ሞስኮ የየቭጌኒ ፕሪጎዢንን ሞት ከምርመራ በኋላ አረጋገጥኩ አለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቫግነር የተባለው የቅጠረኛ ተዋጊ ቡድን መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን በአውሮፕላን አደጋ ሕይወቱ ማለፉ በዘረመል ምርመራ መረጋገጡን ሩሲያ አስታወቀች።
ከጥቂት ቀናት በፊት የቭጌኒ ፕሪጎዢን ተሳፍሮበታል የተባለው አውሮፕላን ከሞስኮ ወደ ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ እየበረረ ሳለ መከስከሱ መዘገቡ ይታወሳል።
የአውሮፕላኑን መከስከስ በተመለከተ ምርመራ ሲያደርግ የነበረ መርማሪ ኮሚቴ የአስር ሰዎችን አስክሬን መሰብሰቡን እና በበረራ ወቅት ከተመዘገበ የተሳፋሪዎች ማንነት ዝርዝር ጋር ማመሳከሩን አስታውቋል።
ሩሲያ በአውሮፕላኑ ከተሳፈሩት 10 ሰዎች መካከል ፕሪጎዢን አንዱ መሆኑን እንዲሁም መንገደኞቹ በሙሉ በአደጋው ሕይወታቸው ማለፉን ትግለጽ እንጂ ለቅጠረኛ ቡድኑ መሪ ሞት እስካሁን ቀጥተኛ ማረጋገጫ ሳትሰጥ ቆይታለች።
አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የቫግነሩ አለቃ የቭጌኒ ፕሪጎዢን በተከሰከሰው አውሮፕላን ላይ ተሳፍሮ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ባይኖርም፣ የመሞቱ ዜና ግን እውነት ሳይሆን አቀይቀርም ሲሉ ነበር።
የቭጌኒ ፕሪጎዢን ተሳፍሮበት የነበረው ኤምባሪዬር አውሮፕላን ተከስክሶ ሕይወቱ ሳያልፍ አይቀርም መባሉን ተከትሎ በርካቶች ለአውሮፕላኑ መከስከስ ምክንያት ነው ያሉትን መላምት ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።
ከእነዚህ መካከል አውሮፕላኑ የተከሰከሰው ከምድር ወደ ሰማይ በሚወነጨፍ ሚሳኤል ከተመታ በኋላ ነው የሚለው ትልቁን ቦታ ይይዛል።
ለቅጥረኛ ቡድኑ ቅርበት ያለው የቴሌግራም ገጽ አውሮፕላኑ ሞስኮ ባሉ ‘ከሃዲዎች’ ከምድር ወደ ሰማይ በሚወነጨፍ ሚሳኤል ተመትቶ ወድቋል ብሎ ነበር።
ይሁን እንጂ አሜሪካ አውሮፕላኑ በሚሳኤል ተመትቶ ወድቋል የሚለው ትንተና እውነት የመሆን ዕድሉ ጠባብ ነው ብላ ነበር።
አንድ በስም ያልተጠቀሱ የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን በተመሳሳይ ለሲቢኤስ ቴሌቪዥን ሲናገሩ፣ አውሮፕላኑ በሚሳኤል ተመትቶ ሳይሆን የተከሰከሰው ምናልባት አውሮፕላኑ ላይ የነበረ ቦምብ ከፈነዳ በኋላ ነው በደረሰ አደጋ ነው ብለዋል።
የሩሲያ ባለሥልጣናት በፑቲን አስተዳደር ላይ ለአንድ ቀን ብቻ የቆየ አመጽ ቀስቅሶ የነበረው የቭጌኒ ፕሪጎዢን እንዲገደል ትዕዛዝ ሰጥተዋል መባሉን የክሬምሊን ቃል አቀባይ ውድቅ አድርገውት ነበር።
የፑቲን ቃለ አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ክሬምሊን ፕሪጎዢን እንዲገደል ትዕዛዝ ሰጥቷል መባሉ “ፍጹም ሐሰት ነው” ብለው ነበር።
ቃለ አቀባዩ በአውሮፕላኑ ላይ ስለደረሰው አደጋ እንዲሁም ተሳፍረው ስለነበሩት ግለሰቦች “አሳዛኝ ሞት በርካታ መላ ምቶች እየተሰነዘሩ ነው” ብለዋል።
“በእርግጥ ከምዕራቡ ዓለም የሚመጣው ይህ መላ ምት ከተወሰነ አቅጣጫ ነው። ሁሉም ፍጹም ሐሰት ነው። በእርግጥ ስለ አደጋው ስንነጋገር በመረጃዎች እና በእውነታዎች ብቻ ልንመራ ይገባል” ብለዋል።
በአንድ ወቅት የቭላድሚር ፑቲን ጠንካራ አጋር የነበረው ፕሪጎዢን በፕሬዝዳንቱ አስተዳደር ላይ የቀሰቀሰው አመጽ ከከሸፈ በኋላ በፑቲን ቂም ተይዞበት ግለሰቡ በሞት ጥላ ስር ነው ሲባል ቆይቷል።












