ለ45 ደቂቃ አርምሞ ማድረግ የደም ግፊትን ይቀንስ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES
አዳዲስ ጥናትና ምርምሮች አዳዲስ ግኝትን ይዘው ይመጣሉ።
በቅርብ የተደረገ አንድ ጥናት ለደም ግፊት የ45 ደቂቃ አርምሞ ፈውስ ይሰጣል የሚል ምክርን ይዟል።
በተለይ ጭንቀትና ውጥረት ያለባቸውና በዚህም ደም ግፊታቸው የሚቀሰቀስባቸው በቀን ውስጥ የ45 ደቂቃ አርምሞ ወሳኝ ነው ይላሉ ባለሙያዎች።
የዓለም የደም ግፊት ማኀበር ከአርምሞ በተጨማሪ ለስላሳ ሙዚቃ ማዳመጥ እና ዮጋ መሥራንት ይመክራል።
የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች ማጨስ ማቆም አለባቸው። ጨው በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ አለባቸው። ከዚህ ጎን ለጎን ግን በቀን ውስጥ ከግማሽ ሰዓት ያላነሰ አርምሞ ያስፈልጋቸዋል።
በደም ግፊት የጤና ጆርናል ላይ የታተሙ ጥናቶች እንደሚያስረዱት ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰዎች በመንፈሳቸው የተረጋጉ፣ ጥሞና የሚያዘወትሩ ሲሆኑ ጤናቸው መለስ ይላል።
የዩኬ የደም ግፊት ባለሙያ ፕሮፌሰር ብራያን ዊሊያምስ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጥሞናና አርምሞ ከካርዲዯቫስኩላር ሲስተም ጋር ያለው ቁርኝት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አብራርተዋል።
በደም ግፊት የሚሰቃዩ ሰዎች ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው። በቀን ውስጥ የተወሰኑ ደቂቃዎችን ለጥሞና እና አርምሞ ሰጥተው አልያም ዘና የሚያደርግ የእግር ጉዞ በማድረግ አልያም ሙዚቃ በመስማት ጤናቸው ላይ ብዙ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ።
ከፍተኛ የደም ግፊት በዓለም ላይ ብዙ ሰዎችን ያለ ጊዜ ከሚገድሉ በሽታዎች አንዱ ነው።
በልብና በደም ቧንቧዎች ላይ ጫና በመፍጠር በጊዜ ሒደት ልብ ላይ ጉዳት የሚያመጣ በሽታ ነው።
የደም ግፊት ቀስ በቀስ ስትሮክ እና ሌሎች ተያያዥ የልብ በሽታዎችን በማስከተል ለሞት ይዳርጋል።
በዓለም ከአራት አዋቂ ሰዎች አንዱ የደም ግፊት አለበት። ይህም በጠቅላላ አንድ ቢሊዮን የዓለም ሕዝብ በደም ግፊት ይሰቃያል ማለት ነው።
የደም ግፊትን ያስታግሳሉ ከሚባሉትና በቅርብ ጊዜ ጥናቶች ከተለዩት መፍትሄዎች መካከል ዮጋ እና የትንፋሽ ልምምዶች ይጠቀሳሉ።
ከዚህ ሌላ በጎ በጎውን ማሰብ እና አመስጋኝ መሆን ለልብ መረጋጋት ያግዛሉ።
ቅንነት እንዲሁም መልካም ተግባርን ማከናወን፣ መጠነኛ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግም ይመከራል።
‘’በየዕለቱ ማንኛንም ለልብ እርጋታን የሚሰጥ ተግባር ማከናወን ለደም ግፊት መጠነኛ ፈውስ ይሰጣል’’ ይላሉ ፕፎፌሰር ዊሊያምስ።
ከዚህ ሌላ በቀን ውስጥ በቂ እንቅልፍ ማግኘት እና ከስልክ ሱስ መላቀቅ፣ አእምሮውን ወደ ውጥረት ከሚከቱ ሌሎች ማንኛውም ተግባራት መታቀብ ይመከራል።
ፕሮፌሰር ዊሊያምስ ‘’በቂ እንቅልፍ ሲባል ረዥም ሰዓት መተኛት ብቻ አይደለም፤ የእንቅልፉ ጥራትም ወሳኝ ነው’ ሲሉ ያስገነዝባሉ።
አንዳንድ ሰዎች ለ7 ሰዓት እንቅልፍ ቢያገኙም ጥሩ እንቅልፍ ካላገኙ ትርጉም የለውም።
ጥሩ እንቅልፍ ለማግኘት ደግሞ አእምሮ በጥሩ መረጋጋት ላይ ሊሆን ይገባል። ጭንቀትን መቀነስ ይገባል። ለዚህም ነው አርምሞና ጥሞና ወሳኝ የሚሆኑት።
በምግብ ረገድ ደግሞ ኦሜጋ-3 ሊሰጡ የሚችሉ እንደ ሳልመን ዓሣ መመገብ ይመከራል። ፋይበር ያላቸው አትክልቶችን ማብዛትም ሌላው ጠቃሚ ነገር ነው።
ሻይና ቡና በመጠኑ መጠጣት ችግር የለውም። ነገር ግን ካፊን የበዛባቸው መጠጦች ለደም ግፊት አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ።
ቀይ ሥር፣ የፖም ጁስ (pomegranate) የደም ግፊትን ዝቅ ስለሚያደርጉ ይመከራሉ። ምክንያቱ ደግሞ በውስጣቸው ኒትሬት ስለሚይዙ ነው። ኒትሬት ደግሞ የደም ቧንቧ ዘና እንዲል ያደርጋል።
የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች የሰውነት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የመኪና ጭስ በማይበዛበት ፓርኮች አካባቢ እንዲሆኑ ይመከራል። ምክንያቱም የተበከለው አየር ልብና ሳምባ ላይ ጉዳት ስለሚያመጣ ነው።
ሌላው ሐኪም ዶ/ር ፓውሊን ፈጣኑ የደም ግፊትን ማስታገሻ መንገድ ጨውን ማስወገድ ነው ይላሉ። “ጨው ምግብ ውስጥ እየጨመሩ ባይሆን እንኳ ብዙዎቹ የፋብሪካ ምግቦች በውስጣቸው ጨው ስላለ ጎጂ ይሆናሉ” ሲሉ ያስገነዝባሉ።
ብዙ ጨው ሰውነት ውስጥ ገባ ማለት ተጨማሪ ውሃ ሰውነት እንዲያጠራቅም ይሆናል፤ ይህ ደግሞ የደም ግፊትን ያስከትላል።
ፍራፍሬና አትክልት በየቀኑ መመገብ፣ በየቀኑ መጠነኛ የሰውነት እንቅስቀሴ ማድረግ፣ በተለይም ሳይከል መጋለብ፣ ዋና መዋኘት፣ ዳንስ መደነስን ይመክራሉ ሐኪሙ።
ዋናው ነጥብ የደም ቧንቧዎች ዘና እንዲሉ ማድረግ ነው። ዋናው ነጥብ ደም ዘና ብሎ በደም ቧንቧ እንዲንሸራሸር ማድረግ ነው።
ለዚህም ነው ጥሞናና አርምሞ ለደም ግፊት ታማሚዎች የሚመከሩት።












