ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ብቻ ያላቸውን ከ300 በላይ መምህራን ከማስተማር አገደ

የፎቶው ባለመብት, Jigjiga University
ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ፤ ከተቀጠሩ ከአምስት ዓመት በላይ የሆናቸው እና የሁለተኛ ዲግሪ የሌላቸው ከ300 በላይ መምህራኑ በ2017 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን “ምንም አይነት ኮርስ” እንዳይሰጡ ውሳኔ ማሳለፉን አስታወቀ።
ዩኒቨርስቲው በመምህራኑ ላይ ወርሃዊ ደመወዝ እንዳይከፈላቸው እግድ አስተላልፎ የነበረ ቢሆንም ይህንን ውሳኔውን ለጊዜው መቀልበሱን ገልጿል።
ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው፤ የመጀመሪያ ዲግሪ ኖሯቸው የተቀጠሩ መምህራን፤ የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ያስተላለፋቸውን ተደጋጋሚ ጥሪዎች ተቀብለው ወደ ትምህርት ባለመግባታቸው እንደሆነ የዩኒቨርሰቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብዲ አህመድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ሁለተኛው ትውልድ” ተብለው ከሚጠሩ 15 ዩኒቨርሰቲዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ጅግጅጋ ዩኒቨርሰቲ ከ1,400 መምህራን ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 800 ገደማው የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው እንደሆኑ ዶ/ር አብዲ አስረድተዋል። ዩኒቨርስቲው ካሉት አጠቃላይ መምህራን ውስጥ 350 ያህሉ የመጀመሪያ ዲግሪ ብቻ ያላቸው እንደሆኑ ገልጸዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪ ካላቸው መምህራን ውስጥ በትምህርት ላይ ያሉት “የተወሰኑት” እንደሆኑ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አስረድተዋል።
“ረዳት ምሩቅ” በሚል ደረጃ የሚቀጠሩት የመጀመሪያ ደረጃ መምህራን ዩኒቨርሲቲውን በመምህርነት በተቀላቀሉ “በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ” የድረኅ ምረቃ ትምህርት ተከታትለው ሁለተኛ ዲግሪ እንዲይዙ እንደሚጠበቅ አብራርተዋል።
በ2010 ዓ.ም. የወጣው የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት “የመምህራን ምልመላ፣ ቅጠር እና ልማት መመሪያ”፤ ረዳት ምሩቃን የድኅረ ምረቃ ትምህርት ማግኘት እንዳለባቸው ያመለክታል።
በዚህ መልኩ የሚቀጠሩት መምህራን ዋነኛ ሥራቸው “ኮርስ ማስተማር” መሆን እንደሌለበት ያስቀመጠው መመሪያው፤ ረዳት ምሩቃን ሥራቸው “ዋና መምህራንን መርዳት፣ የትምህርት ግብዓት መርጃዎችን ማዘጋጀት እንዲሁም የፈተና ወረቀቶችን ማረም” መሆን እንዳለበት ደንግጓል።
ረዳት ምሩቃኑ እነዚህን ተግባራት በሚያከናውኑባቸው ጊዜያት “ራሳቸውን ለድኅረ ምረቃ [ትምህርት] እያዘጋጁ መቆየት” እንዳለባቸው ያስረዳል። ይሁንና የመምህራን ብዙውን ጊዜ ዩኒቨርሲቲዎች በሚያጋጥማቸው የመምህራን እጥረት ምክንያት የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ረዳት ምሩቃን ኮርሶችን እንደሚሰጡ አንድ የትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች እንዲኖራቸው የሚፈለገው የመምህራን የትምህርት ደረጃ ምጣኔ 70 በመቶ ሁለተኛ ዲግሪ እና 30 በመቶ ፒ.ኤች.ዲ እንደሆነ የሚገልፁት ኃላፊው፤ ብዙውን ጊዜ ግን ይህንን ምጣኔ ማሳካት እንደማይቻል ገልጸዋል።
ካሉት አጠቃላይ መምህራን ውስጥ 25 በመቶ ገደማው የመጀመሪያ ዲግሪ ብቻ ያላቸው በሆኑበት ጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ፤ እነዚህ መምህራን “ከፍተኛ ይዘት የሌላቸውን ኮርሶች” እንዲያስተምሩ ሲያደርግ መቆየቱን አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር አብዲ ገልፀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Jigjiga University
ዩኒቨርሲቲው ከአራት ዓመት ገደማ በፊት ባደረገው እንቅስቃሴ “ከተቀጠሩ አምስት እና ከአምስት ዓመት በላይ የሆናቸው አብዛኞቹ መምህራን” በሁለት ዓመት ውስጥ ሁለተኛ ዲግሪ እንዲይዙ አድርጎ እንደነበር አስታውሰዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምረው ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ እና እየተከታተሉ ያሉ መምህራን እንዳሉ የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ “አንዳንዶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ግን እዚያው [ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ቀጠሉ” ሲሉ አሁንም የመጀመሪያ ዲግሪ ብቻ ስላላቸው መምህራን ተናግረዋል።
መምህራኑ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ላለመቀጠላቸው የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያነሱት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ “አንዳንድ መምህራን ሌላ ተደራቢ ሥራ አግኝተው መምህርነቱን እንደ ሁለተኛ ሥራ” መመልከታቸውም በምክንያትነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው እነዚህ መምህራን የድኅረ ምረቃ ትምህርት ያልጀመሩበትን ምክንያት በተመለከተ በተደጋጋሚ ስብሰባዎችን ቢጠራም “ሳይሳተፉ ቀርተዋል” ሲሉ ዶ/ር አብዲ ከስሰዋል።
“2017 ዓ.ም. ሊጀመር ሲል አንደኛ ዲግሪ ያላቸውን መምህራን ብቻ [ስብሰባ] ጠርተን ነበር። መጀመሪያ ላይ የመጡልን 11 መምህራን ብቻ ናቸው። ሁለተኛ ዕድል እንስጥ ብለን የዛሬ ሳምንት [ስብሰባ] ጠርተን ነበር። [ከ300 በላይ መምህራን] ውስጥ 48 መምህራን ነው የመጡት” ሲሉ መምህራኑን ወቅሰዋል።
መምህራኑ ሁለተኛ ዲግሪ አለመያዛቸውን እና የዩኒቨርሰቲው አመራር በጠራቸው ስብሰባዎች ላይም አለመካፈላቸውን ተከትሎ እየተጀመረ ባለው የ2017 ትምህርት ዘመን “ምንም ዓይነት ኮርስ እንዳይሰጡ” ረቡዕ መስከረም 22/2017 ዓ.ም. ውሳኔ መተላለፉን አስታውቀዋል።
“እነዚህ [መምህራን] መማርም ስለማይፈልጉ፤ በአንደኛ ዲግሪ ያለ መምህር አንድም ኮርስ እንዳይሰጥ [ወስነናል]። አንድ መምህር መጀመሪያ ስብሰባ ካልመጣ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። በተደጋጋሚ ስትጠራ ካልመጣ እርምጃ መውሰድ የሚቻልበት ሁኔታ ፖሊሲው ያስቀምጣል” ሲሉ የመምህራኑ ስብሰባ ላይም አለመገኘት ለውሳኔው አስተዋፆ እንዳለው አመልክተዋል።
መምህራኑ ከተላለፈባቸው የማስተማር እገዳ በተጨማሪ ደመወዝም እንዳይከፈላቸው ውሳኔ ተላልፎ እንደነበር ዶ/ር አብዲ ተናግረዋል። ምክትል ፕሬዝዳንቱ ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ለዩኒቨርሲቲው የሰው ኃብት ልማት ሥራ አመራር መምሪያ ዳይሬክቶሬት በጻፉት ደብዳቤ ይህንን ውሳኔ አሳውቀው ነበር።
ቢቢሲ የተመለከተው ይህ ደብዳቤ፤ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው መምህራን “በተደጋጋሚ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ ቢጠሩም በዚህ ውይይት ለመሳተፍ ፈቃደኛ ሆነው ባለመገኘታቸው ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ ደመወዛቸው እንዲታገድ ስል አሳውቃለሁ” ይላል።
ይሁንና ውሳኔው በተላለፈበት በአሁኑ ወቅት የመስከረም የደመወዝ መክፈያ ጊዜ በመድረሱ እና “በዚህ ጊዜ ደመወዝ ማቋረጥ ስለማይቻል” ዩኒቨርሲቲው ይህንን ውሳኔውን ለጊዜው መሻሩን ዶ/ር አብዲ አስታውቀዋል።
ከደመወዝ ጋር የተያያዘው ውሳኔ ቢሻርም የዩኒቨርስቲው አመራር ከኮሌጅ ዲኖች ጋር በመሆን መምህራኑን በተመለከተ ተወያይቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብዲ ለቢቢሲ ተናግረዋል።












