቁ መብራቶች፣ ‘ኤሪያ 51’. . . በሚል ሲጠቀሱ ቆይተዋል።

አሁን ጥያቄው እነዚህን ባዕድ አካላት በተመለከተ የሚነዙ የሤራ ትንታኔዎችን በትክክል መመርመር ካለባቸው ክስተቶች እንዴት መለየት ይቻላል የሚል ነው።

የማይታወቁ በራሪ አካላትን ከቻይና ፊኛ አሊያም ለየት ያለ ቅርፅ ከያዘ ደመና የሚለያቸው ምንድነው? አጥኚዎች በአሁኑ ወቅት ለዚህ ጉዳይ የበለጠ ትኩረት የሰጡትስ ለምን ይሆን?

ሳተላይት

የፎቶው ባለመብት, iStock

በአውሮፓውያኑ 1974 ክረምት ወራት ላይ ከካሊፎርኒያ እስከ ቴክሳስ በአሜሪካ ግዛቶች አንድ ወሬ ይሰራጭ ጀመሮ ነበር።

ብዙዎች ከዚህ በፊት አይተው የማያውቁት የዲስክ ቅርጽ ያለው በራሪ ቁስ ሰማይ ላይ ማየታቸውን ይናገሩ ጀመር።

ይህ ወሬ ቀድሞ የተሰማው ከአንድ አብራሪ እና የንግድ ሰው የመጣ ነው። አንድ ሞተር ባላት አውሮፕላኑ ተመትቶ የወደቀ አውሮፕላን እየፈለገ የነበረው ኬኔት አርኖልድ 10 ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ በተራራማ የዋሺንግተን አካባቢ እጅግ የሚያብረቀርቅ ነገር ይመለከታል።

አተኩሮ ሲመለከት ዘጠኝ ቁሶች ሰማይ ላይ በጣም በአስገራሚ ፍጥነት ሰጓዙ መመልከቱን ይናገራል።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነው አሜሪካዊያን ሰማይ ላይ ታዩ ከሚባሉ የማይታወቁ ፍጥረታት ጋር ውስብስብ ግንኙነት የጀመሩት።

ከዚህ ክስተት በፊት በአሜሪካ ምንም ዓይነት ዩፎም በሉት ኤሊየን አሊያም ታይቶ የማይታወቅ በራሪ ቁስ ስለመታየቱ የተባለ ነገር የለም።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት በርካታ አሜሪካውያን አይተነው የማናውቀው በራሪ ሰማይ ላይ ተመልክተናል የሚል ሪፖርት አድርገዋል።

ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ይህ የሆነበት ምክንያት አንድም ሰዎች ቤታቸው ቁጭ ብለው ተፈጥሮን ማስተዋል መጀመራቸው አሊያም ትኩረታቸውን መስጠታቸው ነው።

ነገር ግን የማናውቀው በራሪ አካል ሰማይ ላይ አየን ያሉት ነዋሪዎች ብቻ አይደሉም።

የአሜሪካ መንግሥት ይፋ እንዳደረገው በ2021 (እአአ) አውሮፕላን አብራሪዎች እና ሌሎች ባለሙያዎች ከ350 ጊዜ በላይ መሰል ቁስ ተመልክተናል የሚል ሪፖርት አድርገዋል።

ምንነታቸው ያልታወቀ በራሪዎች አካላት እንዲህ ያለ ገጽታ እንዳላቸው ሲነገር ቆይቷል
የምስሉ መግለጫ, ምንነታቸው ያልታወቀ በራሪዎች አካላት እንዲህ ያለ ገጽታ እንዳላቸው ሲነገር ቆይቷል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ያም ሆኖ ናሳ ከመረመራቸው 800 በላይ ቁሶች መካከል ከ2 አስከ 5 በመቶ ያሉት ናቸው ለትንታኔ ከባድ ሆነው የተገኙት።

ናሳ እነዚህን ክስተቶች በሁለት ይከፍላቸዋል። የመጀመሪያዎቹ ግዙፍ ፊኛዎች፣ አሊያም ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) ወይም ደግሞ የተፈጥሮ ክስተቶች ሆነው የተገኙ ናቸው።

ሁለተኛ ሆነው የተቀመጡት ደግሞ በአጋጣሚ የሚፈጠሩ ዐይን የሚያጥበረብሩ ክስተቶች ናቸው።

እንደ ምሳሌ ብሪታኒያዊው የጠፈር ተመራማሪ በዓለም አቀፍ የጠፈር ምርምር መንኩራኩር ውስጥ ሳለ የሆነ ነገር ይመለከታል።

ይህ ቁስ አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት. . . እያለ ቁጥሩ እየጨመረ ይሄዳል። በድንጋጤ ልቡ የራደው የጠፈር ተመራማሪ አሊየኖች እየወረሩት ነበር የመሰለው።

በኋላ ሲጣራ ከሩሲያው የጠፈር ምርምር ማዕከል እየፈሰሰ ያለ ውሃ ጠብ ሲል ወደ አብረቅራቂ በረዶነት እየተቀየረ ብርሃን እያንፃባረቀ ነበር።

የናሳ ሳይንቲስቶች አሁን ተስፋ አላቸው። አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ተንቀሳቃሽ ስልክ አለው። እነዚህ ስልኮች ምስል ማስቀረት ይችላሉ። ይህ ደግሞ ወደፊት የሚታዩ ክስተቶችን ምንነት መለየት የበለጠ ቀላል እንዲሆን ያደርገዋል።

የናሳ ዓላማ ከምንኖርበት ምድር ውጭ የመጡ አሊየኖችን መለየት አይደለም። እርግጥ ነው ይህ አይሆንም ማለት አይደለም።

ናሳ እያደረገ ያለው በምድራችን ዙሪያ የተፈጥሮ ክስተቶችን ጨምሮ ምን እየተካደሄደ ነው የሚለውን መመርመር ነው።

ነገር ግን ጉዳዩ አዲስ ነገር ከማግኘት የመነጨ ብቻ አይደለም። ማንኛውም ሰማይ ላይ የሚከሰት ነገር ለሳተላይቶችም ሆነ ለአውሮፕላኖች አደጋ ሊሆን ይችላል።

በለተይ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እንደ አሸን በፈለቡት በዚህ ዘመን ከየት ወደ የት እንደሚበሩ መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ ናሳ ያምናል።

ሰማይ ላይ እየሆነ ያለውን ነገር ለመለየት እና ለማወቅ ዘመን ያፈራቸው ጥራታቸው የላቀ ካሜራዎችን ማዘጋጀት ግድ ይላል።

አሌክስ እና የሥራ አጋርዋ ውቅያኖስ ላይ ያጋጠማቸውን አይተው ወደ ጣቢያቸው ሲመለሱ፣ አብዛኞቹ ሰዎች ሁኔታውን በፈገግታ ነው ያለፉት።

ኬኔት አርኖልድ በ1947 (እአአ) ቃለ-መጠይቅ ሲደርግለት “እኔ ፕሬዝዳንት ብሆን ኖሮ እና የሆነ ሰው ይህን አየው ቢለኝ ለማውቅ እጓጓ ነበር” ማለቱ ይታወሳል።