ሩሲያ የቫግነሩን አዛዥ ፕሪጎዥን እንዲገደል ትዕዛዝ ሰጥታለች መባሏን ውድቅ አደረገች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሩሲያ የቅጥረኛው ተዋጊ ቡድን (ቫግነር) አዛዥ የቭጌኒ ፕሪጎዥን እንዲገደል ትዕዛዝ ሰጥታለች መባሏን ውድቅ አደረገች።
የፑቲን ቃለ አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ክሬምሊን ፕሪጎዥን እንዲገደል ትዕዛዝ ሰጥቷል መባሉ "ፍጹም ሃሰት ነው" ብለዋል።
ቃለ አቀባዩ በአውሮፕላኑ ላይ ስለደረሰው አደጋ እንዲሁም ተሳፍረው ስለነበሩት ግለሰቦች "አሳዛኝ ሞት" "በርካታ መላ ምቶች እየተሰነዘሩ ነው" ብለዋል።
"በምዕራቡ ዓለም በእርግጥ ይህ መላ ምት የሚመጣው ከተወሰነ አቅጣጫ ነው። ሁሉም ፍጹም ሃሰት ነው። በእርግጥ ስለ አደጋው ስንነጋገር በመረጃዎች እና በእውነታዎች ብቻ ልንመራ ይገባል" ብለዋል።
አክለውም "በአሁኑ ጊዜ ብዙ መረጃዎች የሉም።በአሁኑ ወቅት ይፋዊ ምርመራ የተከፈተ ሲሆን ያሉትም መረጃዎች ሊፈተሹ ይገባል" ብለዋል።
በርካታ ሩሲያውያን ከሁለት ቀናት በፊት ህይወቱን ቀጥፏል የተባለው የአውሮፕላን አደጋ ጀርባ ያለው ክሬምሊን ነው የሚል ጥርጣሬ አላቸው።
ከሩሲያውያን በተጨማሪም ምዕራባውያን አገራትም ከግድያው ጀርባ ያሉት የሩሲያ ባለስልጣናት እንደሆኑ ጠቁመዋል።
ነገር ግን ሩሲያ በጭራሽ ይህንን "ፍጹም ሃሰት" ነው ስትል ክዳለች።
በትናንትናው ዕለት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአውሮፕላን አደጋ ለሞቱት ቤተሰቦች ሃዘናቸውን ገልጸዋል።
ፑቲን የቅጥረኛው ተዋጊ ቡድን መሪ ፕሪጎዢን ከሟቾቹ መካከል መኖሩን በይፋ አላረጋገጡም።



















