ዶናልድ ትራምፕ ማሸነፋቸውን ተከትሎ የቢትኮይን ዋጋ አሻቅቦ 80 ሺህ ዶላር ገባ

ቢትኮይን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቢትኮይን ዋጋ እስከዛሬ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጭማሪ አሳይቷል

ባለፈው ሳምንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ የቢትኮይን ዋጋ እስከ ዛሬ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከ80 ሺህ ዶላር በላይ ገብቷል።

ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን ከማሸነፋቸውም በላይ ሪፐብሊካኖች የሕግ መወሰኛውን ምክር ቤት የበላይነት የጨበጡ ሲሆን፣ ኮንግረሱን በበላይነት ለመቆጣጠር ከጫፍ እንደደረሱ እየተሰማ ባለበት ወቅት ነው የቢትኮይት ዋጋ ያሻቀበው።

ተመራጩ ፕሬዝደንት በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ዩናይትድ ስቴትስን “የፕላኔታችን የክሪፕቶከረንሲ መዲና አደርጋታለሁ” ሲሉ ቃል መግባታቸው አይዘነጋም።

የዓለማችን ትልቁ ክሪፕቶከረንሲ የሆነው ቢትኮይት በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት ብቻ ዋጋ ከ80 በመቶ በላይ ጨምሯል።

ሌሎች እንደ ዶጅኮይን ያሉ ክሪፕቶከረንሲዎችም ዋጋቸው ከፍ እያለ ነው። የትራምፕ ቀኝ እጅ የሆነው ኢላን መስክ ዶጅኮይን በስፋት ያስተዋውቃል።

ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ለዲጂታል መገበያያዎች የተመቻቸ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል። ይህን ተከትሎ በክሪፕቶ ኢንዱስትሪ ላይ የተጣለው ቁጥጥር ይላላል የሚል እምነት አለ።

አክለውም ፕሬዝደንት ሆነው ከተመረጡ የመጀመሪያ ሥራቸው የሚሆነው የወቅቱን የሴኪዩሪቲስ ኤንድ ኤክስቼንጅ (የአክሲዮን ገበያ ኮሚሽን) ኃላፊ ጋሪ ጌንስለርን እንደሚያሰናብቱ ተናግረዋል።

ጌንስለር በጆ ባይደን የተሾሙት በአውሮፓውያኑ 2021 ሲሆን፣ መሥሪያ ቤቱን እየመሩ ሳለ በክሪፕቶ እንዱስትሪ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር አድርገዋል ይባላሉ።

“የትራምፕ አስተዳደር ክሪፕቶ ላይ የሚደረገውን ከፍተኛ ቁጥጥር የማያላላ ከሆነ ኢንዱስትሪው ይጎዳል” ይላሉ የዲጂታል ገበያ ተንታኙ ማት ሲምፕሰን።

ትራምፕ የገበያውን ቁጥጥር የሚያላሉ ከሆነ ግን የቢትኮይን ዋጋ 100 ሺህ ሊደርስ ይችላል ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

ዶናልድ ትራምፕ የግብር ክፍያን መቀነስ እና ቁጥጥርን ማላላት ብለው ለነጋዴዎች ቃል መግባታቸውን ተከትሎ ምርጫውን ካሸነፉ በኋላ መዋዕለ ንዋያቸውን የሚያፈሱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ ተዘግቧል።

የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት የሦስቱን የመንግሥት ክንፎች በበላይነት የሚቆጣጠሩ ከሆነ የትራምፕ ሐሳብ ተግባራዊ እንደሚደረግ ይጠበቃል። ሴኔቱ እና ኮንግረሱ በሪፐብሊካን ቁጥጥር ሥር ሆነ ማለት ትራምፕ አጀንዳቸውን ለማስፈፀም አይከብዳቸውም ማለት ነው።

ትራምፕ ምርጫውን ካሸነፉ በኋላ የአሜሪካ ዶላር እና ቦንድ ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል።

ክሪፕቶከረንሲ ምንድን ነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዓለም ባለፉት ክፍለ ዘመናት በከፍተኛ የቴክኖሎጂ እመርታ ውስጥ እያለፈች በርካታ ነገሮች ተቀያይረው በእጅጉ ዘምነዋል። ከእነዚህም መካከል ደግሞ ለግብይት የሚውለው የገንዘብ ገጽታ በእጅጉ ተቀይሯል።

ለዚህ ደግሞ የማይጨበጡት ሃሳባዊ ዲጂታል ገንዘቦች ለምርት እና ለአገልግሎት መገበያያነት ማዋል ከጀመሩ ከረምረም ብለዋል።

ከዚህ አንጻር 21ኛው ክፍለ ዘመን ለዓለም ካስተዋወቃቸው የዘመናዊነት ውጤቶች እና ቃላት መካከል በተቋማት እና በአገራት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ደጋግመው የሚያነሱት እና ብዙ እየተባለለት ያለው “ክሪፕቶከረንሲ” አንዱ ነው።

ኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ክሪፕቶከረንሲን እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፤ የገንዘብ ልውውጦችን ደኅንነት የሚያረጋግጥ፣ የተጨማሪ አሃዶችን መፈጠርን የሚቆጣጠር እና ገንዘብ መተላለፉን የሚያረጋግጥ ጠንካራ ክራፕቶግራፊ የሚጠቀም መገበያያ እንዲሆን ተደርጎ የተቀረጸ ዲጂታል ገንዘብ።

ከላይ የተጠቀሰውን መስፈርት የሚያሟሉ በርካታ ዓይነት ክሪፕቶካረንሲዎች አሉ። በስፋት ከሚታወቁት መካከል ቢትኮይን፣ ኤቴሪያም፣ ሪፕል እና ቢትኮይን ካሽ የሚባሉት ከበርካታ ክሪፕቶካረንሲዎች መካከል ሊጠቀሱ ይችላሉ።

ቢትኮይን ማለት በቀላል ቋንቋ፤ ዲጂታል + ገንዘብ + መገበያያ በማለት ማጠቃለል ይቻላል።

ይህ መገበያያ በኪሳችን ተሸክመን እንደምንዞረው የወረቀት ገንዘብ ወይም ሳንቲም ሳይሆን በበይነ መረብ ላይ የሚቀመጥ ዲጂታል ገንዘብ ነው።

ሌላው የቢትኮይን እና የተቀሩት የክሪፕቶከረንሲዎች ልዩ ባህሪ በመንግሥታት እና በባንኮች አለመታተማቸው እንዲሁም ቁጥጥር አለመደረጉ ነው።

ቢትኮይን የሚፈጠረው 'ማይኒንግ' በሚባል ሂደት ነው። በመላው ዓለም በኔትወርክ በተሳሰሩ ኮምፒውተሮች አማካኝነት ቁጥጥር ይደረግበታል።

ቢትኮይንን የፈጠረው ግለሰብ/ቡድን በዓለም ላይ 21 ሚሊዮን ቢትኮይኖች ብቻ እንዲፈጠሩ ገደብ እንዳስቀመጠ/ጡ ይታመናል።

የብሎክቼይን መረጃዎች እንደሚያሳዩት እስካሁን ከ17 ሚሊዮን ያህል ቢትኮይኖች ማይን ተደርገዋል ተብሎ ይታመናል።