የቭጌኒ ፕሪጎዢን፡ስለተከሰከሰው አውሮፕላን እስካሁን የምናውቀው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን (ቫግነር) መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ተሳፍሮበት የነበረው አውሮፕላን መከስከሱ ተነግሯል።
በመዲናዋ ሞስኮ ሰሜናዊ ግዛት በሚገኝ ስፍራ በተከሰከሰው አውሮፕላን ተሳፍሮም እንደነበር ነው የሩሲያ ባለስልጣናት የተናገሩት።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቁልፍ አጋር የነበረው ፕሪጎዢን የሚመራው ቅጥረኛ ወታደራዊ ኩባንያውም በዩክሬን ጦርነት ላይ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
ነገር ግን በዚህ ዓመት ፕሪጎዢን በሩሲያ ወታደራዊ አመራር ላይ ለአንድ ቀን የዘለቀ ዓመጽ አስነስቶም ተዋጊዎቹ ወደ ሞስኮ እንዲዘምቱ ማዘዙን ተከትሎ ከፑቲን ጋር የነበረው ግንኙነት ሻከረ።
አደጋውን አስመልክቶ መረጃዎች ገና እየወጡ ቢሆንም እስካሁን የምናውቀው መረጃዎችን አጠናቅረናል።
አውሮፕላኑ ምን አጋጠመው?
ኢምብራየር ሌጋሲ የተሰኘው አውሮፕላን ረቡዕ አመሻሽ ላይ በሞስኮ እና በሴንት ፒተርስበርግ መካከል ሲበር እንደነበር የሩሲያ አቪዬሽን ባለስልጣናት አስታውቀዋል። አውሮፕላኑም በሰሜናዊ ሞስኮ በሚገኘው ቴቨር ክልል የመከስከስ አደጋ እንዳጋጠመው ባለስልጣናቱ አረጋግጠዋል።
ነገር ግን ከቫግነር ጋር ግንኙነት ያለው ግሬይ ዞን የተሰኘው የቴሌግራም ገጽ ጄቱ በሩሲያ ጦር ተመትቶ መውደቁን ዘግቧል። ሆኖም ለዚህ ክሱ ማስረጃ የሚሆን አባሪ መረጃ አላቀረበም።
የግል ጄቱ ሰባት ተሳፋሪዎችን እንዲሁም ሶስት የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ ነበር።
ከሩሲያ በተገኘ መረጃ መሰረት በአውሮፕላኑ ውስጥ ተሳፍረው የነበሩ 10 ሰዎች ተገድለዋል። ሁሉም አስከሬኖች መገኘታቸውም ተነግሯል።
በፕሪጎዢን አንደኛው ኩባንያ ስር የተመዘገበው ኢምብራየር ሌጋሲ መሬት ላይ ሲከሰከስም በእሳት ተያያይዟል። ጄቱ ከመሬት ከተነሳ በኋላ በአየር ላይ የነበረውም ከሰላሳ ደቂቀ በታችም እንደነበርም ተነግሯል።
በሩሲያ ኩዘንኪኖ ግዛት ውስጥ አንድ አውሮፕላን ከአየር ላይ ሲወድቅ የሚያሳይም ቪዲዮን ትክክለኛነትም ቢቢሲ አረጋግጧል።
ግሬይ ዞን እንደዘገበው ባለቤትነቱ የፕሪጎዢን የሆነው ሁለተኛ የንግድ ጄት በሞስኮ አካባቢም በሰላም አርፏል።
በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ተሳፋሪዎች እነማን ናቸው?
የግል ጄቱ ሰባት መንገደኞች እና ሶስት የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ ነበር።
የሩሲያ አቪዬሽን የሰባቱን መንገደኞች ማንነት የዘረዘረ ሲሆን እነዚህም የቫግነሩ መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን እንዲሁም ቀኝ እጁ ናቸው የሚባሉት ዲሚትሪ ኡትኪን፣ ሰርጌይ ፕሮፑስቲን፣ ዬቭግኒ ማካራያን፣ አሌክሳንደር ቶትሚን፣ ቫለሪ ቼካሎቭ እንዲሁም ኒኮላይ ማቱሲቭ ናቸው።
የበረራ ሰራተኞቹም አብራሪው አሌክሲ ሌቭሺን፣ ረዳት አብራሪው ሩስታም ካሪሞቭ እና የበረራ አስተናጋጅዋ ክሪስቲና ራስፖፖቫ መሆናቸውም ይፋ ተደርጓል።
ስለ ፕሪጎዢን የቅርብ ጊዜ እንቅስቃሴዎች ምን ይታወቃል?
ፕሪጎዢን እንደተሳፈረበት የሚታመነው የግል ጄት ከመዲናዋ በ60 ማይል ርቀት ላይ ከመከስከሱ በፊት ከሞስኮ ወደ ሴንት ፒተርስበርግ ሲጓዝ ነበር ተብሏል።
ፕሪጎዢን የሩሲያ ከፍተኛ የጦር አዛዦች በዩክሬን በሚያደርጉት የጦር ስትራቴጂ በተደጋጋሚ በሰላ ሲተችም ነበር።
በኋላም በጦሩ አመራሮች ላይ ለአጭር ጊዜ የቆየ እና የከሸፈ አመጽ ማስነሳቱን ተከትሎ ብዙም ስለሱ አይሰማም።
አመጹንም ለማስቆም በተደረገው ስምምነት ፕሪጎዢን ወደ ቤላሩስ እንዲያቀና መንገድ ተመቻችቶለት ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ፕሪጎዢን ለአጭር ጊዜም ቢሆን በቤላሩስ ቆይቶ ነበር።
በሃምሌ ወር አጋማሽ ላይ በቴሌግራም ቻናሎች ላይ የተጋራ ቪዲዮም ፕሪጎዢን በቤላሩስ ለተዋጊዎች አቀባበል ሲያደርግ ታይቷል። ነገር ግን በዚያ ወር ላይ እንዲሁ በአፍረካ- ሩሲያ የመሪዎች ጉባዔ ወቅት በሴንት ፒተርስበርግ ከተማም መገኘቱን የሚያሳይ ፎቶግራፍም ወጥቷል።
በአገሩ ላይ ያስነሳው ነውጥ ከከሸፈ በኋላ ባለፈው ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ መልዕክቱን በቪዲዮ አስተላልፏል።
ቪዲዮው ፕሪጎዢን አፍሪካ ውስጥ እንደሚገኝ የሚጠቁም ቢሆንም የት እንደተቀረጸ ቢቢሲ ማረጋገጥ አልቻለም።
ግሬይ ዞን የፕሪጎዢንን ሞት ከዘገበ በኋላ የሩሲያ አቪዬሽን ኤጀንሲ ከሞስኮ በስተሰሜን በሚገኘው በቴቨር ክልል የተከሰከሰውን አውሮፕላን ተሳፋሪዎችን ዝርዝር ይፋ በማድረግ አረጋግጧል።
በዝርዝሩም ውስጥ የፕሪጎዢን ስም ተካቷል።
በአሁኑ ወቅት ምን እየተከናወነ ነው?
የሩስያ መርማሪ ኮሚቴ እንዳስታወቀው የአደጋውን መንስኤ ለማወቅ የወንጀል ምርመራ መጀመሩን ነው። ምርመራው የትራፊክ ደህንነትን እና የአየር ትራንስፖርትን አሰራር በሚቆጣጠረው የአገሪቱ የወንጀል ህግ አንቀጽ 263 መሰረት እንደሚከናወን ተጠቅሷል።
የአደጋ ጊዜ አገልግሎት በበኩሉ የአውሮፕላን አደጋ የደረሰበትን ስፍራ ፍለጋቸውን ማጠናቀቁ ተገልጿል። አደጋው የደረሰበት የቴቨር ክልል አስተዳዳሪ ኢጎር ሩዴኒያ ምርመራውን በበላይ እንደሚቆጣጠሩት ተዘግቧል።












