ሳይንቲስቶች በአጋጣሚ ያገኙት ባክቴሪያ ወባን ለመከላከል የሚያግዝ ሆኖ ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሳይንቲስቶች በተፈጥሮ ሂደት የሚፈጠር ባክቴሪያ የወባ በሽታ ከትንኝ ወደ ሰው እንዳይተላለፍ ማድረግ እንደሚችል ባላሰቡት አጋጣሚ ደረሱበት።
ተመራማሪዎች በአንድ ቤተ-ሙከራ ውስጥ የሰበሰቧቸው የወባ አስተላላፊ ትንኞች የወባ ጥገኛ ሕዋስ ሳይገኝባቸው ሲቀር ነው ይህ የታወቀው።
አጥኚዎቹ እንደሚሉት ድንገት የተገኘው ባክቴሪያ በዓለማችን ገዳይ ከሚባሉት በሽታዎች አንዱ ለሆነው ወባ መፍትሔ ይዞ ሊመጣ ይችላል።
በዓለም በየዓመቱ ከ600 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ ይሞታሉ።
አሁን ሳይንቲስቶች ይህን ባክቴሪያ ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ጥቅም ላይ ለማዋል ምርመራ እያከናወኑ ነው።
ጂኤስኬ የተባለው የመድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁሶች አምራች ኩባንያ፣ ስፔን በሚገኘው የጥናት ማዕከሉ ነው ይህን መላ ያገኘው።
አጥኚዎቹ መድኃኒት ለማግኘት ለሚደረግ ምርመራ የሚጠቀሙባቸው ወባ አስተላላፊ ትንኞች ወባ መሸከም ማቆማቸውን ሲመለከቱ ነው አዲስ ግኝት ላይ እንደደረሱ የገባቸው።
“የወባ ትንኞቹ የሚያስተላለፉት ተሕዋስ እየቀነሰ መጣ። በዓመቱ መጨረሻ የወባ ትንኞቹ ወባ መሸከም ማቆም ጀመሩ” ይላሉ የጥናቱ መሪ ዶክተር ጃኔት ሮድሪጉዌዝ።
የጥናት ቡድኑ 2014 በሠራው ምርምር ወቅት የደረሱበትን ግኝት ማቀዝቀዣ ውስጥ አስቀምጠው ከሀለት ዓመት በኋላ ምን እንደተፈጠረ ለማወቅተ ተመልሰው መጡ።
ከዚያ በኋላ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ቲሲ1 የተባለው የባክቴሪያ ዓይነት ብዙውን ጊዜ በተፈጥሯዊ ከባቢ ውስጥ የሚገኝ ነው።
ይህ ባክቴሪያ ትንኞቹ ለወትሮው በውስጣቸው ተሸክመው የሚዞሩትን የወባ ተሕዋስ ዕድገት ማቆም ችሏል።
ዶክተር ሮድሪጉዌዝ እንደሚሉት “ባክቴሪያው የወባ ትንኞችን ተሕዋስ ማሳደግ እንዳይችሉ አንድ ጊዜ ካደረገ በኋላ መልሰው መሸከም አይችሉም።”
“ግኝቱ ባክቴሪያው የወባ ትንኞች ጥገኛው ተሕዋስ እንዳይተላከለፍ ማድረግ እንደሚችል ነው።”
ሳይንስ ጋዜጣ ያሳተመው አዲስ መረጃ እንደሚያሳየው ባክቴሪያው ትንኞቹ መሸከም የሚችሉትን ጥገኛ ተሕዋስ አቅም 73 በመቶ ቀንሶታል።
የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ከጂኤስኬ ሳይንቲስቶች ጋር በመጣመር፤ ሃርሜን የሚባለውን ሞሌኪዩል ለትንኞች መስጠት እንደሚቻል ደርሰውበታል።
ይህ ማለት የወባ ትንኞች በሚበዙበት ሥፍራ መሰል ባክቴሪያዎችን በማድረግ በሽታውን መከላከል ይቻላል።
ሞስኪውቶስፊር የሚባል የጤና ማዕከል ቡርኪና ፋሶ ውስጥ ተከፍቶ ተጨማሪ ምርመራ እየተካሄደ ሲሆን፣ ይህም ሃርሜን የተሰኘውን ሞሌኪዩል እንዴት ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል የሚለውን ለመፈተሽ ነው።
የምርመራው ዓላማ ይህን ፀረ-ወባ የሆነ ባክቴሪያ ነክ የሆነ ምርትን በማዘጋጀት ከዓለማችን ጥንታዊ በሽታዎች አንዱ የሆነውን ወባ መታገል ነው።
በየዓመቱ 62 ሺህ ሰዎችን የሚቀጥፈው የወባ በሽታ በተለይ ደግሞ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን ያጠቃል።
በአሁኑ ወቅት ለወባ በሽታ መከላከያ የሚሆን ክትባት የተመረተ ሲሆን፣ ነገር ግን በአህጉረ አፍሪካ ገና መከፋፈል አልጀመረም።
ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ብቻ በየዓመቱ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 260 ሺህ ሕፃናትን ለሚገድለው የወባ በሽታ ክትባት መገኘቱ ሕይወት እንደሚታደግ የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።
ክትባቱ ውጤታማ መሆኑ የተረጋገጠው ከስምንት ዓመታት በፊት ነው። እስከ 40 በመቶ የሚደርሰውን የበሽታውን ቁጥር የሚቀንስ ሲሆን፣ 30 በመቶ ደግሞ አስጊ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ይታደጋል ተብሏል።
በፈረንጆቹ ከ2019 ጀምሮ ተመራማሪዎች የክትባት ፕሮግራሙን በጋና፣ በኬንያ እና በማላዊ ውስጥ ሲያከናውኑ እንደነበረ ተገልጧል።
እስካሁን በተገኙ የምርምሩ ውጤቶች መሠረትም ክትባቱ ከ10 በወባ በሽታ ከሚያዙ ሰዎች መካከል አራቱን መከላከል ይችላል።
ይህ ክትባት በጋና፣ በኬንያ እና በማላዊ የሙከራ ክትባት መርሃ ግብሮች ተደርጎ ስኬታማነቱ መረጋገጡን ተከትሎ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ክትባቱ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ የወባ ሥርጭት ባለባቸው ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት እና በሌሎች አካባቢዎች መጀመር አለበት ብሏል።












