ከናኦሚ ግርማ ጋር ለቢቢሲ የዓመቱ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋችነት ክብር የሚፎካከሩት እነማን ናቸው?

የቢቢሲ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች ማን ልትሆን ትችላለች? ድምፅ መስጠት ተጀምሯል።
በዓለም ዙሪያ ያሉ እግር ኳስ ተመልካቾች ድምፃቸውን መስጠት ይችላሉ። የዘንድሮ ዕጩዎች ባርብራ ባንዳ፣ አይታና ቦንማቲ፣ ናኦሚ ግርማ፣ ካሮላይን ግራሀም ሀንሰን እና ሶፊያ ስሚዝ ናቸው።
በአውሮፓውያኑ 2015 የተጀመረው የቢቢሲ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች ሽልማት 10ኛ ዓመቱን ይዟል።
አድናቂዎች እስከ ጥቅምት 18/2017 ዓ.ም. ድረስ ድምፃቸውን መስጠት ይችላሉ። አሸናፊዋ ኅዳር 17/2017 ዓ.ም. ይፋ ትደረጋለች።
ለዘንድሮው ሽልማት የታጩት አምስቱ እግር ኳስ ተጫዋቾች በዘርፉ ባለሙያዎች የተመረጡ ናቸው።
ናኦሚ ግርማ

- ዕድሜ፡ 24
- የምትጫወትበት ቦታ፡ ተከላካይ
- ቡድን፡ ሳን ዲየጊ ዌቭ እና የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ቡድን
የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ኤማ ሀየስ “እስከዛሬ ካየኋቸው ተከላካዮች ምርጧ ናት” ስትል ናኦሚን ትገልፃታለች። ለአገሯ እና ለክለቧ የጀርባ አጥንት ናት።
ከኢትዮጵያውያን እናት እና አባት የተወለደችው የ24 ዓመቷ ናኦሚ የአሜሪካ ምርጥ ተጫዋች ተብላ የተመረጠች የመጀመሪያዋ ተከላካይ ናት።
የዩናይትድ ስቴትስ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የኦሊምፒክ ወርቅ ባለቤት ሲሆን እያንዳንዱን ደቂቃ ተጫውታለች። የኋላ ደጀን የምትባለው ናኦሚ ኳስ በመቆጣጠር እና በመሪነት ችሎታዋ አድናቆት ይጎርፍላታል።
ምስጋና ለኦናሚ ግርማ ይሁንና የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን በ2024 የፓሪስ ወርቅ፣ ኮንካካፍ ጎልድ ዋንጫ እና ሺ ቢሊቭስ የተባለው ዋንጫ ባለቤት መሆን ችላለች።
ናኦሚ በክለብም ዋንጫ አልተለያትም። ቡድኗ ሳን ዲየጎ ዌቭ የኤንደብሊውኤስኤል እና የቻሌንጅ ዋንጫዎችን አንስታለች።
ከናኦሚ አንደበት
በፓሪስ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት መሆን ምን ይመስላል?
“በጣም ልዩ ነበር። አሠልጣኝ ቀይረን፤ እንደዚያ ተጫውተን ባለድል መሆናችን በጣም አስደስቶናል” ትላለች ናኦሚ።
ናኦሚ እናት እና አባቷ ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ስላሳደረባት በጎ ተፅዕኖም ተጠይቃለች።
“ወላጆቼ ኢትዮጵያ ነው የተወለዱት። ገና በ20ዎቹ ዕድሜያቸው ነው ወደ አሜሪካ የመጡት። አባቴ ስደተኛ ነበር። በሱዳን አቋርጦ ነው ካሊፎርኒያ የገባው። እናቴ ደግሞ ለትምህርት ነው ወደ ዩኤስ የመጣችው” ስትል ታስረዳለች።
“ባህሉ፣ ምግቡ፣ ቋንቋው፤ ሁሉም ነገር ልዩ ነው። ካሊፎርኒያ ሳን ሆዜ ሳድግ ማኅበረሰቡ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክቶልኛል። እግር ኳስ መጫወት የጀመርኩትም እዚያ ነው።”
ናኦሚ ተከላካይ መስመር ላይ መጫወቷን ትወደዋለች። የክለብ እና የብሔራዊ ቡድን አጋሮቿ በጋራ በመጫወት ታምናለች ይሏታል።
የወቅቱ የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ኤማ ሀየስ ስለናኦሚ ግርማ ተናግራ አትጠግብም።
“እስከዛሬ ካየኋቸው ተከላካዮች ምርጧ ናት። ሁሉንም ነገር ተክናለች። በተጠንቀቅ ነው የምትጠብቀው፣ ጠንካራ ተከላካይ ናት፣ ቡድኑን መምራትም ላይ ጎበዝ ናት” ትላለች።
ለቢቢሲ ስፖርት ምርጥ ሴት ተጫዋች ተብላ የታጨችው ሌላኛዋ አሜሪካዊት ሶፊያ ስሚዝ “በዓለማችን ምርጧ ተከላካይ ናት። የቡድናችን የጀርባ አጥንት ናት” ስትል ናኦሚን ታሞካሻታለች።

ስለናኦሚ አንዳንድ እውነታዎች
- ናኦሚ ገና ልጅ ሳለች አባቷ ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች ባቋቋመው ክለብ ውስጥ ትጫወት ነበር
- ከእግር ኳስ በተጨማሪ ቅርጫት ኳስ እየተጫወተች ነው ያደገችው። ጂምናስቲክም ትሠራ ነበር
- ኮመን ጎል ለተባለ በአእምሮ ጤና ላይ የሚሠራ በጎ አድራጊ ድርጅት አባል ነበረች
- በ2024 የአሜሪካ ዓመቱ ምርጥ ተጫዋች እና የሊጉ ምርጥ ተከላካይ ሆና ተመርጣለች። የፓሪስ ኦሊምፒክ ወርቅ ባለቤትም ናት
ባርብራ ባንዳ

የ24 ዓመቷ ዛምቢያዊቷ ባርብራ ባንዳ ለኦርላንዶ ፕራይድ ነው የምትጫወተው።
በቶኪዮ ኦሊምፒክ 2021 ብቃቷን ያሳየችው ባርብራ በ2023 የሴቶች የዓለም ዋንጫም ድንቅ ነበረች።
የባርብራ ስም ጎልቶ የወጣው ባለፈው መጋቢት ኦርላንዶ ፕራይድ ከቻይናው ሻንግሃይ ሼንግሊ በ740 ሺህ ዶላር ሲያስመጣት ነው።
ከሀገሯ ልጅ ሬቸል ኩንዳናንጂ በመቀጠል ሁለተኛ ውድ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች ናት። በአሜሪካ የሴቶች ሊግ ኤንደብሊውኤስኤል ድንቅ 13 ግቦች በማስቆጠር ብቃቷን እያሳየችም ትገኛለች።
በኦሊምፒክ ጨዋታዎች በተከታታይ ሀት-ትሪክ በመሥራት የመጀመሪያዋ ስትሆን፤ በኦሊምፒክ ታሪክ ከፍተኛዋ አፍሪካዊት ግብ አስቆጣሪ ናት።
አይታና ቦንማቲ

የ26 ዓመቷ ስፔናዊት ለባርሴሎና ነው የምትጫወተው።
ከባርሴሎና ጋር በአንድ የውድድር ዘመን አራት ዋንጫዎችን ከማንሳቷም በላይ በሁሉም ውድድሮች 19 ግቦችን ማስቆጠር ችላለች።
ቦንማቲ የ2024 የባለን ደኦር ሽልማት አሸናፊ ናት። ያለፈውን ዓመት ሽልማትም ማንሳቷ ይታወሳል።
በ2023 ስፔን የዓለም ዋንጫ ስታነሳ የቡድን የፊት መስመር ኮከብ ነበረች። በአውሮፓ ኔሽንስ ሊግ ፍልሚያም ሀገሯ ስፔን ዋንጫ እንድታነሳ አግዛለች።
ካሮላይን ግራሃም ሀንሰን

የ29 ዓመቷ የክፍን መስመር ተጫዋች ያልተዘመረላት ትባላለች።
ለክለቧ ባርሴሎና እና ለሀገሯ ኖርዌይ የምትሰለፈው ሀንሰን ባለፈው የውድድር ዘመን ከባርሴሎና ጋር ብዙ ድሎች አጣጥማለች።
ባርሴሎና በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ የውድድር ዘመን አራት ዋንጫዎች ስታነሳ በ40 ጨዋታዎች ለ60 ጎሎች ምክንያት ሆናለች።
በ21 ጎሎች የሊፍ ኤፍ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆና ስትሆን በሱፐርካፕ ፍልሚያ ሦስት ግቦች ማስቆጠር ችላለች።
ሶፊያ ስሚዝ

የ24 ዓመቷ አሜሪካዊት አጥቂ ለፖርትላንድ ቶርንስ ነው የምትጫወተው።
ዩናይትድ ስቴትስ በፓሪስ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያስ ባለቤት ትሆን የቡድኑ የፊት መስመር መከታ ነበረች። በውድድሩ ሦስት ግቦች ማስቆጠረም ችላለች።
በሩብ ፍፃሜው በጭማሪ ሰዓት ጀርመን ላይ ያስቆጠችው ግብ እጅግ ወሳኝ ነበር።
በአሜሪካ የሴቶች ሊግ ኤንደብሊውኤስኤል በ11 ግቦች ያለፈው ዓመት ኮከብ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ነው ያጠናቀቀችው።












