ዩናይትድ ኪንግደም የሩሲያውን ቫግነር አሸባሪ ስትል ልትፈርጅ ነው

የቫግነር ቡድን መለዮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቫግነር የተሰኘው የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን በዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አሸባሪ ተበሎ ሊፈረጅ ነው።

ይህ ማለት የቡድኑ አባል መሆን አሊያም ለቡድኑ ድጋፍ ማድረግ በዩኬ በሕግ ያስቀጣል።

ለፓርላማ የቀረበው ረቂቅ እንደሚጠቁመው የቡድን ንብረቶች የሽብርተኛ ቡድን ተብለው ይወረሳሉ።

የዩኬ ሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እንዳሉት ቫግነር “አመፀኛ እና አጥፊ. . .የቭላድሚ ፑቲን ወታደራዊ መገልገያ ነው።”

ሚኒስትሯ ሱዌላ ብሬቭማን አክለው ቫግነር በዩክሬን እና በአህጉረ አፍሪካ የሚፈፅመው ድርጊት “ለዓለም አቀፍ ደኅንነት ስጋት ነው።”

“የቫግነር ቡድን አጥፊ ተግባራት ዋነኛ ጥቅሙ የክሬምሊንን ፖለቲካዊ አጀንዳ ከግብ ማድረስ ብቻ ነው። በቀላል እና አጭር ቋንቋ ሽብርተኛ ነው። አዲሱ የዩኬ ሕግ ይህንን በግልፅ ያስቀምጣል” ብለዋል።

ቫግነር የተባለው ቅጥረኛ ቡድን ሩሲያ ዩክሬንን ስትወር ትልቅ ሚና ተጫውቷል። አልፎም በሶሪያ እና እንደ ሊቢያና ማሊ ባሉ የአፍሪካ ሃገራትም ተሰማርቷል።

የቡድኑ አባላት በዩክሬን ዜጎችን በመግደልና በማሰቃየት እንዲሁም በሌሎች በርካታ ወንጀሎች ይጠረጠራሉ።

በአውሮፓውያኑ 2020 ዩናይትድ ስቴትስ የቫግነር ወታደሮች በሊቢያ ዋና ከተማ ትሪፖሊ ፈንጅ ቀብረዋል ብላ ነበር።

ባለፈው ሐምሌ ደግሞ ዩኬ ቡድኑ “በማሊ እና በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ግድያና ማሰቃየት ፈፅሟል” ስትል ወቀሳ ማሰማቷ ይታወሳል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቡድን መሪ የቭገኒ ፕሪጎዢን በሩሲያ ከጥቂት ወራት በፊት በአጭሩ የተቀጨ ወታደራዊ አመፅ አንስተው ከከሸፈ በኋላ የቫግነር ዕጣ ፈንታ አጠራጣሪ ሆኖ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2014 ቡድን የመሠረቱት ፕሪጎዢን ባለፈው ወር ከሌሎች የቫግነር ኃላፊዎች ጋር በአውሮፕላኑ እየበረሩ ሳለ ተከስክሰው መሞታቸው ተዘግቧል።

ፕሪጎዢን በሩሲያዋ ሴይንት ፒተርስበርግ ቀብራቸው ተፈፅሟል።

የቫግነር ስም እንደ ቦኮ ሐራም እና ሐማስ ካሉ ድርጅቶች እኩል በዩኬ አሸባሪ የሚል መጠሪያ ይሰጠዋል።

የሽብርተኝነት ድርጊት 2000 የተሰኘው የዩኬ ማዕቀፍ የሃገር ውስጥ ሚኒስትር አንድን ድርጅት ሽብርተኛ ብለው እንዲፈርጁ ሥልጣን የሚሰጥ ነው።

ሽብርተኛ የተባለ ቡድን መርዳት አሊያም ከቡድኑ ጋር አብሮ መሥራት፣ ግንኙነት ማድረግና የቡድን ድርጊት እንዲቀጥል ማበረታታት፤ የቡድን ባንዲራም ሆነ ምልክት ማሳየት በሕግ የሚያስቀጣ ይሆናል።

ይህ ሕግ ተላልፈው የተገኙ ግለሰቦች እስከ 14 ዓመት የሚያደርስ እሥራት ወይም 5000 ፓውንድ ይቀጣሉ።

የዩኬ መንግሥት ቡድኑን አሸባሪ እንዲለው ከፓርላማ አባላት ግፊት ይደርስበት የጀመረው ከወራት በፊት ነው።

የሌበር ፓርቲ ትይዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ ቡድኑ “ዩክሬን ውስጥ በፈፀመው ድርጊት አሸባሪ ሊባል ይገባል” ሲሉ ይከራከሩ ነበር።

መንግሥት ቡድኑን አሸባሪ ለማለት መወሰኑን ተከትሎ ላሚ “እንደውም ውሳኔው ዘግይቷል፤ ነገር ግን መንግሥት በስተመጨረሻ ይህን ማድረጉ መልካም ነው” ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ቢሮ የቡድኑ መሪ የነበረው ፕሪጎዢንና የሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ንብረት ከእንቅስቃሴ እንዲታገድ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የቫግነር ቡድን ባለፈው ሰኔ ከፈፀመው ወታደራዊ አመፅ በኋላ አልፎም የቡድኑ መሪ የአውሮፕላን አደጋ ነው በተባለ ክስተት ከሞቱ በኋላ መዳከሙ ይነገራል።

ቢሆንም ቡድኑ አሸባሪ መባሉ አባላቱ በነፃነት ገንዘብ እንዳያዘዋውሩ አልፎም ዩከሬንና ሌሎች ቫግነርን ከሰው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በዩኬ ፍርድ ቤቶች እንዲያገኙ ያስችላል የሚል እምነት አለ።