በኢትዮጵያ መነጋገሪያ የሆነው ናይጄሪያዊ ድምጻዊ ሬማ ማነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ናይጄሪያዊው ድምጻዊ ሬማ በሸራተን ሆቴል በአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ የሙዚቃ ስራዎቹን ያቀርባል ከተባለ በኋላ ድምጻዊው በኢትዮጵያ መነጋገሪያ ሆኗል።
በሙሉ ስሙ ዲቫይን ኢኮቦር በመባል የሚታወቀው ድምጻዊ በአለባበሱ እንዲሁም በሙዚቃ ቪዲዮ ሰራዎቹ ላይ የሚታዩ ትዕይንቶች ክርስቲያናዊ አይደሉም የሚሉ ቅሬታዎች ሲቀርቡበት ቆይቷል።
በዚህም ምክንያት የሙዚቃ ድግሱ አዘጋጆች ድግሱን እንዲሰርዙ፤ ተመልካቾችም የሙዚቃ እንዳይታደሙ ጥሪዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ምዕመኑ ከመሰል ድርጊቶች ታቅቦ በወርሐ ጷጉሜ በንጹሕ ልቦና በጾምና በጸሎት እንዲያሳልፍ ጥሪ አቅርባለች።
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ነሐሴ 29/2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ በዓላት ሲደርሱ "ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ከሥርዓቷ እና ከአስተምሮዋ ውጪ በሆነ መልኩ የተለያዩ አካላት የዳንኪራ ጥሪ በማዘጋጀት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አግባብነት የሌለው ነው" ያሉ ሲሆን ምዕመናንም ከዚህ እንቅስቃሴ እራሳቸውን ሊያርቁ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ይህን ማሳሰቢያ ተከትሎ በዋዜማ ኮንሰርቱ የሙዚቃ ስራዎች ለማቅረብ ውል ይዘው ከነበሩት አርቲስቶች መካከል አንዷ የሆነችው አርቲስት ኩኩ ሰብስቤ “የቤተ ክርስርትያንን ጥሪ" ተከትሎ የማቀርበውን የሙዚቃ ስራ ሰርዢያለሁ ብላለች።
የሙዚቃ ድግሱ ስፖንሰር የነበረው ኮካ-ኮላ የስፖንሰርሺፕ አጋርነቴን ሰርዣለሁ ብሏል። ኮካ-ኮላ ቤቬሬጅስ አፍሪካ-ኢትዮጵያ "የስፖንሰርሺፕ አጋርነቴን በልዩ ልዩ ምክንያቶች ለመሰረዝ ተገድጃለሁ" ብሏል።
በአዲስ ዓመት ዋዜማ ኮንሰርቱ ላይ የሙዚቃ ስራዎቹን እንደሚያቀርብ የተገለጸው ሌላው እውቅ ኢትዮጵያዊ አርቲስት ልጅ ሚካኤልም እንዲሁ ተሳትፎን እንዲያቆም ጥሪ እየቀረበለት ነው።
ሬማ ማን ነው?
በኢትዮጵያ ለአዲስ ዓመት ኮንሰርት ያካሂዳል ከተባለ በኋላ የሙዚቃ ድግሱ እንዲሰረዝ ጫና የበረታበት ድምጻዊ ሬማ ዝነኛ ናይጄሪያዊ ሙዚቀኛ ነው።
ሬማ በሚለው የመድረክ ስሙ የሚታወቀው ዲቫይን ኢኮቦር እአአ በ2000 ነው ናይጄሪያ የተወለደው።
የሬማ ‘አይረን ማን' የተሰኘው ሙዚቃ እአአ 2019 የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ተወዳጅ የሙዚቃ ዝርዝር ውስጥ ከተካተተ በኋላ ከፍተኛ አድማጭ አግኝቷል።
በመላው ዓለም ተወዳጅነት ያገኘው ዘፈኑ ‘ካልም ዳውን’ ዩቲዩብ ላይ ከፍተኛ የተመልካች ቁጥር ያገኘ የናይጄሪያ ሙዚቃ ተብሎ ተመዝግቧል።
ይህን ዘፈን ከ355 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ዩቲዩብ ላይ ተመልክተውታል።
ከዚህ በፊት ሪከርዱን ይዞ የነበረው 354 ሚሊዮን ሰው ያየው የሲኬይ ‘ላቭ ንዋንቲኒ’ ነው።
በጣም ተወዳጅ የሆነው ዘፈኑ ‘ካልም ዳውን’ የናይጄሪያ ፖፕ እና አር ኤንድ ቢ ውህድ ነው።
ከአሜሪካዊቷ ድምጻዊት ሰሌና ጎሜዝ ጋር ተጣምረው ዘፈኑን ካቀነቀኑ በኋላ ሙዚቃው የበለጠ አድማጭ አግኝቷል።
በቢልቦርድ የምርጥ 100 ዘፈኖች ዝርዝር ሦስተኛ ከመሆኑም በተጨማሪ በአሜሪካ የአፍሮቢትስ ዘፈኖች ሪከርድን ለ52 ሳምንታት በአንደኛነት መርቷል።

ሬማ የተወለደው በናይጄሪያዋ ኤዶ ግዛት ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ይዘፍን፣ ራፕም ያደርግ ነበር።
ሙዚቃ የጀመረው ቤተ ክርስቲያን ነው።
በ2018 የናይጄሪያዊው ድምጻዊ ዲፕሪንስን ‘ጉቺ ጋንግ’ ሲዘፍን በኢንስታግራም ገጹ ከለቀቀ በኋላ ድምጻዊው ወደ ሌጎስ ወስዶታል።
‘ጆንዚንግ ወርልድ’ የተባለው የዲፕሪንስ ሬከርድ ሌብልም አስፈርሞታል።
ከአንድ ዓመት በኋላ ‘ሬማ’ የተባለ በስሙ የተጠራ የመጀመሪያ አልበም ለቀቀ። በናይጄሪያ አፕል ሚውዚክ አንደኛ ሆኗል።
በ2020 የሬማ ዘፈኖች በፊፋ 21 ቪድዮ ጌም ማጀቢያ ሙዚቃ ውስጥ ተካተዋል።
በ2021 ሬማ ሙዚቃዎቹን ‘አፍሮሬቭ’ ሲል መጥራት ጀመረ።
ይህም የአፍሮቢትስ ሙዚቃ ከአረብና ሕንድ ሙዚቃ ጋር የሚጣመርበት ነው። አድናቂዎቹም ‘ራቨርስ’ በሚል ቅጽል ስም ይጠራሉ።
በ2022 ለንደን ኮንሰርት እያቀረበ ሳለ ሙዚቃዎቹ በበይነ መረብ አንድ ቢሊዮን በላይ ተመልካቾች በመላው ዓለም በማግኘታቸው ሽልማት ተሰጥቶታል።
በ2022 የወጣው ‘ሬቭ ኤንድ ሮዝስ’ አልበሙ ውስጥ ከተካተቱ ሙዚቃዎች አሥሩ በአሜሪካ ቢልቦርድ የአፍሮቢትስ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።
በ2020 በቢኢቲ አዋርድስ በዓለም አቀፍ ሙዚቀኛ ዘርፍ ታጭቷል። በ2023 በሌጎስ የዓመቱ ዲጂታል አርቲስት ሽልማት አግኝቷል።
‘ካልም ዳውን’ የተሰኘው ዘፈኑ በናይጄሪያው ዘ ሄዲስ ውድድር የዓመቱ ምርጥ ወንድ ድምጻዊ ሸልማት አስገኝቶለታል።
በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብም ድምጻዊው በዚህ ዘፈን ተካቷል።












