በላሊበላ አምሳያ ስለታነጹት የዳግማዊ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ምን ያህል ያውቃሉ?

የፎቶው ባለመብት, Stuart Butler
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ኢትዮጵያ የነበራትን ድንቅ የኪነ-ህንጻ ጥበብ ማሳያ እና አሻራ ናቸው።
ከስምንት መቶ ዓመታት በፊት ከአንድ ወጥ አለት ተፈልፍለው የተሠሩት እነዚህ አብያ ክርስቲያናት የዓለማችን ድንቅ ቅርስ ሆነው መመዝገብ ችለዋል።
በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም በሆነው ዩኔስኮም በዓለም ቅርስነት ተመዝግበዋል። ኢትዮጵያንም የሚጎበኙ በርካታ ቱሪስቶች ከሚጎበኟቸው ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ስፍራዎች መካከል አክሱም እና ላሊበላ ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው።
በርካታ ጎብኚዎች ስለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ቢያውቁም፣ በተመሳሳይ ከወጥ አለት ተወቅረው ስለተሠሩት “አዲሱ ላሊበላ” ግን ብዙም አይሰማም። ቢቢሲ በአንድ ትጉህ መነኩሴ እና ባህታዊ የተሠሩትን የዳግማዊ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን ጎብኝቷል።
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በመላዕክት ዕገዛ እንደተሠሩ በአፈታሪክ ይነገራል። በሰሜን ኢትዮጵያ ከአለት ስር የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት በ12ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በንጉሥ ላሊበላ የታነጹ ናቸው። በኋላም የቅዱስነት ማዕረግ የተሰጠው ንጉሥ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን ያነጸው በአምላክ ትዕዛዝ ነው ብሏል።
የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት የተገነቡበት ጊዜ የመስቀል ጦርነት የተፋፋመበት ወቅት ነው። በርካታ የክርስትና አማኞች ኢየሩሳሌም የሚገኙ ሃይማኖታዊ ስፍራዎችን ለመጎብኘት አደገኛ የሆነበት ወቅት በመሆኑ ላሊበላ “አዲሲቷ ኢየሩሳሌም” እንድትሆን ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Stuart Butler
ለኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን መንፈሳዊ ጉዞዎችን የሚያደርጉበት ስፍራ እንዲሆኑ ታስበው ነው የታነጹት።
በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ውስጥ እጅግ አስደናቂ ታሪካዊ ቦታ የሆነውን ላሊበላን ለመጎብኘት በርካቶች ይጎርፋሉ።
አብያተ ክርስቲያናቱ ከወጥ አለት ተቀርጸው ስለታነጹበት ሁለት ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ የአካባቢው አስጎብኚ አቶ ወርቅዬ ደሳለ አለሙ ይናገራሉ።
የመጀመሪያው የሚጠቅሱት በዚያን ወቅት የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ ወራሪዎች አብያተ ክርስቲያናትን አውድመዋል። እናም ንጉሥ ላሊበላ ከአለት ስር መገንባታቸው ጥቃት ከሚያደርሱ ጠላቶች ተደብቆ እንዲቆይ በሚል ሲሆን፣ ይህም ትክክል ነው ይላሉ።
ሌላኛው የሚሰጡት ምክንያት “ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ዋሻ ውስጥ ተወልዶ በጎልጎታ ዋሻ ውስጥ ተቀበረ” በሚለውም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ለንጉሥ ላሊበላን እንዲገነባ እንዳነሳሳው ነው አስጎብኚው የሚናገረው።
ንጉሥ ላሊበላ በዚህ መንገድ ለማነጹ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት በሥነ ሕንጻ እጅግ አስደናቂ ሥራዎች ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Stuart Butler
ከቤተ ክርስቲያናቱ መካከል አንዱ የሆነው ቤተ መድኃኒያለም 33 ሜትር ርዝመት፣ 23 ሜትር ስፋት እና 10 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን፣ በዓለማችን ላይ ከአንድ ወጥ ድንጋይ ተወቅረው ከተሠሩ አብያተ ክርስቲያናት መካከልም ትልቁ ነው።
ሌላኛው ቤተ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን አስደናቂ እና ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ ከድንጋይ መቀረጹ ይታወቃል። “አዲሲቷን ኢየሩሳሌምን” ለማነጽ ትልቅ ህልም እና ጽናት የሚጠይቅ ነው።
ንጉሥ ላሊበላ ይህንን ታሪክ ድንቅ የሚለውን ሥራ ካጠናቀቀ በኋላ ተመሳሳይ ግንባታን ማንም ሊሞክረው አይችልም ብለው ያስቡ ይሆናል። ነገር ግን ከላሊበላ በስተደቡብ 60 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ባለ ብቸኛ ተራራ ላይ አንድ ትጉህ መነኩሴ እና ሁለት ዲያቆናት ከአለት በመፈልፈል ድንቅ የሆኑ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን በማነጽ ተጠምደዋል።
በዋናነት መነኩሴው እና ሁለቱ ዲያቆናት ዳግማዊ ላሊበላን እየገነቡ ነው።
ሁሉንም የማነጽ ሥራ ያካሄዱ ያሉት በእጃቸው ሲሆን፣ የጀመሩትም ከአስራ ሦስት ዓመታት በፊት ነው። እስካሁንም ሰባት አብያተ ክርስቲያናትን ከአንድ አለት ድንጋይ ፈልፍለው የሰሩ ሲሆን እንደ ላሊበላ ግንባታው ሲጠናቀቅ 11 ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ይኖሩታል።
አብያተ ክርስቲያናቱን እያነጹ ያሉት መነኩሴ እና ባህታዊ የሆኑት አባ ገብረ መስቀል ተሰማ አብዛኛውን ቃለ መጠይቅ ጊዜ አይሰጡም።
ነገር ግን ለቢቢሲ እንደተናገሩት አብያተ ክርስቲያናቱን እየገነቡ ያሉበት አንደኛው ምክንያት የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት በውጭ አገር ባለሙያዎች እርዳታ ታንጸው መሆን አለበት የሚለው እሳቤ የተሳሳተ መሆኑን ለማሳየት ነው ብለዋል።
ሌላኛው ዳግማዊ ላሊበላን በዚህ ስፍራ እየገነቡበት ያለው ምክንያት በአካባቢው ጸበል ስላለ እንዲሁም በንጉሥ ላሊበላ የተጀመረ እና ያልተጠናቀቀ የዋሻ ቤተ ክርስቲያን በመኖሩ እንደሆነ አባ ገብረ መስቀል ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Stuart Butler
ዳግማዊ ላሊበላ በግንባታውም፣ በቅርጹም ሆነ በግንባታ ጥበቡ ከዋናው ላሊበላ ጋር በጣም ተመሳሳይ ነው።
ሁለቱም ጎልተው የሚታዩ አንዳንዴም በቀለም ያሸበረቁ ከውስጥም ከውጭ ከአለት ድንጋይ የተፈለፈሉ ቅርጾችን ይዘዋል።
በዳግማዊ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት አንደኛው የላሊበላውን ቤተ ጊዮርጊስን በሚመስል መልኩ በመስቀል ቅርጽ ተፈልፍሎ እና ተቀርጾ ነው የተሠራው።
ነገር ግን የዳግማዊ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ከየትኛው የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት በመጠን ያነሱ ናቸው። በተጨማሪም ሌላ የሚለያቸው ነገር የግንባታቸው ቅደም ተከትል ነው።
በዋነኛው የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት የውስጥ እና የውጭ ክፍላቸው በተመሳሳይ ጊዜ እንደተፈለፈለ እና እንደተቀረጸ ይታመናል። በዳግማዊ ላሊበላ ደግሞ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ውጫዊው ክፍላቸው ነው መጀመሪያ የተፈለፈለው።
በሚያስደንቅ ሁኔታ አባ ገብረ መስቀል አብያተ ክርስቲያናቱን በማነጽ ለዓመት ያህል ብቻቸውን ነው ሥራውን ያከናወኑት። በአሁኑ ወቅት ሁለት ዲያቆናት ያግዟቸዋል።
ሆኖም የዲያቆናቱ የሥራ ድርሻ በግንባታው ሂደት የሚፈጠሩ ፍርስራሾችን በማንሳት እና በማጽዳት ብቻ የሚያግዟቸው ሲሆን፣ አባ ገብረ መስቀል የአለት ድንጋዩን በመፈልፈል፣ በመቅረጽ እና በማነጹ በኩል ብቻቸውን ዋናውን ሥራ ያከናውናሉ።

የፎቶው ባለመብት, Stuart Butler
“አባ ገብረ መስቀል አብያተ ክርስቲያናቱን በሚገነቡበት ወቅት ምግብ አይቀበሉም። እንዲሁም ሻማ፣ ጧፍም ሆነ ሰው ሰራሽ መብራትን አይጠቀሙም” ሲልም ከዲያቆናቱ አንዱ ለቢቢሲ ተናግሯል።
“የአብያተ ክርስቲያናቱን ውስጣዊ ክፍል ሲፈለፍሉ እና ሲቀርጹ በጨለማ ውስጥ ሆነው ነው” በማለት አክሏል። አባ ገብረ መስቀል እነዚህን ቤተ ክርስቲያናት ለመገንባት የሚጠቀሙበት መሠረታዊ የግንባታ መሳሪያዎችን ብቻ ነው።
አለቱን ለመፈልፈያነት የሚጠቀሙባቸው አነስ ያለች መጥረቢያ እና መዶሻዎች ልክ በንጉሥ ላሊበላ ዘመን የተጠቀሙበትን ዓይነት የግንባታ መሳሪያዎችን ብቻ ነው። በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ ግንባታዎች በስፋት ጥቅም ላይ የሚያውሏቸው ጡቦች፣ ሲሚንቶ፣ ጣውላ... እዚህ የሉም። በተጨማሪም የሥነ-ህንጻ ዕቅድ የሌለው ሲሆን፣ ሁሉም ልኬቶች የሚከናወኑት በዐይን ነው።
“እነዚህን ባህላዊ የግንባታ ቴክኒኮች መጠቀም ሰዎች የበለጠ መንፈሳዊ ቁርጠኝነት እንዲሰማቸው ያደርጋል” ብለዋል አባ ገብረ መስቀል።
ከአምስት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለአባ ገብረ መስቀል ግንባታዎች ዕውቅና በመስጠት አብያተ ክርስቲያናቱ ተቀድሰው አገልግሎቶችን መስጠት ጀምረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Stuart Butler
በአሁኑ ጊዜ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ለአካባቢው ማኅበረሰብ እና ለጎብኚዎች በመደበኛነት ይካሄዳሉ። ደብዘዝ ያለ ብርሃን ያላቸው የአብያተ ክርስቲያናቱ ውስጣዊ ክፍሎችም በሃይማኖታዊ ሥዕላት እና ቁሶች ተሞልተዋል። አብያተ ክርስቲያናቱን በማንኛውም ዕለት መጎብኘት ይቻላል።
ከወጥ ድንጋይ የተወቀሩትን ሰባቱን አብያተ ክርስቲያናት ገንብተው ጨርሰዋል። በአሁኑ ወቅት በአለቱ ላይ መገንቢያ ቦታ ባለመኖሩም አብዛኛውን ሥራቸውን አቁመው ሌላ ተስማሚ ቦታ እየፈለጉ ነው።
በዚህም ቦታ የመጨረሻዎቹን አራቱን አብያተ ክርስቲያናት ለመገንባትም አቅደዋል። አጠቃላይ ግንባታውን በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የማጠናቀቅ ሃሳብ አላቸው።
በመጪዎቹ መቶዎች ዓመታት ውስጥ ዳግማዊ ላሊበላ ዛሬ ላሊበላ ያለውን ስፍራ እና አድናቆት በጎብኚዎች ዘንድ እንደሚያገኝም ተስፋን ሰንቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Stuart Butler












