ፕሪጎዢን የተሳፈረበት አውሮፕላን ከተከሰከሰ በኋላ ሩሲያ ምን አለች?

ክሬምሊን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሩሲያ በአስገራሚ ክስተቶች የተሞላች አገር ናት።

ሰው አልባ አውሮፕላኖች ( ድሮኖች) በሩሲያ መሃል ሞስኮ በተደጋጋሚ ጥቃት በማድረስ ፍንዳታዎችን ከፈጠሩ እና ሕንጻዎችን ካፈራረሱ በኋላ በርካቶች ተደናግጠዋል።

ከዚያም የሩሲያ መገበያያ ገንዘብ ሩብል ዋጋ ባልተጠበቀ ሁኔታ አሽቆልቁሏል።

በአጭር ጊዜ ውስጥም የአንድ ዶላር ምንዛሬ ዋጋ ከ100 ሩብል በላይ ደርሷል።

ጨረቃ ላይ ለማረፍ ያካሄደችው ተልዕኮዋም አልተሳካም። የሩሲያ ሉና- 25 ላንደር [ጨረቃ ወለል ላይ የሚያርፈው የመንኮራኩል አካል] ጠፈር ላይ ጠፍቶ የነበረ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ከጨረቃ ወለል ጋር ተጋጭቶ ወድሟል።

ዛሬ ደግሞ የቫግነር ቅጥረኛ ቡድን መሪ ዮቭጌኒ ፕሪጎዢን ተሳፍረውበታል የተባለው አውሮፕላን በሩሲያ ትቨር ክልል በእሳት ተያይዞ መከስከሱ ተሰምቷል።

ይህ ግን በርካታ ሰዎችን እምብዛም ያስደነገጠ አይመስልም።

እንዲያውም ሩሲያውያን ክስተቱ ቶሎ ባለማጋጠሙ ሳይገረሙ አልቀረም።

ምክንያቱም በሩሲያ የየቭጌኒ ፕሪጎዥን ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል በሚል ለሳምንታት የተለያዩ መላ ምቶች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቫግነሩ አለቃ ግልጽ የሆነ አመጽ የከፈቱት ልክ የዛሬ ሁለት ወር ነበር።

ቅጥረኛ ወታደሮቹም ዋና የሩሲያን ከተማ ይዘው የነበረ ሲሆን ወደ ሞስኮውም አምርተው ነበር።

ይህ አመጽ ከከሸፈ በኋላም ለፕሪጎዢን ቀን እየተቆጠረለት እንደሆነ በርካቶች ያስቡ ነበር።

አመጹ ለክሬሚሊን ውርደት የነበረ ሲሆን ፐሬዚደንት ፑቲንም ይቅርታ የሚያደርጉ እና የተፈፀመባቸውን የሚረሱ ሰው አይደሉም።

የሩሲያ የፌደራል አቪየሽን ኤጀንሲ ሮሳቪያትሲያ አውሮፕላኑ ከተከሰከሰ ከአንድ ሰዓት ገደማ በኋላ ባወጣው መግለጫ፣ በተከሰከሰው አውሮፕላን ውስጥ ተሳፍረው ከነበሩ ሰዎች ዝርዝር መካከል ፕሪጎዢን እንደሚገኝበት አስታውቋል።

ይህም ባልተለመደ መልኩ በፍጥነት ከኤጀንሲው የተሰጠ መግለጫ ነው።

ሮሳቪያትሲያ አብዛኛውን ጊዜ ለእንዲህ ዓይነት ክስተቶች ፈጣን ምላሽ አይሰጥም።ይህም ብዙዎችን አስገርሟል።

የሩሲያ የመንግሥት ቴሌቪዥንም ያለምንም አስተያየት የመንግሥት ባለሥልጣናትን በመጥቀስ ስለአደጋው መዘገቡን ቀጥሏል።

በምሽቱ የዜና እወጃውም ክሬሚሊን በዜናዎቿ ቻናል 1ን የተቆጣጠረች ሲሆን ለተፈጠረው የአውሮፕላን አደጋም የ30 ሰከንድ ሽፋን ሰጥታለች።

የሩሲያ የቴሌቪዥን አውታር ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነት ክስተቶችን ለመዘገብ እንዴት መዘገብ እንዳለበት የሚገልጽ የባለሥልጣናት መመሪያ እስከሚደርሰው ድረስ ይጠብቃል።

ከቅጥረኛ ወታደሮቹ ጋር ግንኙነት ያለው የቫግነር ቡድን የቴሌግራም መድረክ በበኩሉ “ፕሪጎዢን በሩሲያ ከዳተኞች እንደተገደለ” ገልጿል።

በሴንት ፒተርስበርግ በሚገኘው በቫግነር ዋና መሥሪያ ቤት ጊዜያዊ የፀሎት ሥፍራ ተዘጋጅቷል።

የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ያወጡት ምስሎችም ሰዎች አበባ እና ሻማ በመያዝ ወደ ቫግነር ማዕከል ሲሄዱ አሳይተዋል።

አሁን ላይ ያለው ዋና ትኩረት ግን የአውሮፕላኑ አደጋ መንስኤ ምንድን ነው የሚለው ሆኗል።

እንደ የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ከሆነ መርማሪዎች ከውጭ ሊፈፀም የሚችል ጥቃትን ጨምሮ የአደጋውን መንስኤ እየመረመሩ ነው።

ሆኖም በክስተቱ ላይ አስተያየት የሰጡት የፖለቲካ ተንታኝ ታቲያና ስታኖቫያ፣ "አውሮፕላኑ የተከሰከሰበትን ምክንያት ማወቅ አስፈላጊ አይደለም፤ ይልቁኑ ወሳኙ ነገር ለሌሎች ቅጥረኞች የላከው መልዕክት ነው" ብለዋል።

ምክንያቱም “ይህንን ሁሉም ሰው የበቀል እና ቅጣት እርምጃ አድርገው ያዩታል። ከዚህም በተጨማሪ ከጸጥታ ኃይሎቹ እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት መካከል በርካቶቹ የፕሪጎዢንን ሞት እንደ ትምህርት ሊወስዱት ይችላሉ" ሲሉ አስረድተዋል።