ኩባ ዜጎቼ ለሩሲያ እንዲዋጉ እየተመለመሉ ነው ስትል ቅሬታዋን አሰማች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኩባ በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ለሩሲያ ተሰልፈው እንዲዋጉ ሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች የኩባ ዜጎችን እየመለመሉ መሆኑን ደርሼበታለሁ አለች።
የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ በሩሲያ የሚኖሩ እንዲሁም የኩባ ነዋሪ የነበሩ የአገሪቱ ዜጎች በዩክሬን በውጊያ ላይ ያለን የሩሲያ ጦር መቀላቀላቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።
ኩባ ምንም እንኳ የሩሲያ የቅርብ አጋር ብትሆንም፤ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ የካረቢያኗ አገር በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በየትኛውም መልኩ ተሳታፊ መሆን አልፈልግም ብላለች።
ኩባ ቅጥረኛ ወታደሮችን መመልመልን በተመለከተ ግልጽ እና ጠንካራ አቋም ነው ያለኝ በማለት ዜጎቿ በቀጥታ የጦርነት ተሳታፊ መሆኗቸው እንደማትቀበል አስታውቃለች።
ይህን የኩባ ወቀሳን ተከትሎ እስካሁን ድረስ በሩሲያ በኩል የተባለ ነገር የለም።
የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የአገሪቱን ዜጎች እየመለመለ ያለ ሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪ አለ ይበል እንጂ ምልመላውን እያደረገ ያለውን አካል በስም አልጠቀሰም።
ሩሲያ በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ወታደሮቿን በማጣቷ ባለፈው ነሐሴ ወር ላይ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የጦር ሠራዊት አባላት ቁጥር እንዲጨምር ለአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር።
ከዚያ በኋላ ራያዛን ጋዜት የተባለ የሩሲያ ጋዜጣ ሩሲያ ውስጥ የሚኖሩ የኩባ ዜጎች የሩሲያ ዜግነት እንደሚሰጣቸው ቃል ከተገባላቸው በኋላ ለሩሲያ ጦር ተሰልፈው በዩክሬን እየዋጉ ነው የሚል ዘገባ አውጥቶ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪ ለሩሲያ ለመዋጋት በጎ ፍቃደኛ የሰርቢያ ዜጎች ናቸው የተባሉ ወጣቶች ወታደራዊ ልምምድ ሲያደርጉ የሚያሳይ ምስል ወጥቶ ነበር።
“ዜጎቻችን በሌላ አገር ጦር መሳሪያ እንዲያነግቡ የሚሰሩ ሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ላይ ጠንካራ የሆነ እርምጃ እንወስዳለን” ይላል የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው ዘገባ።
ይህ ከኩባ መንግሥት የወጣው መግለጫ በቅርቡ የንግድ ስምምነት በተፈራረሙት ሁለቱ ወዳጅ አገራት መካከል ያልተለመደ መቃቃርን ያሳየ ሆኗል።
ከሁለት ወር በፊት የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ወደ ሞስኮ ለውይይት አቅንተው የነበረ ሲሆን የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ደግሞ እንዲሁ ሚያዚያ ወር ላይ ወደ ኩባ አምርተው ነበር።












