የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን በአውሮፕላን አደጋ መሞቱ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, TELEGRAM
የቫግነር ቡድን መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ተሳፍሮበት የነበረ አውሮፕላን ተከስክሶ ሁሉም ተሳፋሪዎች መሞታቸውን ሩሲያ ሲቪል አቭዬሽን ባለሥልጣን አስታወቀ።
ከፕሪጎዢን በተጨማሪም በአውሮፕላኑ ውስጥ አብረውት የነበሩት ዘጠኝ ሰዎችም ሞተዋል።
ቀደም ሲል ከቅጥረኛ ቡድኑ ቫግነር ጋር ግንኙነት ያለውና "ግሬይ ዞን" የተሰኘ የቴሌግራም ቻናል እንደዘገበው ፕሪጎዢን ተሳፍሮበት የነበረው ጄት በአየር መከላከያ ተመትቶ ወድቋል ብሏል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ጄት አውሮፕላኑ የተመታው በሰሜናዊ ሞስኮ ቴቨር ክልል ውስጥ ነው።
ፕሪጎዢን ከጥቂት ወራት በፊት በሩሲያ ጦር ላይ ያልተሳካ አመጽ መምራቱ ይታወሳል።
ከሞስኮ ወደ ሴንት ፒተርስበርግ እየበረረ የነበረው ጄት ሰባት ተሳፋሪዎች እንዲሁም ሦስት የበረራ ሠራተኞችን አሳፍሮ ነበር።
ግሬይ ዞን እንዳለው የአካባቢው ነዋሪዎች ከአደጋው በፊት ሁለት ጊዜ የፍንዳታ ድምጽ መስማታቸውን እንዲሁም አውሮፕላኑ ሲበር የተወውን የጭስ መስመር ማየታቸውን ገልጸዋል።
ታስ የዜና ወኪል በበኩል አውሮፕላኑ መሬት ላይ ሲከሰከስ በእሳት መያያዙን ዘግቧል።
እስካሁንም የአራት ግለሰቦች አስከሬን መገኘቱን ዘገባው ጨምሮ አስነብቧል።
አውሮፕላኑ ከተነሳ በኋላ በአየር ላይ የቆየው ከግማሽ ሰዓት በላይ እንደማይሆን ነው የተጠቀሰው።
የቭጌኒ ፕሪጎዢን በአገሩ ላይ ያስነሳው ነውጥ ከከሸፈ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መልዕክቱን በቪዲዮ ከሰሞኑ አስተላልፎ ነበር።
ቪዲዮው ፕሪጎዢን አፍሪካ ውስጥ እንደሚገኝ የሚጠቁም ቢሆንም የት እንደተቀረጸ ቢቢሲ ማረጋገጥ አልቻለም።
ወታደራዊ መለዮ ለብሶ የሚታየው የቅጥረኛ ቡድኑ መሪ ቡድኑ ቫግነር አፍሪካን በበለጠ ነጻ እያደረገ መሆኑን ተናግሮ ነበር።
የቭጌኒ ፕሪጎዢን በዚህ ቪዲዮ ላይ ባስተላለፈው መልዕክት በአህጉሪቱ ውስጥ በማዕድን ፍለጋ እንዲሁም እስላማዊ ታጣቂዎችን እና ሌሎች ወንጀለኞችን በመዋጋት ላይ እንደሆነም ተናግሯል።
“በአሁኑ ወቅት በሥራ ተጠምደናል። የሙቀት መጠኑ ከፍተኛ ነው። ሁሉንም ነገር ወደነዋል። ቫግነር ወታደራዊ ክትትሎችን እንዲሁም ፍለጋዎችን ያካሂዳል። በዚህም ሩሲያን በሁሉም አህጉራት ታላቅ ያደርጋታል፣ እንዲሁም አፍሪካን በበለጠ ነጻ ያደርጋታል” ሲልም ተናግሯል።
“ፍትህ እና ደስታ ለአፍሪካ ሕዝቦች፤ ለእስላማዊው መንግሥት፣ ለአልቃይዳ እና ሌሎች አመጸኞች ሕይወታቸውን በቅዠት እየሞላነው ነው” ብሏል።
ቫግነር እራሱን ‘የግል የጦር ኩባንያ’ ብሎ ይገልጻል።
እውነቱ ግን ለሩሲያ መንግሥት ቅርበት ያለው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ነው።
መሥራቹ የቀድሞው ወንጀለኛ የአሁኑ የቭላድሚር ፑቲን የቅርብ ወዳጅ የነበረው የቭጌኒ ፕሪጎዚን ነው።
ቡድኑ የግል ኩባንያ ነው።
ዋና ተግባሩ ደግሞ ተቀጥሮ መዋጋት ነው።
በዩክሬን ጦርነት ከሩሲያ ጎን በመሰለፍ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ነው።
በአፍሪካ ከ10 ባላነሱ አገራት ውስጥ ተሰማርቷል።
ቫግነር በአፍሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎች እንዳሉት የሚታመን ሲሆን በሰፈረባቸውም አገራት በትርፋማ ንግዶች እየተሳተፈ ስለመሆኑ ይነገራል።
የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ በተለያዩ የመብት ተሟጋቾች የጦር ወንጀሎችን በመፈጸም የሚከሰሰው የዚህ ቡድን ተዋጊዎች በዋናነት በማሊ እንዲሁም በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ይገኛሉ።
ባለፈው ወር ዩናይትድ ኪንግደም በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በሚገኙ ሁለት የቫግነር ኦፕሬሽን ኃላፊዎች ላይ ማዕቀብ ጥላለች።
ለዚህም ምክንያቱ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ማሰቃየት እና ግድያ ፈጽመዋል በሚል ነው።












