የወር አበባ ናሙናን በመመርመር ለሴቶች ጤና እና ሕክምና ጠቃሚ መረጃ ሊገኝ ይችላል ተባለ

የደም ናሙና

የፎቶው ባለመብት, QVIN

በዓለም ዙሪያ በእያንዳንዱ ቀን ወደ 800 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች የወር አበባ ያያሉ።

ቁጥሩ በዚህ መልኩ ከፍ ያለ ይሁን እንጂ የወር አበባ ደምን በተመለከተ እምብዛም የተጠና ዝርዝር ነገር የለም። ካለም ብዙም አይታወቅም።

በጤና ጉዳይ ላይ የሚሠራ የራሷን ተቋም የመሠረተችው ዶክተር ሳራ ናስሪ ይህንን እውነታ ለመቀየር እየሠራች ነው።

ሆኖም በጉዳዩ ላይ በቂ ጥናት አለመኖሩ ይህን ተግባር ሰፊ ጊዜ እንዲወስድ ያደርገዋል ተብሎ ይታመናል።

አሁንም በጥናት ላይ ያለችው ዶክተር ናስሪ በወር አበባ ደም ላይ የተደረገ አንድ ጥናት ብቻ ነው ያገኘችው። እንደ አውሮፓውያኑ በ2012 የተደረገው ይህ ጥናት የወር አበባ ደምን አወቃቀር እና ይዘትን የተመለከተ ሲሆን፣ የወር አበባ ደም ውስጥ ብቻ የሚገኙ 385 ንጥረ ነገሮች እንዳሉ በግኝቱ አረጋግጧል።

ይኸው ጥናት ሌሎች ግኝቶችን ያመላከተ ነው።

“ደም የህክምና ውሳኔውችን ለመወሰን በቋሚነት ጥቅም ላይ የሚውል የሰውነት ፈሳሽ ነው” የምትለው ዶክተር ናስሪ፣ “‘ሴቶች በእያንዳንዱ ወር ደም ይፈሳቸዋል። ይህንን ለምንድን ነው ለህክምና ዓላማ የማንጠቀመው?’ እያልኩ አስብ ነበር” ስትል ታስረዳለች።

ታዲያ ዶክተር ነስሪያ ያቋቋመችው ድርጅት በጉዳዩ ዙሪያ ያለውን የምርምር ክፍተት ለመሙላት ይሠራል። በርካታ ተማሪዎችን በጥናት ውስጥ በማካተት ከደም ስር ወይም ከጣት የሚወሰድ ደም እና በወር አበባ ደም መካከል ያለው ግንኙነት ማጥናት ዋነኛ ዓላማው ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የመነሻ ጥናቱ ተስፋ የሚጣልበት ቢሆንም ተጨማሪ ምርምሮችን ግን ይፈልጋል።

እነዚህ ጥናቶች ውጤት የሚያስገኙ ከሆነ ለተለመዱ የጤና እክሎች ምርመራ ወይም ክትትል የወር አበባ ደም ናሙን መውስድ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

ለምሳሌ የስኳር ህመም ወይም የኮሌስትሮል ችግር ያለባቸው ሴቶች በየወሩ ለሚያደርጉት ምርመራ የወር አበባ ናሙና ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል ማለት ነው።

ይህ ጥረት እየተፈተነ ያለው በቂ ጥናት ባለማግኘት ብቻ ሳይሆን፣ የወር አበባ የደም ናሙናን ለመመርመር ቤተ ሙከራዎች ከማቅማማታቸው ባለፈ የሰዎች አመለካከት ፈታና ሆኗል።

በርሊን የሚገኝ ተቋም የወር አበባ ደም ናሙናዎችን ሊመረምር የሚችል ቤተ ሙከራ በማፈላለግ ላይ ይገኛል።

በምርምሩ አስተማማኝ መረጃዎችን ምገኘት ከተቻለ፣ የወር አበባ ደምን በመጠቀም በስፋት የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን ለመከታተል እና ለመመርመር ከፍ ያለ ጠቀሜታ ይኖራዋል።

በተጨማሪ ደግሞ በሴቶች ዘንድ የሚያጋጥሙ የተዋልዶ ጤና አካላት የጤና ችግሮችን በቀላል እና በአመቺ ሁኔታ ለመመርመር ያስችላል።

በአሁኑ ጊዜ ያሉት ዝቅተኛ የሴቶች የተዋልዶ ጤና ችግሮችን የተመለከቱ ጥናቶች የምርመራ ሂደትን አዝጋሚ እና ያሉ የሕክምና አራጮችም ውስን ናቸው። በተጨማሪም በህሙማን ላይ የሚደረገው ምርመራ ህመም እና ስቃይ ያለው ነው።

ይህ በዶክተር ሳራ ናስሪ የተጀመረው ጥረት ፈታኝ ሁኔታዎች የሚገጥሙት ቢሆንም፣ ስኬታማ መሆን ከቻለ ሴቶች በሕይወት ሂደታቸው ውስጥ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ቀላል እና ከባድ የጤና እክሎችን በወር አበባቸው አማካይነት ለመለየት እና ሕክማና ለማግኘት ዕድል ይፈጥርላቸዋል።

በተለይ ደግሞ ሰቶች በተዋልዶ ሥርዓታቸው ላይ የሚያጋጥሙ ከባድ የጤና እክሎችን የወር አበባን መሠረት ባመድረግ በመደበኝነት በቀላሉ ለመከታተል ያስችላቸዋል።

ይህም ከባድ የሚባሉ የጤና ችግሮችን ለመከላከል፣ በጊዜ ለማወቅ እንዲሁም አስፈላጊውን ሕክምና ሴቶች እንዲያገኙ በማድረግ የበርካቶችን ስቃይና ሞትን ሊያቀል ይችላል ተብሎ ይታመናል።