በሞሮኮ ርዕደ መሬት የ32 ተማሪዎቿን ሕይወት ያጣችው መምህርት

የትምህርት ቤት ቦርሳዎች

የፎቶው ባለመብት, Adaseel School

ከሰሞኑ በሞሮኮ አስከፊ የርዕደ መሬት ተከስቷል።

በሬክተር ስኬል 6.8 የሆነው ርዕደ መሬት የአንድ ክፍል ተማሪዎችን ህይወት ቀጥፏል።

አዳሴል በተባለችው እና የርዕደ መሬቱ ማዕከል አቅራቢያ በሆነችው መንደርም አስደንጋጭ ሁኔታ ተከስቷል።

በወቅቱ ማራኬሽ በምትባል ከተማ የነበረችው መምህርቷ ናስሪን አቡ ኤልፋዴል ርዕደ መሬቱን ስትሰማ ልቧ ተሸበረ።

የአረብኛ እና ፈረንሳይኛዋ መምህርት ተማሪዎቿን ፍለጋ ወደ ተራራማዋ መንደር ያቀናችው በድንጋጤ ነው።

ሆኖም 32ቱም የአንድ ክፍል ተማሪዎቿ ህይወት መቀጠፉን ሰማች። ዕድሜያቸውም ከስድስት እስከ 12 ነው።

ልቧ አላረፈም። መሞታቸውን ብትሰማም ተማሪዎቿ የት አሉ? በማለት መወትወቷን አላቆመችም

“ወደ መንደሩ ሄጄ ስለ ልጆቼ መጠየቅ ጀመርኩ። ሶማያ የት ነው? የሱፍ ነው? ይህች ልጅ የት ነው? ያ ልጅ የት ነው?” የክፍሏን ተማሪዎች አንድ በአንድ መጥራት ብትቀጥልም መልሱ ከሰዓታት በኋላም ቢሆን ‘ሁሉም ሞተዋል’ የሚል ነበር።

“በክፍል ውስጥ የሁሉንም የ32 ተማሪዎቼን ስም እየጠራሁ አቤት የሚሉኝን አስታወስኩ። አሁን ሁሉም ላይመለሱ ይህችን አለም ጥለዋት ሄደዋል” ስትልም ለቢቢሲ ተናግራለች።

ህጻናቱ ጳጉሜ 3/2015 ዓ.ም አመሻሽ ላይ በሞሮኮ በተመዘገበው አስከፊው ርዕደ መሬት ከተገደሉት ወደ 3 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ተካተዋል።

በክፍል ውስጥ እየተማሩ ያሉ ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Adaseel School

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በርዕደ መሬቱ በከፍተኛው የተጠቁት ከማራኬሽ በስተደቡብ ያሉ ስፍራዎች ሲሆኑ በርካታ የተራራማ መንደሮች ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ወድመዋል። ተማሪዎቹ የሞቱባት አዳሴልም ከነዚህ ስፍራዎች አንዷ ናት።

ናስሪን በጣም ከምትወዳቸው ተማሪዎቿ አንዷ የሆነችው የስድስት ዓመቷ ከድጃ ምን እንደደረሰባት ሰምታለች።

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች የህጻኗን አስከሬን ያገኙት ከወንድሟ መሃመድ እና ከሁለት እህቶቿ ሜና እና ሃናን አጠገብ ነበር።

ሁሉም ናስሪን በምታስተምርበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ነበሩ። አልጋቸው ላይ የተገኙት እነዚህ ታዳጊዎች በርዕደ መሬቱ ወቅት ምናልባት ተኝተውም ይሆናል።

“ከድጃን በጣም እወዳት ነበር። ደስ የምትል፣ ጎበዝ፣ ንቁ እና መዝፈንም ትወድ ነበር። መኖሪያ ቤቴም ትመጣ ነበር። ከሷ ጋር ማውራት እና ማጥናት ያስደስተኝ ነበር” ብላለች መምህርቷ።

መምህርቷ ገና በልጅነታቸው ያጣቻቸውን ተማሪዎች “መላዕክት” ስትልም ትገልጻቸዋለች። ለትምህርት የሚጓጉ፣ ሰው አክባሪዎች ነበሩም ትላለች።

ቤተሰቦቻቸው ከከፋ የኑሮ ውድነት እና ድህነት ጋር እየታገሉ ቢሆን ትምህርትን ለተሻለ ህይወት አማራጭ በማድረግም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ አላቅማሙም።

“የመጨረሻው የትምህርት ክፍለ ጊዜያችን አርብ ማታ ነበር- አካባቢዋ በርዕደ መሬቱ ከመታቷ ከአምስት ሰዓታት በፊት” የምትለው ናስሪን “የሞሮኮን ብሔራዊ መዝሙር እያጠናን ነበር እናም ሰኞ ማለዳ በሁሉም ተማሪዎች ፊት ለመዘመርም አቅደን ነበር” በማለትም ትናገራለች።

ምንም እንኳን ናስሪን በተረጋጋ ድምጽ ብትናገርም ጥልቅ ሃዘን እና ህመም ላይ ናት። በተማሪዎቿ እና በትምህርት ቤቷ ላይ የደረሰውን ነገር ለመቀበል እየታገለች ትገኛለች።

“እንቅልፍ የለኝም፣ አልተኛም። አሁንም በድንጋጤ ውስጥ ነኝ” ትላለች።

“ሰዎች በህይወት በመትረፌ ከዕድለኞች እንደ አንዷ አድርገው ይመለከቱኛል። ለኔ ግን ቀጣዩ ህይወቴን እንዴት እንደምገፋው አላውቅም” ብላለች።

የፈረሰው የአዳሴል ትምህርት ቤት

በመንደሯ በዋነኝነት የሚኖሩት የአማዚግ ማህበረሰብ ናቸው። ቋንቋቸውም ታማዚት ነው። በዚህችም መንደር ናስሪን ለህጻናቱ አረብኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋን ማስተማር ያስደስታት ነበር።

"አረብኛ እና ፈረንሳይኛ ለመማር በጣም አስቸጋሪ ቋንቋዎች ናቸው። ነገር ግን ተማሪዎቼ በጣም ብሩህ ነበሩ። ሁለቱንም ቋንቋዎች እያቀላጠፉ ነበር” በማለትም ታስታውሳለች።

ናስሪን ለወደፊቱ በማስተማር ህይወቷን ለመግፋት አቅዳለች።

በርዕደ መሬቱ የፈረሰውን የአዳሴልን ትምህርት ቤት ባለስልጣናቱ እንደሚገነቡትም ተስፋን ሰንቃለች።

በሞሮኮ በተከሰተው ርዕደ መሬት ምክንያት በአጠቃላይ በ530 የትምህርት ተቋማት ላይ በተለያየ ደረጃ ጉዳት ደርሶባቸዋል። አንዳንዶቹ ሙሉ በሙሉ የወደሙ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ውስን ጉዳቶችን ማስተናገዳቸውን ሪፖርቶች ገልጸዋል።

የሞሮኮ መንግሥት በርዕደ መሬቱ በከፋ በተጠቁ አካባቢዎች ለጊዜው ትምህርት እንዲቆም ትዕዛዝ አስተላልፏል።

"ምናልባት አንድ ቀን ትምህርት ቤቱን መልሰው ሲገነቡ እና የመማር ማስተማሩ ሂደት ወደቀደመው ሲመለስ በርዕደ መሬቱ በአሳዛኝ ሁኔታ ያጣናቸውን 32 ልጆቻችን ልናስታውሳቸው እና ታሪካቸውን ልንነግር እንችላለን" ብላለች።