የትንሳዔ ገበያ፡ በወሊሶ አካባቢ 115 ሺህ ብር የተገዛው በሬ

የፎቶው ባለመብት, West Shoa Ilu Wereda Communucation
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ለሚከበረው ለትንሳኤ በዓል በየአካባቢው ለአውደ ዓመት የሚቀርቡ የእርድ እንስሳትና ሌሎች ምርቶች ሞቅ ባሉ የግብይት ስፍራዎች ለሽያጭ ይቀርባሉ።
በዚህም ሁሉም እንደ አቅሙ እና ፍላጎቱ ይሸምታል። በዓልን በዓል ከሚያስመስሉ ነገሮች መካከል ደግሞ አንዱ የገበያው ድባብ ነው።
ዶሮ፣ እንቁላል፣ ቄጤማ፣ ቅቤ፣ ፍየል፣ በግ፣ በሬው ገበያውን በስፋት ይቆጣጠሩታል። ሸማችና ሻጭ በዋጋ ክርክር ይወዛገባሉ።
የከተሞች ዋና መንገዶች በእርድ እንስሳት፤ በሰው ትርምስ ይሞላሉ።
በዚህ ሁሉ መካከል አንዱ ሸማች ሌላኛውን የገበያውን ውሎ ይጠይቃል። መቼም ቢሆን "ርካሽ ነው" የሚል ወሬ ከገበያተኛ አይሰማም።
እኛም ከሰሞኑ አንድ በሬ በ115 ሺህ ብር ስለመሸጡ ሰምተናል።
115 ሺህ ብር አውጥተው ይሄን ግዙፍ ሰንጋ የገዙት ሰው ደግሞ አቶ አሸብር ናቸው።
አቶ አሸብር ጎሳ ባልቻ የከብት ነጋዴ ናቸው።
ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ወሊሶ አካባቢ በሚገኝ የከብት ገበያ ከቀናት በፊት በሬውን በ115ሺህ ብር መግዛታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ አሸብር 115 ሺህ ብር ስለወጣበት በሬ ምን አሉ?
"በሬው ትልቅ ነው። ሁለት ዓመት አካባቢ ነው የተቀለበው። በሬውን የገዛሁት ከገበሬ ነው። ሻጩ ሦስት ዓመት ሲቀልበው እንደነበር ነግሮኛል" ሲሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
እሳቸው የተፍኪ ከተማ ነዋሪ ናቸው። በሬውን የገዙት ደግሞ ኢሉ ወረዳ ተጂ ውስጥ ነው።
"እኔ የከብት ነጋዴ ነኝ። ለሥጋ ቤት ወይም በበዓሉ ሰሞን ዝግጅት ላላቸው ወይም ሆቴል ለሚያስመርቁ ሰዎች ለመሸጥ ነው ያሰብኩት። ያው እንደ ገበያው ሁኔታ ሆኖ እስከ 3ሺህም 2ሺህም አትርፌ እሸጣለሁ። እንደ ገበያው ነው።" ብለዋል።
ለዚህ ከብት 115ሺህ ብር አውጥተው የገዙት በገበያው ሁኔታ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ አሸብር፤ "ፋጉሎ እኮ እስከ 3ሺህ ብር እያወጡ ነው የሚገዛው። ይሄ በሬ ሁለት እና በሦስት ዓመት ሲቀለብ ስንት ኩንታል ጨርሷል የሚለውን ማሰብ ነው።" ሲሉ ዋጋው ያን ያህል እንዳልተጋነነ በስሌት አስረድተዋል።
እንዲህ በውድ ዋጋ የተሸጠ በሬ ከዚህ በፊት ያውቁ ይሆን?
እኔ እስከማውቀው በትልቅ ብር የተሸጠው በሬ ይሄ ነው። ትልቁ ይሄ ነው። ከዚህ በታች ያለው 85ሺህ፣ 75ሺህ፣ 65ሺህ የሚሸጥ አለ።
በግ ራሱ 12ሺህ ብር ተሽጧል። ዳዎ ወረዳ ቡሳ ከተማ አንድ በግ 12 ሺህ ብር ተሽጧል።
በሌሎች አካባቢስ ከፍተኛው የከብት ዋጋ ስንት ይሆን? መልካም በዓል!












