በቬትናም ጦርነት የበላይ ትዕዛዝ የጣሱት ወታደር ትልቁ የአሜሪካ ሜዳልያ ተሰጣቸው

ካፒቴን ላሪ ቴይለር

የፎቶው ባለመብት, REUTERS

የምስሉ መግለጫ, ካፒቴን ላሪ ቴይለር ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሽልማት ሲበረከትላቸው

በቬትናም ጦርነት ወቅት የተሰጣቸውን ትዕዛዝ የተላለፉት ወታደር የአሜሪካ ትልቁ የወታደር ሜዳልያ ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተሰጣቸው።

81 ዓመት የሞላቸው ካፒቴን ላሪ ቴይለር ከበላይ አለቃቸው የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ጥሰው የትግል አጋሮቻቸውን አትርፈዋል።

እአአ በ1968 ተዋጊ ሄሊኮፕተር አብራሪ የነበሩት ወታደር ውጊያ ውስጥ ቀጥታ ገብተው አራት አሜሪካውያን ወታደሮችን ከሞት አድነዋል።

ለዚህም በዋይት ሀውስ ሜዳልያ ተበርክቶላቸዋል።

ወታደሩ የወሰዱት እርምጃ ከዚያ በፊት ተሞክሮ የማያውቅ እንደነበረ የአሜሪካ ጦር ገልጿል።

ወታደሮቹን ለማዳን በወሰዱት እርምጃ በሆ ቺ ሚን ከተማ በጠላት ወታደሮች ተከበው ነበር። የሄሊኮፕተር ነዳጅ እየጨረሱ ጥይትም እያለቀባቸው ነበር።

ወደ መሬት ዝቅ ብለው በመብረር ጠላት ላይ ለግማሽ ሰዓት ከተኮሱ በኋላ አሜሪካውያኑን ወታደሮች ለማዳን እንደሚያስቸግር ሲያውቁ ወታደሮቹ ወደሌላ ቦታ እንዲዛወሩ አድርገዋል።

ወታደሮቹ ወደ አዲስ ቦታ ከተዛወሩ በኋላ ለነፍሳቸው ሳይሳሱ ሄሊኮፕተሩን አሳርፈው ወታደሮቹን ጭነዋቸዋል።

ሄሊኮፕተሩ መያዝ የሚችለው ሁለት ሰዎች ብቻ ስለሆነ ወታደሮች ከውጭ ተንጠላጥለው ነበር የተጓዙት።

ባይደን ሽልማቱን ጡረታ ለወጡት ወታደር ሲሰጧቸው “እርዳታ የሚሰጥ ሄሊኮፕተር ወደ እነሱ እየተጓዘ ስላልነበር ወታደሩ ወደ ጦር ሰፈሩ እንዲመለስ ታዞ ነበር። ወታደሩ ግን ‘ጓዶቼን ማዳን አለብኝ። ጓዶቼን ማዳን አለብኝ’ ሲል ነው የመለሰው” ብለዋል።

እያበረሩት የነበረው ኮብራ ሄሊኮፕተር ወታደሮችን ለማዳን የሚውል አይደለም። ከወታደሩ በፊት ይህንን ሄሊኮፕተር ወታደሮችን ለመታደግ የተጠቀመበት ተዋጊም አልነበረም።

ወታደሮቹን ለማዳን ባደረጉት ሙከራ ሄሊኮፕተራቸው በተደጋጋሚ በጥይት ተመቷል።

“ሆኖም ግን ተስፋ አልቆረጠም። ጓዶቹ አሜሪካውያንን ጥሎ ለመሄድ አልፈቀደም። ግዴታውን ለመወጣት ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም” በማለት ባይደን ወታደሩን አሞግሰዋል።

“የአራት ወታደሮችን እና የቤተሰቦቻቸውን የወደፊት እጣ ፈንታ ቀይሯል” ሲሉም አክለዋል።

ከአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ በተለያዩ ጦርነቶች ከተሰለፉ 40 ሚሊዮን ወታደሮች መካከል ከፍተኛ የወታደር ሜዳልያ የተሸለሙት 3,515 ወታደሮች ብቻ ናቸው።

ካፒቴን ላሪ ቴይለር ከእነዚህ መካከል አንዱ ሆነዋል።