በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች “የጦር መሳሪያ ደብቃችኋል አምጡ” በሚል ግድያዎች መፈጸማቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች “የጦር መሳሪያ ደብቃችኋል አምጡ” በሚል በመንግሥት የጸጥታ አካላት ከፍርድ ውጭ ግድያዎች መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።
በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች ከቀጠለው ግጭት ጋር ተያይዞ በመንግሥት የጸጥታ አካላት ከፍርድ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎች እጅግ አሳሳቢም እንደሆነ ኢሰመኮ መስከረም 4/2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በመንግሥት የጸጥታ አባላት ከህግ ውጭ የተፈጸሙት ግድያዎች በአዴት፣ ደብረማርቆስ፣ ደብረታቦር፣ ጅጋ፣ ለሚ፣ ማጀቴ፣ መራዊ፣ መርጦ ለማርያምና ሸዋ ሮቢት ከተሞች ከሐምሌ 24- ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ተስፋፍተው የተፈጸሙ መሆኑም ተጠቅሷል።
የግድያዎቹ ሰለባዎች ከሆኑት መካከል ቤት ለቤት በተደረገ ፍተሻ የተያዙ፣ በግጭቱ ወቅት መንገድ ላይ የተገኙ እና ያልታጠቁ ሰዎች፣ “ የጦር መሳሪያ ደብቃችኋል አምጡ” በሚል የተያዙ ሰዎች ይገኙበታል ብሏል።
በተጨማሪ በአማራ ክልል ከተቀሰቀው ግጭት ጋር በተያያዘ እንደ አስፈላጊነቱ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ ተፈጻሚ ይሆናል ተብሎ ስራ ላይ ከዋለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘም የሰዓት እላፊ ገደቦችን ተላልፈው የተገኙ ሰላማዊ ነዋሪዎች በጸጥታ አካላት ከፍርድ ውጭ መገደላቸውን ኢሰመኮ ገልጿል።
በተጨማሪም ከመከላከያ ጋር በግጭት ላይ ያለው እና በቁጥጥር ስር የዋሉ የፋኖ ታጣቂ አባላትም ስለመገደላቸውም መግለጫው አስፍሯል።
በመንግሥት የጸጥታ አባላት ከፍርድ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎችን በተመለከተ ኮሚሽኑ እና የአስቸኳይ ጊዜ መርማሪ ቦርድ የተሟላ ምርመራ ሊያደርጉበት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥቷል።
ኮሚሽኑ ከፍርድ ውጭ ከሆኑ ግድያዎች በተጨማሪ፣ በክልሉ በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ እየደረሱ ያሉ ጉዳቶች እንዲሁም የዘፈቀደ እስር እጅግ አሳሳቢ መሆኑንም ተመልክቷል።
ኮሚሽኑ በአማራ ክልል ግጭቱ ወደ ክልሉ ልዩ ልዩ ወረዳዎችን መስፋፋቱን ከነዋሪዎች፣ ከተጎጂዎች፣ ከተጎጂ ቤተሰቦች እና ከዓይን እማኞች መረጃዎችን ሰብስቤያለሁ ብሏል።
በደብረ ማርቆስ፣ በአዴትና መራዊ፣ በደብረ ታቦር፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደልጊ፣ በማጀቴ፣ በሸዋ ሮቢት እና አንጾኪያ ከተሞች ከነሐሴ 19 እስከ ነሐሴ 30 በደረሱ ግጭቶች የንጹሃን ህይወት መቀጠፉንም ኢሰመኮ ገልጿል።
በእነዚህ ከተሞች አንዳንድ የገጠር ቀበሌዎች በተኩስ ልውውውጥ ወይም በከባድ መሳሪያ ተኩስ በርካታ ሰላማዊ ነዋሪዎች መሞታቸውን፣ ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን እና ንብረት መውደሙን የገለጸው ኢሰመኮ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ግን ያለው ነገር የለም።
ከሞቱትም መካከል በመንገድ እና በእርሻ ስራ ላይ እንዲሁም በቤታቸው ውስጥ የነበሩ ሰዎች ጭምር የተካተቱበት መሆኑን ኢሰመኮ ቤተሰቦች እና የዓይን እማኞችን ዋቢ በማድረግ በመግለጫው አስፍሯል።
በአማራ ክልል በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ውጊያ ረገብ ብሎ እንደነበር የተዘገበ ቢሆንም ከከተሞች ወጥቶ በክልሉ ባሉ የገጠር ቀበሌዎች ላይ እየተካሄደ ስለመሆኑ አንዳንድ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።
የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች በድርድር እንዲፈቱ ለመወያየት በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ አቅንተው የነበረ ሲሆን ስለደረሱበት ጉዳይ የተባለ ነገር የለም።
ሆኖም በቅርቡ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ “ጽንፈኛ ኃይሎች ስጋት ወደማይሆኑበት ደረጃ” ላይ ደርሰዋል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ መናገራቸው ይታወሳል።
ኢሰመኮ ሌላኛው በዚህ መግለጫ ያሰፈረው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያያይዞ የተስፋፋ እና የዘፈቀደ እስር እየተፈጸመ ስለመሆኑ ነው።
አዋጁን በበላይነት የሚመራው የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ኮማንድ ፖስት በይፋ ካሳወቃቸው እስሮችና ቦታዎች ውጭ በተለይም በአማራ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እስሮች ስለመፈጸማቸው እሰፍሯል።
ኮሚሽኑ ከጠቀሳቸውም የዘፈቀደ እስሮች ተፈጽሞባቸዋል ብሎ ከጠቀሳቸውም ስፍራዎች መካከል ባህር ዳር፣ ደብረ ታቦር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ጎንደር፣ ላሊበላ፣ መካነሰላም፣ ቆቦ እና ሸዋ ሮቢት፣ ሸገር እና አዲስ አበባ ከተሞች ይገኙበታል።
በተለምዶ አቦስቶ ተብሎ በሚታወቀው በደቡብ ክልል ማሰልጠኛ ኮሌጅ ግቢ የነበሩ ታሳሪዎች የተወሰኑት ቢለቀቁም ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቀ ሰዎች በዚህ ማሰልጠኛ ታስረው ይገኛሉ ብሏል።
በመንግሥት የጸጥታ አካላት የታሰሩ ሰዎች “ለታጣቂ ቡድኑ ድጋፍ ታደርጋላችሁ” እንዲሁም “የጦር መሳሪያ ደብቃችኋል” በሚል ምክንያት እንደሆነም ኢሰመኮ ገልጿል።
በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ገላን ክፍለ ከተማ ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ህጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ውሏቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ነዋሪዎች ተይዘው የሚቆዩበት ጊዜያዊ ማዕከል እንዳለም ተመልክቷል።
ሲዳ አዋሽ ወረዳ ተብሎ በሚጠራው አካባባቢ የሚገኘው ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከል ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፊት እና በኋላም ከጎዳና ላይ የተወሰዱ ሰዎች እንዲቆዩ የሚደረጉበት ቦታ ነው ብሏል።
በቅርቡ ወደ ማዕከሉ ከተወሰዱት ውስጥ 29 ሰዎች በመታወቂያ ካርዳቸው ተለይተው ተለቀዋል። የተወሰኑት ደግሞ በመልሶ ማቋቋም ፕሮግራም ወደየመጡበት አካባቢዎች እንዲመለሱ ተደርገዋል ብሏል።
በጣቢያው ውስጥ ተከስቶ የነበረው ተላላፊ በሽታ በቁጥጥር ስር የዋለ ስለመሆኑም ኮሚሽኑ በክትትሉ መመልከቱን አስፍሯል። በማቆያው ምን ያህል ሰዎች እንዳሉ እንዲሁም እስካሁን ሰዎች ስለመኖራቸው መግለጫው ያለው ነገር የለም።
ኮሚሽኑ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች፣ ከፍርድ ውጭ የሆኑ ግድያዎች እና የዘፈቀደ እስሮች በአፋጣኝ ማስቆም ይገባል ሲልም አሳስቧል።












