በተከሰከሰው አውሮፕላን ውስጥ የነበረው የፕሪጎዢን ቀኝ እጅ ዲሚትሪ እና ሌሎቹ ተሳፋሪዎች እነማን ናቸው?

የፕሪጎዥን ቀኝ እጅ የነበረው እና በተከሰከው አውሮፕላን ተሳፍሮ የነበረው ዲሚትሪ

የፎቶው ባለመብት, Social Media

የምስሉ መግለጫ, የፕሪጎዥን ቀኝ እጅ የነበረው እና በተከሰከው አውሮፕላን ተሳፍሮ የነበረው ዲሚትሪ

የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን (ቫግነር) የቭጌኒ ፕሪጎዢንን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች በተከሰከው አውሮፕላን ውስጥ ተሳፋሪዎች እንደነበሩ የሩሲያ አቪዬሽን ባለሥልጣናት ያወጡት መረጃ ያስረዳል።

የተዋጊ ቡድኑን ቫግነር በሚል እንደሰየመው የሚታመነው እና የፕሪጎዢን ቀኝ እጅ የነበረው ዲሚትሪ ኡትኪንም ከተሳፋሪዎቹ መካከከል አንዱ ነበር ተብሏል።

በተጨማሪም ለተዋጊ ቡድኑ የገንዘብ ምንጭ ወሳኝ ሰው ነበር የሚባለው ቫለሪ ቼካሎቭ በተከሰከሰው አውሮፕላን ውስጥ ነበሩ ብላለች ሩሲያ።

ከቫግነር አባላት በተጨማሪ ሦስት የበረራ ሠራተኞችም በዚህ የአውሮፕላን አደጋ ምክንያት መሞታቸው ተነግሯል።

ሌሎች ተሳፋሪዎች እነማን ናቸው?

ዲሚትሪ ኡትኪን

ቫግነር አመሠራረትም ሆነ ታሪኩ ምስጢራዊ ነው።

ነገር ግን ዱካውን ለተከተለ የዲሚትሪ ኡትኪንን ስም ማግኘቱ አይቀርም።

የ53 ዓመቱ ዲሚትሪ፣ ሩሲያ ካካሄደቻቸው ጦርነቶች ጋር ተያይዞ ስሙ ይነሳል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአውሮፓውያኑ ከ1994 አስከ 2000 ድረስ ሩሲያ በቺቺኒያ ውስጥ ባካሄደቻቸው ጦርነቶችም የውጊያ አርበኛ ተብሏል።

ቅጥረኛው ተዋጊ ኩባንያ ቫግነር ከተመሠረተበት ከ2014 (እአአ) ጀምሮ ዲሚትሪ ነበር።

ቡድኑንም ቫግነር ሲል የሰየመው እሱ እንደሆነ ይታመናል።

ቫግነር የተሰየመው የአዶልፍ ሂትለር ተወዳጅ የሙዚቃ አቀናባሪ የሆነውን ሪቻርድ ቫግነርን በማስታወስ ነው።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ የፕሪጎዢን የቀኝ እጅ እንደነበረ የሚነገረው ዲሚትሪ በአጠቃላይ ለቡድኑ ትዕዛዝን በመስጠት እንዲሁም የወታደራዊ ሥልጠና ኃላፊነትም የእርሱ ነበር ተብሏል።

ዲሚትሪ ብዙ ፎቶ የለውም። ነገር ግን ከተገኙት መካከል አንዱ ፎቶ የኒዮ ናዚ ንቅሳት በሰውነቱ ላይ እንዳለው ያሳያል።

ዲሚትሪ የሥራ ልምዱን አስመልክቶ በኢንተርኔት ላይ ከለጠፈው የልምድ መዘርዝር (ሲቪ) እንዲሁም ቤሊንግካት የተሰኘው የምርመራ ድረገጽ ባደረገው ማጣራት ፎቶውን ያጋራው በ2013 (እአአ) ነው።

በዚህም መሠረት ዲሚትሪ ከ1988 እስከ 2008 (እአአ) በሩሲያ የወታደራዊ መረጃ ክፍል ውስጥ አገልግሏል።

በውጊያዎች ውስጥ በነበረው ድንቅ ተሳትፎ የመንግሥት ሽልማቶችን እንዳገኘም ያስረዳል። ዲሚትሪ በዚህም መረጃው የጦር መሳሪያዎችን መተኮስ መቻሉ እንደ ችሎታ አስቀምጧል።

ዲሚትሪ የወታደራዊ መረጃ ክፍልን ከለቀቀ በኋላ ተፈላጊ ሰው ሆነ። በምሥራቃዊ ዩክሬን የሩሲያ ደጋፊ የሆኑ ተገንጣዮች ከቫግነር ጋር በመሆን በ2014 (እአአ) አብሮ ተዋግቷል።

ቫግነር በሶሪያ እና በአፍሪካ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይም ዲሚትሪ ተሳታፊ ነበር። ከሁለት ዓመት በፊት ቢቢሲ ቫግነር በሩሲያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ባጋለጠበት የምርመራ ዘገባው የዲሚትሪ ስም ተነስቷል።

ሩሲያ ከቫግነር ጋር ምንም ግንኙነት የለኝም በምትልበት በ2016 (እአአ) ዲሚትሪ ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በክሬምሊን በነበረ ዝግጅት ላይ በአንድ ፎቶ ታይቷል። ከዚያን ጊዜ በኋላ ፕሬዝዳንት ፑቲን መንግሥታቸው ቡድኑን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በመመደብ መደገፉን ተናግረዋል።

ቫለሪ ቼካሎቭ

ቼካሎቭ ከቫግነር መሪ ፕሪጎዢን ጋር ለሁለት አስርት ዓመታት የቆየ ቅርብ የሆነ የንግድ ትስስር እንደነበረው ይታመናል።

የ47 ዓመቱ ቼካሎቭ የፕሪጎዢን ወታደራዊ ያልሆኑ ንግዶች ላይ ተሳትፎ ያለው ሲሆን፣ ይህም ገንዘብ ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድኑን ለመደገፍ ጥቅም ላይ እንደሚውል ምዕራባውያኑ ይናገራሉ።

ቼካሎቭ ከፕሪጎዢን ጋር ግንኙነት ካለው እና ከጥቂት ዓመታት በፊት በሶሪያ ውስጥ ጋዝ እና ዘይት ለማምረት ውል ከተፈራረመው ኤቭሮ ፖሊስ ኩባንያ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው።

በአሜሪካ ግምጃ ቤት መረጃ መሠረት ይህ ኩባንያ ከሶሪያው ፕሬዝዳንት በሻር አል አሳድ መንግሥት ጋር ውል የተፈራረመው “የሶሪያን የነዳጅ ቦታዎችን ለመጠበቅ እና ከሚገኘው የነዳጅ እና የጋዝ ምርት 25 በመቶ ድርሻ ለማግኘት” ነው።

ከስምምነቱ የተገኘው ገንዘብ ለቫግነር ተዋጊዎች ክፍያ እና የጦር መሳሪያ ግዥ ጥቅም ላይ መዋሉንም የአሜሪካ ግምጃ ቤት አስታውቋል።

ቼካሎቭ በመላው አፍሪካ ቫግነር የነበረውን የንግድ ፕሮጀክቶችንም ሲመራ እንደነበር ይታመናል።

ግለሰቡ ከፕሪጎዢን ጋር ባለው ግንኙነት በአሜሪካ እና በዩክሬን ማዕቀቦች ተጥሎበታል።

በተጨማሪም ኢቭሮ ፖሊስ፣ ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በበርካታ መንግሥታት ማዕቀብ ጥሎበታል።

አራቱ የቫግነር አባላት?

የቭጌኒ ማካርያን፣ ሰርጌይ ፕሮፑስቲን፣ አሌክሳንደር ቶትሚን እና ኒኮላይ ማቱሴዬቭ የተባሉት አራት ግለሰቦች በተከሰከሰው አውሮፕላን ውስጥ ተሳፋሪ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ሁሉም የቫግነር ተዋጊዎች እንደሆኑ ይታመናል።

እንደ ዲሚትሪ እና ቼካሎቭ እነዚህ አራት ግለሰቦች በዓለም አቀፉ ማዕቀብ ዝርዝሮች ላይ ስማቸው አልተጠቀሰም። እንዲሁም በምዕራባውያን መንግሥታት እንደ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አልተቆጠሩም።

ፕሪጎዢን ራሱን በቅርብ ሰዎቹ የሚከብ ሲሆን፣ በተለይም ከቭላድሚር ፑቲን ጋር የነበረው ቁርሾ መክረሩን ተከትሎ አራቱ ግለሰቦች እንደ ግል ጠባቂዎቹ አብረውት እየተጓዙ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።

ሦስቱ ግለሰቦች የቭጌኒ ማካርያን፣ ሰርጌይ ፕሮፑስቲን እና አሌክሳንደር ቶትሚን በዩክሬን ደጋፊ ተሟጋቾች ዘንድ የቫግነር ተዋጊ ተብለው በመረጃ ቋት ውስጥ ስማቸው ከተዘረዘሩት መካከል ተካተዋል።

ሆኖም በሩሲያ ባለሥልጣናት ዘንድ ኒኮላይ ማቱሴዬቭ ተብሎ የተጠቀሰው ግለሰብ በቫግነር ተዋጊዎች ስም ዝርዝር ውስጥ አልገባም።

አንድ የሩሲያ ቴሌግራም ቻናል በበኩሉ የቫግነር አጥቂ ክፍል አባል የሆነው ኒኮላይ ማቱሴቪች ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል።

የተከሰከሰው አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሦስቱ የአውሮፕላኑ ሠራተኞች

ዋና አብራሪ አሌክሲ ሌቭሺን፣ ረዳት አብራሪ ሩስታም ካሪሞቭ እና የበረራ አስተናጋጇ ክሪስቲና ራስፖፖቫ በተከሰከሰው አውሮፕላን ውስጥ ህይወታቸው እንዳለፈ የተገለጹ ሦስት የበረራ ሠራተኞች ናቸው።

ሦስቱ የበረራ ሠራተኞች በቀጥታ በፕሪጎዢን ኩባንያ ወይም በሌላ ኩባንያ ስለመቀጠራቸው እንዲሁም ሌሎች መረጃዎችን በተመለከተ ግልጽ የሆነ ነገር የለም።

ፕሪጎዢን በመደበኛነት በግል ጄቱ የሚጓዝ ሲሆን፣ አደጋው የተከሰተበት ኤምብራየር ሌጋሲ የተሰኘው ብራዚል ሰራሽ ጄት ከዚህ ቀደም ይጠቀምበት እንደነበር ታውቋል። አውሮፕላኑ ከአራት ዓመት በፊትም በአሜሪካ ማዕቀብ ተጥሎበት ነበር።

ቢቢሲ ስለ በረራ ሠራተኞቹ ዝርዝር መረጃዎችን አግኝቶ ለማረጋገጥ ባይችልም፣ ነገር ግን ከዘመዶቻቸው ጋር የተደረጉ ቃለ ምልሶችን የያዙ ዘገባዎች በሩሲያ ድረ ገጾች ላይ እየተስራጩ ይገኛሉ።

የ39 ዓመቷ ክርስቲና በረራው ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ቤተሰቧን አነጋግራ፣ ፎቶግራፎችን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ለጥፋ እንደነበር ተነግሯል።

ረዳት አብራሪው የ29 ዓመቱ ሩስታም በኩባንያው ውስጥ የሠራው ለሦስት ወራት ያህል ብቻ እንደሆነ እና አራተኛ የጋብቻ በዓሉንም በቅርቡ እንዳከበረ የሩሲያ ሚዲያ ከአባቱ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ ዘግቧል።

የ51 ዓመቱ ዋና አብራሪ አሌክሲ ሌቭሲን ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት የነበረ ሲሆን፣ ሙሉ ሕይወቱን በአቪዬሽን ዘርፍ እንደሠራ የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ቤተሰቦቹን ዋቢ በማድረግ ዘግበዋል።