የ800 ከብቶች ባለቤትና የ52 ልጆች አባት የሆኑት የአርሲው አዛውንት

የፎቶው ባለመብት, Jarso Deksiso
በኦሮሞ ባሕል ከብቶች ትልቅ ቦታ አላቸው። የተወደዱ ናቸው። የከብት ባለቤት በከብቶቹ ይወደሳል።
ድሮ ድሮ ባለጸግነትም በከብት ብዛት ይገለጽ ነበር። አርብቶ አደር በሆኑ አካባቢዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ከብቶች ባለቤትን መመልከት የሚያስደንቅ ነገር አልነበረም።
አሁን አሁን ግን ይህ ታሪክ እየሆነ መጥቷል።
በአርሲ ዞን አጄ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት የ75 ዓመት አዛውንት ግን ሃብታቸው ዛሬም ድረስ የሚለካው እንደከዚህ ቀደሙ ባሏቸው ከብቶች፤ በሚያልቧቸው ላሞች ብዛት ነው።
አቶ ጃርሶ ዳክሲሶ ስማቸው የሚነሳው ከ800 በላይ በሆኑት ከብቶቻቸው ብቻ አይደለም። አምስት ሚስቶች አሏቸው። ከአምስቱ ሚስቶቻቸው ደግሞ 52 ልጆችን አፍርተዋል።
አዛውንቱ በየዓመቱ ከ80 ከማያንሱ ላሞቻቸው የሚያልቡት ወተት እጅግ በጣም ብዙ ከሆኑት ቤተሰቦቻቸው አልፎ ለጎረቤት ይበቃል፤ ለገበያም ይቀርባል።
አቶ ጃርሶ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከብቶቻቸውን የሚቆጥሩት ለግጦሽ የሚሰማሩት እና በበረት ውስጥ የሚውሉ በማለት በሁለት ጎራ በመክፈል ነው።
“ለግጦሽ የሚሰማሩ 800 ከብቶች አሉኝ። ይሄ ከላሞች ጋር የሚሄዱ ጥጆችን ይጨምራል” ይላሉ።
አዛውንቱ በጠቅላለው ከ800 በላይ የሚሆኑ ከብቶች አሏቸው።
አዛውንቱ ይህን ያህል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ከብት ባለቤት እንዴት ሊሆኑ ቻሉ?
አቶ ጃርሶ ከወላጆቻቸው በውርስ ያገኙት ከብት እንዳለ ቢገልጹም እርሳቸውም በረዥም ዓመታት ከብት ማርባታቸውን ይናገራሉ።
“ሳረባ ነው የኖርኩት። ከአባቴ የወረስኩት አለ። እኔም ያረባሁት አለ። አንድ ላይ ተደማምሮ ነው እዚህ የደሰው። እርግጥ ከአባቴ 42 የሚሆኑ ከብቶች ወርሻለሁ” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ ጃርሶ ከከብቶች በተጨማሪ በርካታ የጋማ ከብቶችን ጨምሮ በጎች እና ፍየሎች አሏቸው።
“ፍየል እና በጎች በድምሩ 150 አለኝ። አህዮች እና ፈረሶች ደግሞ ወደ 50 አሉኝ።” ይላሉ።
አቶ ጃርሶ ከብቶቻቸውን የሚያግዱላቸው ከሰባት ያላነሱ እረኞች አሏቸው።
አቶ ጃርሶ በከብት እርባታ ብቻ አይደለም የሚኖሩት። ሰፊውን ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር የእርሻ ሥራም ይሠራሉ።
ከአምስት ሚስቶቻቸው 52 ልጆችን መውለዳቸውን የሚናገሩት አቶ ጃርሶ የልጅ ልጆቻቸውን ጨምሮ አጠቃላይ የቤተሰቡ አባላት ከ100 እንደሚያልፍ ይናገራሉ።
አቶ ጃርሶ በሚኖሩበት አርሲ ዞን አጄ ሻለ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከእርሳቸው በተጨማሪ በርካታ ሰዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ከብቶች ባለቤት መሆናቸውን ይናገራሉ።
የእሳቸው የበኩር ልጅ እንኳን ከ300 ያላነሱ ከብቶች እንዳሉት ይገልጻሉ።
አቶ ጃርሶ በየዓመቱ እስከ 95 ላሞችን እንደሚያልቡ የሚናገሩ ሲሆን ከላሞቻቸው የሚገኘው ወተት ለቤተሰብ እንደሚቀርብ እና የተረፈውን ወተት እና የወተት ተዋጽኦ እንደሚሸጡት ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, ABDURHAAMAN RUBE
“ወተት ለሰው እንሰጣለን፤ እረኞች ይጠጣሉ፤ እንግዳ ይጠጣል። እናቶች መውጣት ያለበትን ቅቤ እና አይብ አውጥተው አጄ ከተማ ወስደው ይሸጣሉ።”
አቶ ጃርሶ በየሳምንቱ ከወተት እና የወተት ተዋጽኦ ከፍተኛ ገቢ እንደሚያገኙ ይናገራሉ።
ካሏቸው ከብቶች መካከል በመቶ የሚቆጠሩት በሬዎች የእርሳቸውን እና የዘመዶቻቸውን መሬት እንደሚያርሱም ይገልጻሉ።
አቶ ጃርሶ ከ800 በላይ የሆኑት ከብቶች የእሳቸው ይሁኑ እንጂ ልጆቻቸው እና የልጅ ልጆቻቸው ከብቶቹን እንደራሳቸው ንብረት እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ።
“በቁጥር የኔ ናቸው ይባሉ እንጂ በጣም ብዙ ሰው ነው የሚጠቀምባቸው። ለተቸገሩት፣ ከልጆቼ ለተጋቡ 10 ወይም 20 ከብቶች እያደረኩት እየመደብኩ እነሱ ናቸው የሚጠቀሙባቸው” ብለዋል።
አቶ ጃርሶ ከከብት እርባታ በተጨማሪ በሰፊ የእርሻ ሥራ ተሰማርተው ስኬታማ ገበሬ ናቸው። አቶ ጃርሶ በመቶዎች የሚቆጠሩ በሬዎች ቢኖሯቸውም እርሻ የሚያከናውኑት በትራክተር ነው።
“ከ40 ሄክታር በላይ አርሳለሁ። ትልቁ ምርቴ ቦቆሎ ነው።”
ከቦቆሎ በተጨማሪ ቦሎቄ፣ ድንች እና ዳጉሳ እንደሚያመርቱ አዛውንቱ ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, ABDURHAAMAN RUBE
‘ኪለ ሊጡ’
በአርሲ እና ባሌ አካባቢ ብዙ ከብቶችን ያፈሩ ሰዎች የሚፈጽሙት ‘ኪለ ሊጡ’ ወይም (ጉድጓድ ውስጥ መጥለቅ) የሚባል የቀደመ ሥነ-ሥርዓት አለ።
በዚህ ሥነ-ሥርዓት ባለ ብዙ ከብት ባለቤት በቁመቱ ልክ ጉድጓድ ከተቆፈረ በኋላ ጉድጓዱ በወተት ይሞላል። ከዚያም የከብት ባለቤቱ በወተት ወደተሞላው ጉድጓድ ገብቶ በመውጣት ሥነ-ሥርዓቱን ይፈጽማል።
አቶ ጃርሶ ምንም እንኳ የከብቶቻቸው ቁጥር ከ800 ቢሻገርም ይህን ሥነ-ሥርዓት እስካሁን መፈጸም አለመቻላቸውን ይናገራሉ።
ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በሲኮ እና መንዶ ባሕል መሠረት የ'ኪለ ሊጡ' ሥነ-ሥርዓት መፈጸም የሚቻለው በአንድ ዓመት ውስጥ 100 ጊደሮች የመጀመሪያ ጥጆቻቸውን ከወለዱ ብቻ ነው።
አቶ ጃርሶ በየዓመቱ እስከ 95 ላሞቻቸው ጥጆች ቢወልዱም በአንድ ዓመት ግን እስካሁን ድረስ 100 ጊደሮች አለመውለዳቸውን ይገልጻሉ።
ሕይወት ከገጠር ወደ ከተማ
አቶ ጃርሶ ዕድሜ ዘመናቸውን በገጠራማ አካባቢ ቢኖሩም በቀጣይ ሕይወትን ከተማ ለመመስረት ማሰባቸውን ይገልጻሉ።
ለዚህ ደግሞ ትልቁ ምክንያታቸው ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ለከብቶቻቸው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ማግኘት ከግዜ ወደ ግዜ ፈታኝ እየሆነ በመምጣቱ መሆኑን ይናገራሉ።
“በየዓመቱ ከብቶች እና ጥጆችን ውሃ ለማጠጣት ብዙ ገንዘብ ነው የማወጣው። ለአንድ መኪና ውሃ ከ7-10ሺህ ብር ነው የምገዛው” ብለዋል።
አዛውንቱ የከብቶቻቸውን ቁጥር በመቀነስ ፊታቸውን ከገጠር ሕይወት ወደ ከተማ የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“የከብት እርባታ ሥራ በጣም አድካሚ ሥራ ነው” የሚሉት አቶ ጃርሶ፤ ስለ ልጆቻቸው ሲያወሩ አሁን ሁሉም ወደ ትምህርት፣ ወደ ንግድ ሥራ እና ሹፌርነት ፊታቸውን አዙረዋል። ሕይወትን በከተማ እየመረጡ ነው። ፈጣሪ ካለ እነዚህን ከብቶች ወደ ገንዘብ ለመቀየር እያሰብን ነው” ብለዋል።
አቶ ጃርሶ በአጄ ከተማ ሕንጻ መገንባት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
የዚህ ሕንጻ የታችኛው ክፍል ለባንክ መከራየቱን እና በዚችው አጄ ከተማ “ቡና ቤት” መክፈታቸውን እና መጋዘንም እንዳላቸው ይናገራሉ።
አቶ ጃርሶ ልጆቻቸው በአጄ እና ሻሸመኔ ከተሞች በትምህርት ላይ እንደሚገኙ የገለጹ ሲሆን ለልጆቻቸው እና ለሚስቶቻቸው ከወዲሁ ውርሳቸውን ከፋፍለው መጨረሳቸውን ይገልጻሉ።












