አሜሪካ ከወሊድ በኋላ የሚመጣን ድባቴ ለማከም የሚወሰድ ክኒን አፀደቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ እናቶች ከወለዱ በኋላ የሚያጋጥማቸውን ድባቴ ለማከም የሚወሰድ የመጀመሪያውን ክኒን ገበያ ላይ እንዲውል አፀደቀች።
የአገሪቱ የምግብ እና መድሃኒት አስተዳዳሪ (ኤፍዲኤ) ዙራኖሎን የተባለው ክኒን ከወሊድ በኋላ ለሁለት ሳምንታት በቀን አንድ ግዜ እንዲወሰድ ፍቃድ ሰጥቷል።
ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው እናቶች ከወሊድ በኋላ ለከፍተኛ ድባቴ ይጋለጣሉ። በአሜሪካ የተካሄደ አንድ ጥናት ከሰባት እናቶች አንዷ ከወሊድ በኋላ ድብርት ውስጥ ትገባለች ይላል።
ከወሊድ በኋላ ድባቴ የሚያጋጥማቸው ሴቶች ከሚታዩባቸው ምልክቶች መካክለ ጥልቅ የሐዘን ስሜት ውስጥ መግባት፣ አቅም ማጣት፣ እራስን የማጥፋት ሃሳብ መጠናወት፣ የደስታ ስሜትን ለማግኘት መቸገር እንዲሁም አዲስ ነገር ለማወቅ፣ ለማሰላስ ወይም ለማስታወስ መቸገር ናቸው።
ከዚህ ቀደም ከወሊድ በኋላ የሚያጋጥም ድባቴ መድሃኒት የሚሰጠው በመርፌ አማካይነት ብቻ ነበር።
አዲሱ ክኒን የተተመነለት ዋጋ እስካሁን ይፋ ባይደረግም በጥቂት ወራት ውስጥ ግን ለገበያ ይቀርባል ተብሏል።
በኤፍዲኤ የሥነ አእምሮ ሕክምና ክፍል ኃላፊ የሆኑት ቲፋኒ ፍራቺዮኒ ከወሊድ በኋላ የሚከሰተው ድባቴ ለሕይወት አስጊ የሆነ የጤና መቃወስ ነው ይላሉ።
“ድህረ ወሊድ ድባቴ ሴቶች ሐዘን ውስጥ እንዲገቤ፣ የተጠያቂነት እና የዋጋ ቢስነት ስሜት ይሰማቸዋል። ባስ ሲል ደግሞ እራሳቸውን ወይም ጨቅላ ልጃቸውን ስለመጉዳት ያስባሉ። ይህ አደገኛ እና ለሕይወት አስጊ ነው” ይላሉ ቲፋኒ ፍራቺኦን።
ከወሊድ በኋላ የሚያጋጥመው ድባቴ በልጅ እና በእናት መካከል ያለን ቁርኝነት ከማጥፋቱ በተጨማሪ አዲስ በተወለደው ልጅ አካላዊ እና ሥነ-ልቦናዊ እድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል ይላሉ ባለሙያዋ።
አሁን ላይ ይህ ክኒን አማራጭ መድሃኒት ሆኖ መቅረቡ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እያለፉ ላሉ እናቶች ጠቃሚ ነው ብለዋል ቲፋኒ ፍራቺኦን።
ኤፍዲኤ በክኒኑ ላይ የተደረጉ ሙከራዎች መድሃኒቱ ለተከታታይ ሦስት ቀናት ከተወሰደ የድባቴ ምልክቶችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ እና ለአራት ሳምንታትም የሕመሙ ምልክቶችን እንደሚያስቀር ተመልክተናል ብሏል።
ይህ ክኒን ታዲያ በአንዳንድ ሴቶች ላይ ተቅማጥ፣ ድካም፣ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን እና መፍዘዝ የመሳሰሉ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪ እናቶች መደሃኒቱን በወሰዱ በ12 ሰዓታት ውስጥ መኪና ከማሽከርከር እና ከባድ ማሽናሪዎችን ከማንቀሳቀስ ሊቆጠቡ ይገባል ይላሉ ባለሙያዎች።
ይህን መድሃኒት የማረቱት ሴግ ቴራፒዩቲክስ እና ባዮጂን ይህ ዙራኖሎን የተባለ ክኒን ከፍተኛ የሆነ የአእምሮ ጭንቀት ውስጥ ለገቡ ሰዎች ጭምር በሃኪም እንዲታዘዝ የአሜሪካውን የምግብ እና መድሃኒት ተቆጣጠሪ ባለስልጣናን ጠይቀዋል።
ኤፍዲኤ ግን ዙራኖሎን ከባድ ድባቴ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ለማከም ፍቱን ስለመሆኑ እስካሁን በቂ ማረጋገጫ ስላልተገኘ ተጨማሪ ጥናት መድረግ አለበት ሲል ጥያቄውን ውድቅ አድርጓል።












