በከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ስለተመታችው ሞሮኮ 12 አጫጭር እውነታዎች

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
በከባድ ርዕደ መሬት የተመታችው ሞሮኮ ከ2ሺህ በላይ ዜጎቿን አጥታለች። በዚህ አጋጣሚ ስለ ሞሮኮ አጫጭር መረጃዎችን እናቀበላችሁ።
1/ ሞሮኮ በትንሹ የአራት ባሕሎች ቅይጥ ናት። አረብ፣ በርበር፣ አውሮፓዊና አፍሪካ። ለዚህም ነው የባሕል መዲና በሚል ቅጽል የምትታወቀው። በዓመት 10 ሚሊዮን ቱሪስት ሞሮኮን ይጎበኛል።
2/ ሞሮኮ የባሕር ድርቻዎች ሜዲትራኒያንን ብቻ ሳይሆን አትላንቲክ ውቅያኖስንም ይዋሰናሉ። የጠረፉ መጠነ ዙርያ ከ200 ኪሎ ሜትር በላይ ነው።
3/ ሞሮኮ እንደ አውሮፓዊያኑ ከ1912 እስከ 1956 ድረስ በፈረንሳይ ጥበቃ ሥር ነበረች። ይሁንና ነጻነቷን በይፋ ያወጀችወው በ1956 ዓ/ም ነበር።
4/ ከሰሜን አፍሪካ አገሮች ሁሉ በምዕራብ አቅጣጫ ጥግ የምትገኘው ሞሮኮ ማግሪብ በሚለው ስሟ በአረቦች ዘንድ ትታወቃለች። ማግሪብ ማለት ‘ምዕራብ’ ማለት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
5/ ሞሮኮ እንደ አውሮፓዊያኑ በ1975 ደቡባዊ ጎረቤቷን ዌስተርን ሳሃራዊን በኃይል እጇ አስገብታለች። የስፔን ቅኝ የነበረችው ዌስተርን ሰሐራዊ ሪፐብሊክ አሁንም ድረስ ሞሮኮ የግዛቷ አካል አድርጋ ነው የምትወስዳት። 16 ዓመታት ከፈጀ ጦርነት በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ያሸማገለው ስምምነት ቢኖርም ዛሬም ድረስ ግን ሞሮኮ በሰሐራዊ ሪፐብሊክ ሕዝበ ውሳኔ አላደረገችም። አልጄሪያ የሰሐራዊን ፖሊሳሪዮ ፍሮንት ትደግፋለች በሚል ከሞሮኮ ጋር ጤናማ ግንኙነት የላትም።
6/ ሞሮኮ ዋና ከተማዋ በሰሜናዊ ክፍል የሚገኘው ራባት ሲሆን ከ2 ሚሊዮን ያነሰ ሕዝብ ይኖርበታል። ነገር ግን ትልቅ ከተማ አይደለም። ከራባት በቅርብ ርቀት የሚገኘው ካዛብላንካ ከተማ ደግሞ ከዚህ እጥፍ የሚሆን ሕዝብ ይኖራል። አሁን በርዕደ መሬት የተመታችው ማራካሻ ደቡባዊ ከተማ ስትሆን በውቡ የአትላስ ተራራ ምክንያት ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት ያላት ናት።
7/ ሞሮኮ በሕዝብ ብዛቷ 38 ሚሊዮን ደርሷል። አረብኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ በርበር እና አሜዚ ቋንቋዎች በስፋት ይነገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty image
8/ ሞሮኮ ሕገ መንግሥታዊ ዘውጋዊ አገዛዝ ያላት ሲሆን አሁን የሞሮኮ ንጉሥ መሐመድ ስድስተኛ ይባላሉ። በዓለም ረዥም ዘመን ካስቆጠሩ ዘውድ ሥርዓቶች አንዱ የሞሮኮ ዘውድ ሥርዓት ነው። ሞሐመድ 6ተኛ ከአባታቸው ዙፋኑን የተረከቡት እንደ አውሮፓዊያኑ በ1999 ዓ/ም ነበር። ንጉሡ በአባታቸው ዘመን የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲመረመሩ በማድረጋቸውና ለሴቶች የተሻለ ነጻነት በመስጠታቸው ይወደሳሉ።
9/ በሞሮኮ ሚዲያዎች በመንግሥት ወይም ለንጉሣዊ ቤተሰብ ቅርብ በሆኑ ባለሃብቶች የተያዙ ናቸው። ሃይማኖትን እና ንጉሡን መተቸትም አይችሉም። የሞሮኮ 99% ሕዝብ የሱኒ ሙስሊም ተከታይ ነው።
10/ አሜሪካ የዌስተርን ሰሃራዊ ሪፐብሊክን ዕውቅና ስትሰጥ ቆይታለች። ነገር ግን ሞሮኮ ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ለመቀጠል በመስማማቷ ትራምፕ በ2020 ዓ/ም ዌስተርን ሳሃራዊ ሪፐብሊክ የሞሮኮ አካል ናት በሚል እውቅና ሰጥተዋል።
11/ በሞሮኮ በተለይም ማራኬሽ እና ካዛብላንካ ከተሞች በርካታ ፊልሞች ተቀርጸዋል። በዚህ የተነሳ የአፍሪካ ሆሊውድ ትባላለች። ከነዚህ መሀል Inception (2010), Gladiator (2000), Mission impossible Rogue Nation (2015), The Jewel of the Nile (1985), The Mummy (1999), The Old Guard (2020) ይገኙበታል። የሚገርመው ካዛብላንካ (Casablanca) የተሰኘው ፊልም የተቀረጸው በሞሮኮ አይደለም።
12/ ሞሮኮ በጂብራልታር ማዶ ከስፔን ጋር ትዋሰናለች። ሞሮኮና ስፔን በዚህ መስመር ርቀታቸው 13 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው።













