ራስል ብራንድ የጾታዊ ትንኮሳ እና የመድፈር ውንጀላዎች ቀረበበት

ራሰል ብራንድ

የፎቶው ባለመብት, PA MEDIA

ኮሜድያን እና ተዋናይ ራሰል ብራንድ በዝና ማማ ላይ በነበረባቸው ሰባት ዓመታት ውስጥ በመድፈር፣ ጾታዊ ትንኮሳ እና የሥነ ልቡና ጥቃት በማድረስ ውንጀላዎች ቀረቡበት።

ውንጀላዎቹ የቀረቡት ሰንዴይ ታይምስ፣ ዘ ታይምስ እና ቻናል 4 በጋራ ባካሄዱት ምርመራ ነው።

እኤአ ከ2016-2013 ባለው ጊዜ ውስጥ አራት ሴቶች ወሲባዊ ትንኮሳ አድርሶብናል ሲሉ ክሳቸውን አሰምተዋል።

ብራንድ ግን ውንጀላዎቹን በሙሉ የካደ ሲሆን፣ የነበረው ግንኙነት “ምን ጊዜም በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ነበር” ብሏል።

ብራንድ ውንጀላው በቀረበባቸው ዓመታት ውስጥ በተለያዩ ከፍተኛ ስም ባላቸው ድርጅቶች እንደ ቢቢሲ ራዲዮ 2፣ ቻናል 4 እንዲሁም በሆሊውድ በተዋናይነትን ይሰራ ነበር።

በምርመራው ብራንድ ላይ ከቀረቡት ውንጀላዎች መካከል ጥቃት አድራሽ መሆኑ ፣ በየት ወጣችሁ በየት ገባችሁ የሚል ተቆጣጣሪ እና የሄዱበትን አነፍንፎ የሚከተል መሆኑ ተገልጿል።

የምርመራው ውጤት በሰንደይ ታይምስ የታተመ ሲሆን፣ የምርመራ ዘገባውን የያዘው ‘ራሰል ብራንድ- ኢንፕሌይን ሳይት’ የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ደግሞ በቻናል 4 ቅዳሜ ዕለት ለዕይታ በቅቷል።

ራሰል ብራንድ በአሁኑ ሰዓት የኮመዲ ስራዎቹን በተለያዩ ስፍራዎች እያቀረበ ሲሆን ውንጀላው ለሕዝብ ይፋ በሆነ በሰዓታት ውስጥም 2000 ሰዎችን በሚይዝ የቴአትር አዳራሽ ውስጥ የኮመዲ ስራውን ለሕዝብ አቅርቧል።

ለአንድ ሰዓት ያህል መድረክ ላይ በቆየበት ወቅትም ውንጀላው መቅረቡን ጠቀስ ቢያደርግም በቀጥታ ግን ጉዳዩን በሚመለከት አስተያት ከመስጠት ተቆጥቧል።

ለታዳሚዎቹ ማውራት የሚፈልጋቸው ጉዳዮች እንዳሉ ነገር ግን እንደማይፈልግ ገልጿል።

ብራንድ ላይ ክሳቸውን ካቀረቡ ሴቶች መካከል አራቱ የደረሰባቸውን ትቃት በዝርዝር እነዲህ በማለት አስረድተዋል።

ከብራንድ ጋር ሎስ አንጀለስ ትሰራ የነበረች ሴት እደተናገረችው በሎስ አንጀለስ በሚገኘው ቤቱ ከግድግዳ ጋር አላትሞ ያለፍላጎቷ እና ያለ ኮንዶም ደፍሯታል። በዚያው ዕለት ለተደፈሩ ሴቶች ድጋፍ ወደሚሰጥ ማዕከል ሄዳ የሕክምና ድጋፍ አግኝታለች። ዘ ታይምስ ይህንን ውንጀላ በሕክምና ማስረጃ ሪፖርትን ማስደገፉን ጠቅሷል።

ሌላኛዋ ሴት ደግሞ ብራንድ በ30ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ እያለ እና እርሷ የ16 ዓመት አዳጊ እያለች ትንኮሳ እንዳደረሰባት ተናግራለች።

በነበራቸው ግንኙነት ወቅትም በየት ወጣሽ በየት ገባሽ የሚል፣ የሥነ ልቡና ጥቃት የሚያደርስ እንደነበር “ትንሿ ልጅ” እያለም ይጠራት እንደነበር አክላለች።

ሦስተኛዋ ሴት በበኩሏ በሎስ አንጀለስ ከእርሱ ጋር ትሰራ በነበረበት ወቅት ጾታዊ ትንኮሳ እንዳደረሰባት ገልጻ ስለጉዳዩ ለማንም ትንፍሽ ብትል ሕጋዊ እርመጃ እወስዳለሁ ሲል እንዳስፈራራት ተናግራለች።

አራተኛዋ ሴት በበኩሏ ከጾታዊ ጥቃት ባሻገር አካላዊ እና ሦነልቡናዊ ጥቃትም እንዳደረሰባት ተናግራለች።

ራሰል ብራንድ የኮመዲ ስራውን እያቀረበ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አርብ ዕለት ራሰል ውንጀላዎቹን በተመለከተ በቪዲዮ ምላሽ የሰጠ ሲሆን እርሱ ላይ ሆን ተብለው ተቀነባብረው የቀረቡ “ የወንጀል ክሶች ሁሉ” አልፈጸምኩም ሲል አስተባብሏል።

ተዋናይና ኮሜድያን ራሰል ብራንድ ከጋዜጣው እና ከቴሌቪዥን ጣብያው “ ጥቃቶችን የያዘ ዝርዝር” ደብዳቤ እንደ ደረሰው አክሏል።

በዩቲዩብ እና በኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) ላይ በለጠፋቸው ቪድዮዎች ብራንድ “ . . . የቀረቡብኝን ክሶች ሙሉ በሙሉ እቃወማለሁ። እነዚህ ክሶች የቀረቡብኝ በትልልቅ ሚዲያዎች ላይ በምሰራበት ወቅት፣ በጋዜጦች ላይ በምጽፍበት ወቅት፣ በፊልሞች ላይ በምተውንበት ጊዜ ነው እናም በመጽሐፎቼ ላይ እንዳሰፈርኩት በወቅቱ በጣም በጣም በርካታ የወሲብ ጓደኞች ነበሩኝ።

ይኹን እንጂ ከበርካታ ሴቶች ጋር ወሲባዊ ግንኙነት በነበረኝ ሰዓት ሁሉም በስምምነት ላይ የተመሰረተ ነበር” ሲል አብራርቷል።

ብራንድ “የተቀናጀ ጥቀት እንደተከፈተበት” እንደሚያምን ከገለጸ በኋላ የቀረቡበት ውንጀላዎች “ከረር ያሉ” በመሆናቸው በሚገባ እንደሚያጤናቸው ተናግሯል።

ፖሊስ የኮሜዲያኑን ስም በይፋ ባይገልጽም “በሚድያ ላይ ስለቀረቡ የወሲብ ትንኮሳ ወንጀሎች” መስማቱን አስታውቆ ምንም ዓይነት የክስ ፋይል ግን አለመቅረቡን አስረድቷል።

“ማንም ሰው ወሲባዊ ትንኮሳ እንደደረሰበት የሚያምን ከሆነ፣ ጊዜው ምንም ያህል ቢርቅ ወደ ፖሊስ ቀርቦ ጉዳዩን እንዲያስረዳ እንመክራለን” ሲል አክሏል።

ዘ ሰንዴይ ታይምስ ሁሉም ሴቶች ጋዜጠኞች ካናገሯቸው በኋላ ጉዳያቸውን ወደ ፖሊስ መውሰድ እንዳለባቸው እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

ጋዜጣው አክሎም በርካቶቹ ይህ እንዲሰማቸው ያደረገው ብራንድ በኦንላየን ላይ አዲስ እያገኘ የመጣው የጤና አንክብካቤ ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ እንደሆነ ተናግረዋል።

እንደጋዜጣው ዘገባ ከሆነ በርካቶቹ ብራንድ ላይ ውንጀላቸውን ያቀረቡ ሴቶች እርስ በእርስ የማይተዋወቁ ሲሆን ማንነታቸውም እንዲገለጽ አይፈልጉም።

ዘ ሰንዴይ ታይምስ ለብራንድ ስለቀረቡበት ውንጀላዎች ምላሽ እንዲሰጥ ስምንት ቀናት ቢሰጠውም፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ግን በዩቲዩብ ቻናሉ ላይ ቀርቦ ክሶቹን ማስተባበል መርጧል።

ብራንድ በርካታ የሬድዮ እና የቲቪ ፕሮግራሞችን በቻናል 4፣ ኤምቲቪ፣ ራዲዮ ኤክስ እና ቢቢሲ ላይ ይመራ ነበር።

እኤአ በ2000ዎቹ መጀመርያ ላይ በኮመድያንነት የጀመረው ራሰል ብራንድ፣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ‘ቢግ ብራዘርስ ቢግ ማውዝ’ የተሰኘ ፕሮግራም ላይ የመድረክ መሪ በመሆን እውቅናን አገኘ።

ከዚያ በኋላም በሆሊውድ የተለያዩ ፊልሞች ላይ ተውኗል።

ራሰል ብራንድ የጾታዊ ትንኮሳ እንዳደረሰባቸው ከተናገሩ ሴቶች መካከል አንዷ የሆነችው የ16 ዓመት አዳጊ፣ ጉዳዩ በተፈጸመበት ወቅት፣ እኤአ 2020፣ ወደ ወኪሎቹ በማምራት የተፈጸመባትን ተናግራ እንደነበር አስረድታለች።

የብራንድ ኤጀንት በመሆን በወቅቱ ይሰራ የነበረው ታቪስቶክ ውድ፣ ለቢቢሲ እንደተናገረው በወቅቱ ብራንድ ጉዳዩን ሽምጥጥ አድርጎ ክዷል።

“. . . አሁን እንደምንረዳው ግን ፈጽሞ አሳስቶናል። ድርጅታችን ከብራንድ ጋር ያለውን የትኛውንም ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አቋርጧል” ሲል አክሏል።

የቻናል 4 ቃል አቀባይ በበኩላቸው ብራንድ የፈጸማቸውን ነገሮች ሲሰሙ በከፍተኛ ሁኔታ ማዘናቸውን ተናግረው፣ ይህ ጉዳይ ደግሞ ራሰል በድርጅታቸው ይሰራ በነበረባቸው ዓመታት ውስጥ የተፈጸሙ በመሆናቸው ጉዳዩን በአንክሮ እንዲመለከቱት ማድረጉን ተናግረዋል።

እንደ ቃል አቀባዩ ማብራርያ ከቀረቡ ውንጀላዎች ተነስተው ጉዳዩ በወቅቱ ለድርጅታቸው ሪፖርት ተደርጎ እንደሆን በሚል ምርመራ ያደረጉ ቢሆንም በወቅቱ ምንም ዓይነት ክስ ወደ ድርጅቱ አለመምጣቱን ተረድተዋል።

ነገር ግን አሁንም ቢሆን በደረሳቸው መረጃ ተነስተው ምርመራቸውን እንደሚቀጥሉ፣ በወቅቱ ፕሮግራሞቹን ያዘጋጁ የነበሩ ድርጅቶችም የቀረቡ ወንጀላዎችን መሰረት በማድረግ ዳግም ፍተሻ እንዲያካሄዱ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የ16 ዓመቷ ታዳጊ ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ያደረሰው ብራንድ ቢቢሲ ራድዮ 6 ሚዩዚክ ላይ በሚሰራበት ወቅት ነው።

በጣብያው ላይ በሚሰራበት ወቅት ብራንድ ስቱድዩ ውስጥ ልብሱን ያወልቅ እንደነበር ተገልጿል።

የቀጥታ ፕሮግራም ስርጭት ላይ እያለም ስለ ሌላ ዜና አንባቢ ወሲብ ነክ የሆኑ አስተያየቶችን ይሰጥ እንደነበር ተሰንዶ ተቀምጧል።

በዚህ ድርጊቱ የተነሳም የቢቢሲ ፕሮዳክሽን ባልደረቦች በወቅቱ ይቅርታ እንዲጠይቅ አድርገውታል።

የቢቢሲ ቃል አቀባይ ብራንድ ቢቢሲን የለቀቀበት ምክንያትን ሲያስታውሱ በ2008 የኢዲቶርያል ሕጎችን በመጣሱ መሆኑን ተናግረዋል።

በወቅቱም የጣሰው ኢዲቶርያል በዝርዝር የተቀመጠ መሆኑን በማስታወስ ቢቢሲ እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮችን በዋዛ እንደማይመለከታቸው እና እርምጃ ከመውሰድም ወደ ኋላ እንደማይል ገልፀዋል።