የቫግነር አዛዥ የቭጌኒ ፕሪጎዢን በሞት ጥላ ሥር ነበር?

የቭጌኒ ፕሪጎዢን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ባለፈው ሰኔ ወር በሞስኮ ላይ ወታደራዊ አመጽ ካካሄደ ጀምሮ የቭጌኒ ፕሪጎዢን በሩሲያውያን ዘንድ በቅርቡ ሟች እንደሆነ ተደርጎ ይገለጽ ነበር።

በቅጥረኛ ቡድኑ መሪ በሕይወት የመቆያ ጊዜን በተመለከተ አስተያየት የሰጡት የአሜሪካው የስለላው ተቋም (ሲአይኤ) ዳይሬክተር ዊሊያም በርንስ “እኔ ፕሪጎዢንን ብሆን ኖሮ፣ የምግብ ቀማሸን አላቃጥልም ነበር” ብለዋል የፑቲን የቀድሞ ምግብ አብሳይ (ሼፍ) የነበረው ፕሪጎዢን ሊገደል እንደሚችል በመጠቆም።

ፕሪጎዢን ተሳፍሮበት የነበረው አውሮፕላን ተከስክሶ ሕይወቱ ማለፉ የተነገረውም ዳይሬክተሩ አስተያየቱን ከሰጡ ከአንድ ወር በኋላ ነው።

ፕሪጎዢንን ያሳፈረው አውሮፕላን በበረራ ላይ እያለ እንዲከሰከስ መደረጉ ሆነ ተብሎ በክሬምሊን የተፈፀመ በቀል መሆኑ ከተረጋገጠም ክስተቱን በሩሲያ ታሪክ የተፈፀመ “ልዩ የሆነ ወታደራዊ ኦፕሬሽን” ያደርገዋል።

የቀድሞው ፍርደኛ፣ ምግብ አብሳይ (ሼፍ) የነበረው እና በኋላ ላይ የቅጥረኛ ወታደሮች አዛዥ የነበረው ፕሪጎዢን፣ በቫግነር ቅጥረኛ ጦር ውስጥ እና ከዚያም ባሻገር በርካታ አድናቂዎች ነበሩት።

ከሁለት ወር በፊት ለ24 ሰዓታት ብቻ ለቆየው አመጽ ወደ ደቡባዊ የሩሲያ ከተማ ሮስቶቭ ኦን ዶን ሲያቀና ሕዝቡ ያደረገለትን ደማቅ አቀባበል በርካቶች ተመልክተዋል።

ይሁን እንጂ በሞስኮ በርታ ባላንጣዎች ነበሩት። ይህም በተደጋጋሚ እና በግልጽ ትችት ሲሰነዘርባቸው በነበሩት በሩሲያ ጦር የላይኛው የሥልጣን እርከን ላይ ባሉ ባለሥልጣናት በይበልጥ ታይቷል።

ፕሪጎዢንን ለሞት ለዳረገው ስህተት ያበቃውም እንደ አውሮፓውያኑ ሰኔ 23 በሞስኮ ላይ አመጹን ሲያስነሳ የፕሬዝዳንት ፑቲንን ቀይ መስመር መተላለፉ ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል።

በዚያን ወቅት ፕሪጎዢን ምንም እንኳን ፑቲንን በስም ባይጠቅስም ሩሲያ የካቲት 2022 ላይ በዩክሬን ላይ ለከፈተችው ወረራ በይፋ የተሰጡትን ምክንያቶች በመተቸት ክሬምሊንን አስቆጥቷል።

ሩሲያውያን እንደተታለሉ እና በደካማ አመራር ምክንያት ልጆቻቸው በዩክሬን ጦርነት እየሞቱ እንደሆነ ተናግሮ ነበር።

ይህም በሩሲያ ባለሥልጣናት ዘንድ ቁጣን የፈጠረ ሲሆን ፑቲን የዚያኑ ዕለት ያስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክትም መራር ነበር።

ፑቲን በመልዕክታቸው ፕሪጎዢን በሞስኮ ላይ ያስነሳውን አመጽ “ክህደት እና ከጀርባ እንደመወጋት ነው” ብለውታል።

ቭላድሚር ፑቲን ደግሞ በባህሪያቸው ከሃዲዎችንም ሆነ ተቃዋሚዎቻቸውን ይቅር የሚሉ ሰው አይደሉም።

ከዚህ ቀደም የቀድሞው የሩሲያ የደኅንነት መኮንን የነበረው እና ኋላ ላይ ተቃዋሚ የሆነው አሌክሳንደር ሊትቪኔንኮ፣ ፖሎኒየም 210 በተባለ ራዲዮአክቲቭ ከተመረዘ በኋላ በሕመም ሲሰቃይ ቆይቶ በ2006 በለንደን ሆስፒታል ሕይወቱ አልፏል።

በእርሱ ላይ የተካሄደው ምርመራም ከሩሲያ መንግሥት ቤተ ሙከራ የወጣ ነው የተባለ አደገኛ የተባለውን ንጥረ ነገር ነፍሰ ገዳዮች ከሩሲያ በማምጣት እንደመረዙት ድምዳሜ ላይ ደርሷል።

ይሁን እንጂ ሞስኮ በጉዳዩ ላይ እጇ እንደሌለበት የገለጸች ሲሆን፣ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ለማድረግ አልፈቀደችም።

ከዚያም የሩሲያ ደኅንነት ኤጀንሲ የቀድሞ መኮንን እና በኋላ ላይ ከድቶ ዩናይትድ ኪንግደም የነበረው ሰርጌይ ስክሪፓል እንደ አውሮፓውያኑ 2018 ከሴት ልጁ ዩሊያ ጋር ለጥቂት ከሞት ተርፈዋል።

በሩሲያ ውስጥም ተቺዎችን እና ባለሃብቶችን ጨምሮ የሞት ጽዋን በድንገት የተጎነጩ ጥቂቶች አይደሉም። በአንዳንድ ሁኔታዎችም ከፎቅ ላይ በመውደቅ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎችም አሉ።

ፕሬዝዳንት ፑቲን ተቀናቃኝ አሌክሲ ናቫንሊይ ፖለቲካዊ ክስ በግዞት ቅጣት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ እርሱም ቢሆንም በ2020 ወደ ሰርቢያ ሲያቀና አውሮፕላን ውስጥ ከተመረዘ በኋላ ከሞት አፋፍ ተርፏል።

ሆኖም የፕሪጎዢን ጉዳይ ከእነዚህ ሁሉ የተለየ ነው። የእርሱ መሞትም ለበርካታ ሩሲያውያን መነጋገሪያ ሆኗል። በበርካቶች ዘንድ ለክሬምሊን እጅግ ጠቃሚ ሰው እንደነበር የሚታሰብ ሲሆን፣ በጥቂት ሩሲያውያን ዘንድም እንደ “ብሔራዊ ጀግና” ይታያል።

የቭጌኒ ፕሪጎዢን( በግራ) እንደ አውሮፓውያኑ 2011 ቭላድሚር ፑቲንን ሲያስተናግዱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የቭጌኒ ፕሪጎዢን( በግራ) እንደ አውሮፓውያኑ 2011 ቭላድሚር ፑቲንን ሲያስተናግዱ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቅጥረኛ ተዋጊዎች ቡድን ቫግነር የተመሠረተው እንደ አውሮፓውያኑ 2014 ሲሆን የተመሠረተውም በሩሲያ የቀድሞ ልዩ ኃይል (ስፔዝናዝ) እና በሌሎች ወታደሮች ጠንካራ መሠረት ላይ ነው።

ቡድኑ በተለይ በምሥራቅ ዩክሬን በስፋት ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን፣ የዩክሬን ጦር ከባኽሙት እንዲወጣ አድርጓል። ይህም ቫግነር አስፈሪ ስም እንዲኖረው አስችሎታል።

ከዚያም ፕሪጎዢን ራሱ የሩሲያ እስር ቤቶችን በመጎብኘት በሺዎች የሚቆጠሩ አስገድዶ መድፈር ወንጀል የፈፀሙ እና ነፍሰ ገዳዮችን ጨምሮ በርካታ ፍርደኞችን በመመልመል ቡድኑን አጠናክረዋል።

እነዚህ ምልምሎችም በምሥራቃዊ ዩክሬን በሚፈለገው ሁኔታ ጥቅም ላይ ውለዋል።

ቫግነር በሶሪያ ውስጥ ለዓመታት የተዋጋ ቢሆንም፣ ለክሬምሊን ወሳኝ የሆነ ውጤት ያስመዘገበው ግን በአፍሪካ ውስጥ ነው።

ቡድኑ በአፍሪካ ውስጥ ጭካኔ የተሞላበት አሠራር የፈጠረ ሲሆን፣ በዚህም ዲሞክራሲያዊ ባልሆኑ አገዛዞች እውቅናን አትርፏል።

ልዩ እና ከፍተኛ ጥበቃ (ቪአይፒ) የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ከመጠበቅ ጀምሮ ምርጫዎች ላይ ተፅዕኖ እስከ ማድረግ እና ትችቶችን እሰከ ማፈን የሚደርስ የደኅንነት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።

በምላሹ ውድ ማዕድናትን የማውጣት መብትን በመጎናጸፍ ወርቅን ጨምሮ ሌሎች ውድ ማዕድናትን ከበርካታ አፍሪካ አገራት አግኝቷል።

ገንዘቡን ወደ ሩሲያ በመላክም ሁሉም ሃብታም እንዲሆኑ አድርጓል።

ከዚህም ባሻገር የቫግነር ወታደሮች በማሊ እና በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የተፈፀመውን የሰላማዊ ሰዎች ጭፍጨፋ ጨምሮ በበርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይከሰሳሉ።

ሆኖም የፈረንሳይን እና ሌሎች የምዕራባውያን ኃይሎችን ቦታ በመተካት በአህጉረ አፍሪካ ስኬትን ተቀዳጅተዋል።

ፕሪጎዢን ለመጨረሻ ጊዜ የታየው በዚህ ሳምንት በቴሌግራም ቻነል ላይ በተጋራ እና ማሊ ውስጥ የተቀረጸ ሳይሆን አይቀርም በተባለ ቪዲዮ ላይ ነው።

በመልዕክቱም የቫግነርን እንቅስቃሴ በአፍሪካ እንደሚያስፋፋ እና ለሕዝቦች ነጻነት እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል።

ይህ ሁሉ ቢሆንም በሞስኮ በተለይ በጦር ደኅንነቶች በኩል ለፑቲን አስተደዳር እና በዙሪያቸው ላለ ሥርዓት የወደፊት ስጋት ተደርጎ ይታይ ነበር።