ሩሲያን አሸብሮ የነበረው የቫግነር ቡድን ማን ነው? መሪውስ?

የቫግነር መስራች እና መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን (መሃል) ከሩሲያ መከላከያ ሚንስትር ጋር ሲነጋገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የቫግነር መስራች እና መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን (መሃል) ከሩሲያ መከላከያ ሚንስትር ጋር ሲነጋገሩ

ሩሲያ ከጥቂት ወራት በፊት ውጥረት አይሎባት ነበር።

ቫግነር የተባለው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስተዳደር ላይ አምጾ በሞስኮ ውጥረትም ነግሶ፤ ሽብርም ተነዝቶ ነበር።

በአሁኑ ወቅት ህይወቱ አልፏል የተባለው የቡድኑ መስራች የቭጌኒ ፕሪጎዢን የሩሲያን መከላከያ ከፍተኛ አመራሮች “ልክ አስገባለሁ” ብሎ ዝቶ ወደ ሞስኮ መገስገስ ጀምሮ ነበር።

ይሁን እንጂ በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስተዳደር ላይ አመጽ አስነስተው ወደ ሞስኮ ሲገሰግሱ የነበሩት የቅጥረኛው ቫግነር ቡድን መሪ የጦር እንቅስቃሴያቸውን ለማቆም ተስማምተው ከአገር ወጥተዋል።

ቫግነር ማነው?

ቫግነር እራሱን ‘የግል የጦር ኩባንያ’ ብሎ ይገልጻል። እውነቱ ግን ቢያንስ እስከ ትላንት በስቲያ ድረስ ለሩሲያ መንግሥት ቅርበት ያለው፤ ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ነው።

እጅግ ምስጢራዊ እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ቡድን ዋና ተግባሩ ተቀጥሮ መዋጋት ነው።

ይህ የሩሲያዊያን የቅጥር ተዋጊዎች ስብስብ ሩሲያ በሌሎች አገራት ላይ ለሚኖራት ፖለቲካዊ ፍላጎት ወታደራዊ ምላሽ የሚሰጥ ድርጅት እንደሆነ አንዳንድ ተንታኞች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

ምንም እንኳ ይህ ቡድን ከሩሲያ ጋር በተደጋጋሚ ይነሳ እንጂ ሞስኮ ከዚህ ቅጠረኛ ተዋጊዎች ቡድን ጋር ግንኙነት የለኝም ስትል ታስተባብላለች።

የቫግነር ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጦር እንቅስቃሴ የገባው እአአ በ2014 ሩሲያ ክሬሚያን ወደ ግዛቷ በጠቀለለችበት ወቅት እንደነበረ ይታመናል።

ይህ ቅጥረኛ ቡድን ‘የግል ኩባንያ’ ነኝ ይበል እንጂ ከሩሲያ በተጨማሪ ከሌሎች አገራት ጋር ግንኙነት አለው።

በሶሪያ እንዲሁም በአፍሪካ ከ10 ባላነሱ አገራት ውስጥ ተሰማርቶ ይገኛል አልያም ተሰማርቶ ነበር።

ሊቢያ፣ ሞዛምቢክ፣ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ፣ ማሊ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፓብሊክ፣ ከሰሞኑ ደግሞ በሱዳን የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ስሙ እየተነሳ ነው።

በዩክሬን ጦርነት ደግሞ ከሩሲያ ጎን ተሰልፎ በመዋጋት ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።

ይህ ቡድን በሚሰማራባቸው አገራት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በማድረስ እና ከጦር ወንጀሎች ጋር ስሙ በተደጋጋሚ ይነሳል።

እንደማሳያ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች የቫግነር ወታደሮች በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ሰላማዊ ሰዎችን በመግደል፣ በማሰቃየትና በመደብደብ ከሷቸዋል።

ሂውማን ራይትስ ዎች የዓይን ምስክሮች ዋቢ አድርጎ በ2020 አውጥቶት በነበረው ሪፖርት ቡድኑ 10 ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎችን ከገደለ በኋላ ከመንገድ ዳር ባለ ጉድጓድ ውስጥ አስክሬናቸውን ጥሏል ብሏል።

ይህ ቡድን ገንዘብ ተቀብሎ አልያም በአልማዝ ፣ በወርቅ እና በዩራኒየም በበለጸጉ አገራት በመሰማራት የሚሰጠውን ተልዕኮ ያለአንዳች ጥያቄ ይፈጽማል ይባላል።

የቫግነር ቡድን አባላት በሱዳን
የምስሉ መግለጫ, የቫግነር ቡድን አባላት በሱዳን

ቫግነር ምን ያክል ጠንካራ ነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች በኋላ የዚህ ቡድን ኃይል በብርቱ ጨምሯል። አባላቱ ቁጥራቸው ጨምሯል። የሚታጠቀው መሳሪያ ብዛት እና አይነት ከፍ ብሏል።

ዩናይትድ ኪንግደም ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ በዩክሬን የሚገኙ የቅጥረኛ ቡድኑ ተዋጊዎች ቁጥር ከ1,000 ወደ 20,000 ማደጋቸውን ይፋ አድርጋ ነበር።

ቫግነር አብዛኛውን ግዜ አባል አድርጎ የሚመለምላቸው ሥራ አጦች፣ የጦር አዋቂዎችና በሩሲያ ብሔራዊ ስሜት ተነሳስተው በተዋጊነት ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ ግለሰቦችን ነው።

በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ብዙ አባላቱን ያጣው ቫግነር አዲስ አባላትን ለመመልመል ወደ ሩሲያ እስር ቤቶች ፊቱን አዙሮ ነበር።

የቅጥረኛው ቫግነር ቡድን መስራች እና መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን በዩክሬን ጦርነት ውስጥ ለሩሲያ የሚዋጉ ወታደሮችን ከእስረኞች መካከል ሲመለምል ሾልኮ በወጣ ተንቀሳቃሽ ምስል ታይተው ነበር።

“ለስድስት ወራት ካገለገላችሁ [ለቫግነር ቡድን]፤ ነጻ ናችሁ” ካሉ በኋላ ለመዋጋት ከተስማሙ በኋላ ክህደት በሚፈጽሙት ላይ ከባድ ቅጣት እንደሚኖር ፕሪጎዢን ሲያስጠነቅቁ በዚህ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ታይተዋል።

ቫግነር በጦር እንቅስቃሴው ጦር መሳሪያዎችን ከሚገኝባቸው አገራት መካከል ሰሜን ኮሪያ አንዷ መሆኗ ይጠቀሳል።

አሜሪካ ከዚህ ቀደም ዩክሬንን ለማጥቃት የሚውሉ ሚሳኤሎችን እና ሮኬቶችን ሰሜን ኮሪያ ለቫግነር እያቀረበች ነው ስትል ከሳ ነበር።

እንደ አሜሪካ ከሆነ ቫግነር ከሰሜን ኮሪያ ለሚቀበላቸው ጦር መሳሪያዎች ከፍያው የሚፈጸመው በሩሲያ ነው።

በአንድ ወቅት የኋይት ሃውስ የብሔራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ፤ ቫግነር በዩክሬን እያደረገው ባለው ጦርነት በየወሩ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እያወጣ ነው ብለው ነበር።

ሩሲያ ከቫግነር ቅጥረኛ ተዋጊዎች ቡድን ጋር ግንኙነት የለኝም ስትል ታስተባብል እንጂ፣ የቡድኑ መሥራች ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ቅርብ ግንኙነት ነበራቸው።

የቭጌኒ ከዚህ ቀደም በወንጀል ድርጊቶች ጥፋተኛ ተብሎም ተፈርዶበታል። የቭጌኒ “የፑቲን ሼፍ” በመባል የሚታወቅ ከበርቴ ነው። 'የፑቲን ሼፍ' የሚለውን ስያሜ ያገኘው የክሬምሊን ምግብ አዘጋጅ እና የሬስቶራንት ባለቤት ስለነበር ነው።