ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ደጋሎ ‘አንድ ወታደር እስኪቀረን ድረስ እንዋጋለን’ አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ የሆኑት ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ደጋሎ “አንድ ወታደር እስከሚቀረን ድረስ እንዋጋለን” አሉ።
ወታደሮቻቸው በሱዳን መዲና “በከፍተኛ ቁጥር” እንደሚገኙም ተናግረዋል።
በአገሪቱ ጦር ሠራዊት እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል የሚካሄደው ጦርነት አምስተኛ ወር ይዟል።
ኤክስ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ ጀነራሉ ባስተላለፉት የድምጽ መልዕክት፣ በጀነራል አብዱል ፋታህ አልቡርሐን የሚመራው የሱዳን ጦር ሠራዊት ጦርነቱን በመጀመር ከሰዋል።
ደጋሎ የአገሪቱ ጦር ከሥልጣን የተወገዱትን ኦማር አል በሽር ወደ ሥልጣን ለመመለስ እየተመሳጠረ ነው ሲሉም ከሰዋል።
ከዚህ በፊት ነሐሴ መጨረሻ ላይ ባወጡት መግለጫ በድርድር ላይ የተመሠረተ ስምምነት ላይ ለመድረስና ሲቪል መር መንግሥት ለማቋቋም ጥሪ አቅርበው ነበር።
አዲሱ መልዕክታቸው ግን ነሐሴ ወር ላይ ካቀረቡት ጥሪ ጋር የሚቃረን ነው።
ነሐሴ ላይ ያቀረቡትን ጥሪ ጀነራል አልቡርሐን አልተቀበሉትም። ጦራቸው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን እንደሚያሸንፍም ተናግረዋል።
አልቡርሐን ወታደራዊ የበላይነት እንዳላቸው በሚጠቁም ሁኔታ ከነሐሴ ወዲህ በተደጋጋሚ በአደባባይ ታይተዋል። ወደ ደቡብ ሱዳን እና ግብፅም ተጉዘዋል።
ከዚህ ቀደም የጦሩ አጋር የሆነውን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “አሸባሪ ቡድን” ብሎ እንዲፈርድ ጦሩ በተደጋጋሚ ጠይቋል።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ባወጣው መግለጫ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አመራሮች ጋር መገናኘታቸው “አደገኛ ነው” ሲል ተችቷል።
ሱዳንን በጋራ ሲሟሯት የነበሩት የአገሪቱ ጦር መሪ ጀነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጀነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ አገሪቱ ወደለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት ገብታ ከፍተኛ ኪሳራ እያስተናገደች ነው። ከ7 ሚሊዮን የማያንስ ሕዝብም ቀዬውን ጥሎ ተፈናቅሏል።
በጦርነቱ ምክንያት በአገሪቱ መንግሥት አለ ማለት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። የፖሊስ ኃይል ተበትኗል። እስር ቤቶች ተሰብረዋል እንዲሁም ፍርድ ቤቶcእ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም።












