ኤርትራውያን በጀርመኗ ስቱትጋርት ከተማ ሁከት አስነስተው በመቶዎች የሚቆጠሩት በቁጥጥር ሥር ዋሉ

የስቱትጋርት ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, AP

ቅዳሜ መስከረም 5/2015 ዓ.ም. በጀርመኗ ስቱትጋርት ከተማ የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

ሁከቱ የተፈጠረው የኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች በከተማዋ የባሕል ፌስቲቫል ማዘጋጀታቸውን ተከትሎ ተቃዋሚዎች ሥነ-ስርዓቱን ለማወክ ሁከት ከፈጠሩ በኋላ ነው።

ተቃዋሚዎቹ በጀርመን ፖሊስ አባላት ላይ ጥቃት አድርሰው በአጠቃላይ 26 የፖሊስ አባላት የተጎዱ ሲሆን ከስድስት የማያንሱ አባላት ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

የስቱትጋርት ከተማ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ወደ ስፍራው የተሰማራው ፖሊስ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያልጠበቀው ከባድ አመጽ አጋጥሞታል ብለዋል።

ፖሊስ ባወጣው መግለጫ ተቃዋሚዎቹ በዱላ፣ በሚስማር፣ በብረት፣ በጠርሙስ እና በድንጋይ የጀርመን ፖሊስ አባላት ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።

ሁከቱን ተከትሎ 228 ኤርትራውያን በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተገለጸ ሲሆን በሁከቱ ምን ያክል ኤርትራውያን ጉዳት እንደደረሰባቸው እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

ቅዳሜ ከሰዓት የባሕል ፌስቲቫሉ ከመጀመሩ በፊት ወደ 200 የሚጠጉ ተቃዋሚዎች የፌስቲቫል ተሳታፊዎች እና የፖሊስ አባላት ላይ ድንጋይ፣ ጠርሙስ እና ሌሎች ነገሮችን መወርወር መጀመራቸውን ኤፒ ዘግቧል።

በጀርመኗ ስቱትጋርት ከተማ የተከሰተው ሁከት የአገሪቱን ባለስልጣናት አስቆጥቷል።

የስቱትጋርት ከተማ ከንቲባ በጀርመን በሌላ አገር ጉዳይ ሁከት እንዳይፈጠር ጥብቅ እርምጃ መውሰድ አለብን ብለዋል።

ከቅርብ ግዜ ወዲህ የኤርትራ የባሕል ፌስቲቫል ዝግጅትን ምክንያት በማድረግ በኤርትራውያን መካከል በአውሮፓ እና አሜሪካ ከተሞች ግጭት ሲፈጠረ ማየት እየተለመደ መጥቷል።

በቅርብ ወራት ብቻ በጀርመን ጊሰን ከተማ፣ በስዊድን፣ በኖርዌይ፣ በካናዳ ቶሮንቶ እና በእስራኤል ቴል-አቪቭ ብዙዎችን ለጉዳት የዳረጉ ግጭቶች ተከስተዋል።

የባሕል ፌስቲቫሉን የሚቃወሙት ሥነ-ስርዓቱ "ለአምባገነኑ የኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት ገንዘብ ማሰባሰቢያ ነው" ይላሉ።

በጊሰን ከተማ ከአንድ ዓመት በፊት ከፌስቲቫሉ መካሄድ ጋር በተያያዘ ሁከት ተፈጥሮ በርካታ ሰዎች ተጎድተው ነበር።

የጀርመን ዜና ወኪል ዲፒኤ ከአንድ ዓመት በፊት በነበረው ሁከት 100 የፌስቲቫል አዘጋጆች እና ጎብኚዎች ላይ ጉዳት ደርሶ እንደነበር ዘግቧል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በእስራኤል መዲና ቴል አቪቭ የተከሰተው ሁከት የአገሪቱን መንግሥት ያበሳጨ ሲሆን ጠቅላይ ሚንስትር ኔታኒያሁ አፍሪካውያን ስደተኞች በሙሉ ‘በአስቸኳይ’ ከእስራኤል ለማባረር የሚያስችል እቅድ እንዲወጣ ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር።

በቴል አለቪቭ በነበረው ሁከት በርካቶች ላይ ጉዳት ደርሶ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በቴል አለቪቭ በነበረው ሁከት በርካቶች ላይ ጉዳት ደርሶ ነበር።

ኤርትራውያኑ ቅዳሜ ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም. በቴል አቪቭ ከባድ ሁከት ከፈጠሩ በኋላ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በሁከቱ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ ኤርትራውያን በአስቸኳይ ከአገር እንዲባረሩ እፈልጋለሁ ያሉ ሲሆን ሁከቱን በተመለከት ውይይት ለማድረግ በጠሩት ልዩ የሚንስትሮች ስብሰባ ላይ በሁከቱ “ተሳታፊ የነበሩትን ወደ አገራቸው መመለስን ጨምሮ በአመጸኞቹ ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ እንፈልጋለን” ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኤርትራ መንግሥት በእስራኤል የባሕል ፌስቲቫል ላይ ሁከት የፈጠሩት እንደ ሞሳድ ባሉ የደኅንነት ተቋማት የተደገፉ ናቸው ብሎ ነበር።

የኤርትራ ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር ማክሰኞ ነሐሴ 30/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ "የእነዚህ ድርጊቶች ዋነኛ ዓላማ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኤርትራውያን ለአስርት ዓመታት የዘለቀውን ማንነታቸው እና አገራዊ ትስስራቸውን ለማጠናከር የሚያደርጉትን ጥረት ማደናቀፍ ነው" ብሏል።

በቅርብ ዓመታት ጀርመን ከፍተኛ ቁጥር ላለቸው ኤርትራውያን ስደተኞች ጥገኝነት የሰጠች ሲሆን፣ ይህም በአውሮፓ ሕብረት ካሉ አፍሪካውያን ማሕብረሰቦች ኤርትራውያኑን ከቀዳሚዎቹ ተርታ አስልፏቸዋል።

በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኤርትራ መንግሥት በዜጎቹ ላይ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጽም ይገልጻሉ።

በዚህም ምክንያት በኤርትራ ያለውን የፖለቲካ እና የእምነት ነጻነት ጭቆና እንዲሁም የጊዜ ገደብ የሌለውን አስገዳጅ የብሔራዊ አገልግሎት በመሸሽ በርካቶች ኤርትራውያን አገር ጥለው ይሰደዳሉ።