ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ወሲባዊ ባርነት እና ግድያዎችን ፈጽመዋል-አምነስቲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ወሲባዊ ባርነት፣ ግድያዎችን እና ሌሎች ከባድ ጥሰቶች መፈጸማቸውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪው አምነስቲ አስታወቀ።
የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ የፈጸሟቸው ጥሰቶች የጦር ወንጀሎች እንዲሁም በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ሊሆን እንደሚችልም ነው አምነስቲ በአዲሱ ሪፖርቱ ያወጣው።
ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት የቋጨውን ስምምነት የፌደራሉ መንግሥት እና ህወሃት ከመፈረማቸው በፊትም እንዲሁም በኋላም በትግራይ ያሉት የኤርትራ ወታደሮች ጥሰቶችን በመፈጸም ለወራት መቀጠላቸው በሪፖርቱ ተካቷል።
አምነስቲ ‘ቱደይ ኦር ቱሞሮው፣ ዘ ይ ሹድ ቢ ብሮውት ቢፎር ጀስቲስ”- በሚል ያወጣው አዲሱ ሪፖርቱ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት አባላት መድፈር፣ሴቶችን ለወራት ለወሲባዊ ባርነት መዳረግ፣ የዘፈቀደ ግድያ፣ ዘረፋዎችን እየፈጸሙም እንደሆነም ተካቷል።
ለነዚህ ጥሰቶች ተጠያቂነት ሊሰፍን እንደሚገባ የጠየቀው አምነስቲ እርስ በርስ በነበረው ጦርነት የተፈጸሙ የጦር ወንጀሎችን እንዲያጣራ በተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመው የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን የስልጣን ቆይታ ሊራዘም እንደሚገባም ጠይቋል።
የስልጣን ቆይታው መስከረም የሚጠናቀቀው ኮሚሽኑ በጦርነቱ በሰላማዊ ዜጎች ላይ መደፈር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የዘፈቀደ ግድያ እና ረሃብ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን የመጀመሪያ ግኝቱ በሆነው ሪፖርቱ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
አምነስቲ ማርያም ሸዊቶ በምትባል ወረዳ ቢያንስ 20 ነዋሪዎች በዋነኝነት ወንዶች ከጥቅምት15- ጥቅምት 22 2015 ዓ.ም ድረስ ባለው ወቅት በኤርትራ መከላከያ ኃይል መገደላቸውን ከዓይን እማኞች፣ ከጥቃቱ ከተረፉ እና የጥቃቱ ሰለባ ከሆኑ ቤተሰቦች መስማቱን አካቷል።
በዚሁ ወረዳ በኤርትራ መከላከያ በዚህ ወቅት የተገደሉ የ100 ነዋሪዎችን ስም የመዘገቡ አንድ የማህበራዊ ጉዳይ ሰራተኛ ዝርዝሩንም አምነስቲ ሰጥተውኛል ቢልም ተቋሙ ተፈጸሙ የተባሉ ግድያዎችን ከርቀት ማረጋጋጥ እንዳልቻለም ጠቅሷል።
የፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ከተፈረመ በኋላም ለሶስት ወራት ያህል የኤርትራ መከላከያ ኃይል ወታደሮች ሴቶችን በመድፈር፣ ለወሲባዊ ባርነት በመዳረግ እንዲሁም 24 ሰላማዊ ነዋሪዎችን በኮኮብ ጽባህ ወረዳም ገድለዋል ተብሏል።
“ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ቢፈረምም በትግራይ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰው ግፍ ቀጥሏል። የኤርትራ ወታደሮች ሴቶችን በመድፈር፣ ለወሲባዊ ባርነት በመዳረግ፣ በደቦ መድፈርን ጨምሮ አሰቃቂ ጥቃቶች ተፈጽሞባቸዋል።ሰላማዊ ወንዶችም በዘፈቀደ ተገድለዋል።” ሲሉም የአምነስቲ የምስራቅ እና የደቡብ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ቲገሬ ቻጉታህ ተናግረዋል።
እነዚህ የጦር ወንጀሎች የተፈጸሙበት ወቅት በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ጦርነት በቆመበት እንዲሁም ሰላማዊ ነዋሪዎችን እንዲሁም የቀድሞ ተዋጊዎችን ለመጠበቅ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ህግ በሰፈነበት ወቅት መሆኑንም ተመልክቷል።
አምነስቲ በሪፖርቱ ውስጥ ያካተታቸው የከፉ ሰብዓዊ የመብት ጥሰቶች የጦር ወንጀሎች እንዲሁም በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ሊሆኑ እንደሚችሉም አመላክቷል።
ከወሲባዊ ጥቃት የተረፉ እንዲሁም የግድያዎቹ የዓይን እማኞች ለተቋሙ እንደተናገሩት ወታደሮቹን በመለዮ ልብሳቸው፣ በሚናገሩት የትግርኛ ቋንቋ ቅላጼ እንዲሁም የሚጠይቁት ጥያቄ የኤርትራ መከላከያ አባላት መሆናቸውን መለየት እንዳስቻላቸው ነው።
ጥሰቶቹ የተፈጸሙባቸው ኮኮብ ጽባህ እና ማርያም ሸዊቶ በኤርትራ ድንበር አቅራቢያ የሚገኙ ሲሆን ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎች የኤርትራ ወታደሮችን በቀላሉ መለየት እንደሚችሉም ተናግረዋል።
መደፈር እና ወሲባዊ ባርነት
አምነስቲ በኮኮብ ጽባህ የተደፈሩ እና ለወሲባዊ ባርነት ተዳርገው የነበሩ 11 ሴቶችን አናግሯል።
ከ40 በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎችም የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ በኋላ እንደተደፈሩ እና ለወሲባዊ ባርነት እንደተዳረጉም ለአካባቢው ለሚገኝ የሲቪል ማህበረሰብ መናገራቸውም ሰፍሯል።
አንዳንዶቹ በኤርትራ መከላከያ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ፣ ሌሎቹ በራሳቸው መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም የኤርትራ ኃይሎች በተቆጣጠሯቸው መኖሪያ ቤቶች ውስጥ መደፈራቸውንም ገልጸዋል።
በኮኮብ ጽባህ የሚገኙ የማህበራዊ ጉዳይ ሰራተኛ፣ የአካባቢው ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች እና ከጥቃቱ የተረፉ ሴቶች ለአምነስቲ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
የኤርትራ ወታደሮች ሴቶቹን ወደ ወታደራዊ ካምፕ የወሰዷቸው የትዳር ጓደኞቻቸው፣ ወንድ ልጆቻቸው፣ ዘመዶቻቸው የትግራይ ኃይል አባላት በሚል ጥርጣሬ እንደሆነ መናገራቸው ተጠቅሷል።
አለም አቀፍ ተቋሙ ከዚህ ቀደም ያጠናቀራቸውን ሪፖርት በመጥቀስም በኮኮብ ጽባህ የተመዘገበው የመድፈር እና ለወሲብ ባርነት መዳረግ በሰላማዊ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ፣ መጠነ ሰፊ እና ስልታዊ ጥቃት አካል ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል ጠቅሶ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊሆን እንደሚችልም ነው ያመላከተው።
በማርያም ሸዊቶ እና በኮኮብ ጽባህ ወረዳዎች የሰፈሩ የኤርትራ ወታደሮች የትግራይ ኃይል አባላትን እና ደጋፊዎችን ለመያዝ በሚልም የቤት ለቤት ፍተሻም በማድረግ ሆን ብለው በሰላማዊ ሰዎች በተለይም ወንዶች ላይ ግድያ መፈጸማቸውም በዚሁ ሪፖርት ተገልጿል።ነው።
አምነስቲ በርካታ ቃለ መጠይቆችን ያደረገ ሲሆን እነዚህም በዘፈቀደ ግድያ የተፈጸመባቸው ሰላማዊ ነዋሪዎችን መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ከግድያው የተረፉ ምስክሮች፣ የዓይን እማኞች እና ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው ግለሰቦች የኤርትራ ወታደሮች ንብረታቸውንና ከብቶቻቸውን መዝረፋቸውን አምነስቲ ነግረውኛል ብሏል።
በርካቶች ለመጠለያ እና ለምግብ አጥተው በቤተሰብ እጅ ላይ ወድቀው ጥገኛ ለመሆን የተገደዱ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ወደ ልመና ገብተዋል ተብሏል።
አምነስቲ የመጀመሪያ የምርመራ ግኝቱን አስመልክቶ ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ መንግሥት ነሐሴ 17/ 2015 ዓ.ም ቢያጋራም ይህ ሪፖርት እስካጠናቀረበት ድረስ ምላሽ አለማግኘቱን አስፍሯል።












