አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በኬንያዊቷ ተይዞ የነበረውን የ5 ሺህ ሜትር ክብረ ወሰን ሰበረች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትላንት ዕሁድ መስከረም 6/2016 ዓ.ም. በአሜሪካዋ ኦሪገን፣ ዩጂን በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ የ5 ሺህ ሜትር ውድድር ጉዳፍ ጸጋይ የዓለም ክብረ ወሰንን በማሻሻል አሸነፈች።
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ10 ሺህ ሜትር አሸናፊዋ ጉዳፍ የትላንቱን ውድድር 14 ደቂቃ ከ00.21 በመጨረስ ነው ውድድሩን ያሸነፈችው።
ጉዳፍ በኬንያዊቷ ፌዝ ኪፕዬጎን ተይዞ የነበረውን የዓለም ሴቶች የ5 ሺህ ሜትር ወድድር ክብረ ወሰን በ5 ሰከንዶች አሸሽላለች።
ፌዝ ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ነበር ፓሪስ ላይ በተደረገ ውድድር 14 ደቂቃ ከ05.20 ሰከንድ በመግባት ለ8 ዓመታት በገንዘቤ ዲባባ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን መስበር ችለ ነበር።
ሆኖም ኬንያዊቷ ፌዝ ይዛው የነበረውን የርቀቱን ክብረ ወሰን ጉዳፍ ወደ 5 ሰከንድ ገደማ አሻሽላዋለች።
የውድድሩ የመጨረሻ ደውል ላይ በ12 ደቂቃ ከ55 ሰከንድ ላይ የደረሰችው ጉደፍ የመጨረሻውን መስመር 14 ደቂቃ ከ00.21 ላይ አልፋዋለች።
በዚህ ውድድር ኬንያዊቷ ቢትሪስ ቼቤት ጉዳፍን በመከተል በ14 ደቂቃ 05.92 ሰከንድ በመጨረስ የርቀቱን ሶስተኛ ፈጣኝ ሰዓት አስመዝገባለች። ኢትዮጵያዊቷ እጅጋየሁ ታዬ ደግሞ ውድድሩን በሶስተኝንት አጠናቃለች።
በሌላ የዳይመንድ ሊግ ውድድር ኢትዮጵያዊ ዮሚፍ ቀጀልቻ በ3000 ሺህ ሜትር ውድድር በሁለተኝነት አጠናቋል።
ይህንን ውድድር የ22 ዓመቱ ኖርዌያዊ ኢንግብሪትሰን በአንድኝነት ጨርሷል።












