በኬንያ ዋነኛ አየር ማረፊያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦ መንገደኞች በመጉላላታቸው ኃላፊዎች ተባረሩ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በኬንያ ዋነኛው አየር ማረፊያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦ መንገደኞች በጨለማ በመንገላታታቸው ምክንያት የኬንያ ኤርፖርቶች ባለስልጣን ኃላፊ ተባረሩ።
በዋና መዲናዋ ናይሮቢ የሚገኘው ጆሞ ኬንያታ አየር ማረፊያ ለሰዓታት ያለመብራት ቆይቷል።
የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ኪፕቹምባ ሙርኮሜን የኬንያ ኤርፖርቶች ባለስልጣን ኃላፊ የሆኑት አሌክስ ጊታሪን ከሥራ አሰናብተዋል።
በአየር ማረፊያው የኤሌክትሪክ ኃይል የተቋረጠው ከአርብ ምሽት እስከ ቅዳሜ ረፋድ በመላ አገሪቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከተቋረጠ በኋላ ነው።
በመላ ሃገሪቱ ለተከሰተው የመብራት መቋረጥ ምክንያቱ ምን እንደሆነ አብላጫው ድርሻው በመንግሥት የተያዘው ኮርፖሬሽን ይፋ አላደረገም።
አርብ ዕለት በተከሰተው የመብራት መቋረጥ ምክንያት በርካታ ሰፈሮች ጨለማ ሲያድሩ የንግድ ሱቆችም በክስተቱ መጎዳታቸውን ገልጠዋል።
10 በመቶ የሚሆነውን የኬንያ ጠቅላላ የሃገር ውስጥ ምርት የሚሸፍነው ቱሪዝም ነው። የምስራቅ አፍሪካዋ ሃገር የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝም ያግዛታል።
ኬንያዊያን ዋናው የሃገሪቱ አየር ማረፊያ ለመሰል ጊዜ የሚሆን ጄኔሬቴር እንዴት የለውም ሲሉ ቁጣቸውን በማሕበራዊ ሚድያዎች ገልጠዋል።
ከኤርፖርቶች ባለስልጣን ኃላፊ በተጨማሪ አንድ ከፍተኛ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንም ከመንበራቸውን ተነስተዋል።
የናይሮቢ ጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ደግሞ ከመንበራቸው ተቀንሰው ወደ ሞምባሳ አየር ማረፊያ እንዲሄዱ ተደርገዋል።
በመብራት መቋረጥ ምክንያት ዲጂታል የመክፈያ ሥርዓቶች በመቆራረጣቸው ወደ ብሔራዊ ፓርክ ጎብኝዎች መግባት ሳይችሉ ቀርተዋል።
ምንም እንኳ መብራት መቋረጥ በኬንያ ያልተለመደ ነገር ባይሆንም የሃገሪቱ አየር ማረፊያ፣ ሆስፒታሎችና ቤተ-መንግሥቱ በጨለማ እስኪዋጡ ድረስ የሚቆይ መቋረጥ መታየቱ አዲስ ነገር ነው።
በርካታ ኬንያዊያን መብራቱ መቋረጡን ተከትሎ የሃገሪቱ መብራት ኃይል ሙሰኛ ነው ሲሉ ወቀሳቸውን አሰምተዋል።
የትራንስፖርት ሚኒስትሩ እንደገለጡት ለአየር መንገዱ ተብለው ከሁለት ዓመት በፊት የተገዙ ሁለት ጄኔሬተሮች እስካሁን ሥራ አልጀመሩም።
ጄኔሬተሮቹ በምን ያክል ዋጋ እንደተገዙ እና እስካሁን ለምን ሥራ እንዳልጀመሩ የሚታወቅ ነገር የለም።












