የትራምፕ ማሸነፍን በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውን እንዴት ይመለከቱታል? ለኢትዮጵያስ ምን ይዞ ይመጣል?

ትራምፐ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከአራት ዓመታት በፊት በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የአፍሪካ አገራትን በማንቋሸሽ እና በጸያፍ ዘለፋዎች በመንቀፍ ይታወቃሉ ትራምፕ።

“የአሜሪካን ታላቅነት በድጋሚ ለማምጣት” በተደጋጋሚ የሚምሉት ትራምፕ ፀረ-ስደተኝነት፣ፀረ- ሙስሊም የሆኑ ንግግራቸው እና አቋማቸውን ደጋግመው አንጸባርቀዋል።

ከሥልጣን ወርደው ለሁለተኛ ጊዜ በመመረጥ ታሪክ የሠሩት ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ለመሆኑ ትራምፕ ማሸነፋቸውን ኢትዮጵያውያን እንዴት ተመለከቱት?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሪፐብሊካኑ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የአሜሪካ የምርጫ ውጤት በይፋ ሳይገለጽ ነበር።

“በምርጫ ድልዎት እና ወደ ሥልጣን በመለለስዎ እንኳን ደስ አለዎት ማለት እፈልጋለሁ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኤክስ ገጻቸው ላይ መልዕክታቸውን አስፍረው ነበር።

አክለውም “በእርስዎ የሥልጣን ዘመን የሁለቱን አገራት ግንኙነት በበለጠ ለማጠናከር በጋራ የምንሠራበትን ጊዜ እጠብቃለሁ” ሲሉም በዚሁ መልዕክታቸው ላይ አትተዋል።

ትራምፕ ድላቸውን ቀድመው ማወጃቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንኳን ደስ አለዎት ማለታቸው የሚያስተላልፈው መልዕክት ይኖር ይሆን?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአሜሪካ የሕግ ባለሙያ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ፕሮፌሰር ሔኖክ ጋቢሳ ትራምፕ ምንድን ነው ፖሊሲያቸው? የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለማቸውስ? የሚለውን አገራት የራሳቸውን ትንተና እንደሚሠሩ ይጠቅሳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሥልጣን የቆዩባቸው የባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ አራቱ በዲሞክራቶች የሥልጣን ዘመን እንደሆነ ያወሳሉ።

ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ደም አፋሳሹ የትግራይ ጦርነት ምክንያት በተፈጸሙ ጥሰቶች በርካታ ማዕቀቦች በአሜሪካ መጣላቸው ከዴሞክራቶች ጋር ያለው ግንኙነት መሻከር እንደ ምክንያትነት ከሚጠቅሷቸው መካከል ናቸው።

ከእነዚህም ውስጥ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በትግራይ ጦርነት ላይ ጥሰቶችን ፈጽመዋል የተባሉ አካላት ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ መፈረማቸው ይታወሳል።

ማዕቀቡ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የኤርትራ መንግሥት፣ የአማራ ክልል አስተዳደር እና የህወሓት አመራሮችን ተጠያቂ የሚያደርግ እንደሆነም ተገልጿል።

ዕቀባው ግጭቱ እንዲራዘም አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትን ያደናቀፉ፣ ተኩስ አቁሙን የተከላከሉ በቀጥታ ተጠያቂ የሆኑ ወይም ተባባሪዎቻቸው ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ባይደን በጊዜው አስታውቀው ነበር።

የምጣኔ ሀብት እና የደኅንነት እገዛ እንዲቋረጥ፣ ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡ የመከላከያ ወታደራዊ ንግዶች ላይ ገደብን አሜሪካ የጣለች ሲሆን፣ በተጨማሪም በባለሥልጣናት ላይ የጉዞ እቀባ ተጥሎ ነበር።

ባለፈው ዓመት ጳጉሜ ወርም ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣል የሚያስችለውን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲራዘም መወሰናቸው አስታውቀዋል።

ሌላኛው የአሜሪካ መንግሥት ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገራት የዘረጋው ከቀረጥ ነጻ ዕድል (አጎዋ) ተጠቃሚ የነበረችው ኢትዮጵያ እየተካሄደ በነበረው ጦርነት ሳቢያ ከተጠቃሚነት ውጪ እንድትሆን መደረጓ ይታወሳል።

በጦርነቱ ወቅት የሁለቱ አገራት ግንኙነት ሻክሮ የነበረ ሲሆን፣ አሜሪካም በጦርነቱ የተፈጸሙ የጦር ወንጀሎችን በመንቀስ ስታወግዝ ቆይታለች።

ባለፉት አራት ዓመታት የሥልጣን ቆይታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ከአሜሪካ ዴሞክራቶች ጋር በነበራቸው ግንኙነት “በመከራ እና በሰቆቃ” እንዳሳለፉ ፕሮፌሰር ሄኖክ ያስረዳሉ።

“ስለዚህ የዲሞክራቶች ከዋይት ሐውስ መውጣት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት አዲስ መስመር ወይም አዲስ ዕድል የሚያመጣ ሊሆን ይችላል” ብለው ሊያስቡ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

የትግራይ ጦርነት ቢቋጭም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ውስጥ ያሉ ግጭቶች የቀጠሉ ሲሆን፣ የትራምፕ ፖሊሲ ይህንን አስመልክቶ ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው የሚታይ ይሆናል።

ትራምፕ በአፍሪካ ቀንድስ ምን ዓይነት ፖሊሲዎችን ይከተሉ ይሆን?

በአፍሪካ ቀንድ ያለው ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጋጋለ እየመጣ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ እንዲሁም በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል ውጥረቶች ነግሰዋል።

ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል።

በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት ለዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር ስትወዛገብ የነበረችው ግብፅ ከሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት በመፈራረም ለሶማሊያ የጦር መሳሪያዎችን እየላከች ትገኛለች።

እንዲሁም ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ወታደሮቿን ያዋጣችበት የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) የጊዜ ቆይታ ሲያበቃም ግብፅ በሶማሊያ ወታደሮቿን በሰላም አስከባሪነት ታሰማራለች እየተባለ ነው።

ከዚህ አንጻር የአሜሪካ ሚና በተለይ ደግሞ የትራምፕ ፖሊሲ ምን ሊሆን ይችላል?

ትራምፕ በአፍሪካ ቀንድ የተለየ ፖሊሲ ሊከተሉ የሚችሉት በግብፅ ምክንያት እንደሆነ ፕሮፌሰሩ ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለዘመናት ፈታኝ በሚባል ግንኙነት ውስጥ ቢያሳልፉም ግብፅ በአሁኑ ወቅት የሰላም አስከባሪ ሚናውን ልጫወት እያለች ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ውጥረቱ መባባሱን የሕግ ባለሙያው ያስረዳሉ።

“ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከግብፅ ጋር የተለየ ፍቅር ባይኖራቸውም ለግብፅ የተለየ ስፍራ ይሰጧታል። በእስራኤል እና በተለይም በአረቡ አገራት መካከል ያለውን አጠቃላይ ሰላም ለማምጣት ግብፅ ትልቅ ሚና ስለምትጫወት ይፈልጓታል” ይላሉ ፕሮፌሰር ሄኖክ።

በተለይም ግብፅ ወደ እስራኤል፣ ዌስት ባንክ፣ ጋዛ ወደ አፍሪካ ለመግባት መዳረሻ ከመሆኗ አንጻር “ለትራምፕ ግብፅን ማሳዘን፣ መጉዳት፣ ሊከብድ” እንደሚችል ፕሮፌሰር ሄኖክ ያስረዳሉ።

አክለውም “ግብፅን ከመቆጣት ኢትዮጵያን መቆጣት ለትራምፕ በጣም ይቀላቸዋል። አል ሲሲን ከማሳዘን ዐቢይን ማሳዘን ቀላል ነው” ይላሉ።

የትራምፕ መመረጥ በአሜሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንስ ምን ፋይዳ አለው?

ካማላ ሃሪስ ሲኤንኤንን ጨምሮ የበርካታ መገናኛ ብዙኃን ድጋፍ ነበራት የሚሉት በኒውዮርክ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት አበባየሁ ይልማ ነገር ግን ትራምፕ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝባዊ ድምጽ (ፖፑላር ቮት) አግኘተው ለማሸነፍ በቅተዋል ይላሉ።

ትራምፕ የማጭበርበር ክሶችን ጨምሮ በሌሎች ክሶች መካከል ማሸነፋቸው ለዲሞክራቶች ያስተላለፈው መልዕክት እንዳለም ነው ተባባሪ ፕሮፌሰሩ የሚገልጹት።

ትራምፕ በምርጫው ማሸነፋቸውን ከ50 በመቶ በበለጠ ይጠበቁት እንደነበር የሚናገሩት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ “ካማላ ሃሪስ ብታሸንፍ ደስ ይለኝ ነበር” ይላሉ።

ትራምፕ ለማሸነፍ ቃል የገቧቸው ስደተኞችን የመቆጣጠር፣ የምጣኔ ሀብት እና ሌሎች ጉዳዮችን ለመመረጣቸው እንደ ምክንያትነት ይጠቅሷቸዋል።

ትራምፕ ስደተኞችን በጅምላ ለማባረር በዘመቻቸው ላይ ቃል የገቡ ቢሆንም ይህ ሊሆን የማይችልባቸው ሕጋዊ ማነቆዎችን ይጠቅሳሉ።

በድንበሮች በኩል የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ ትልልቅ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚችሉም ይናገራሉ።

በአሜሪካ የፒኤችዲ ተማሪው አሸናፊ ብሩ በበኩሉ በቀጣዮቹ አራት ዓመታት መልካም ነገሮችን እንደሚጠብቅ ይገልጻል።

“በጣም ከፍተኛ ደስታ ነው የተሰማኝ። የአሜሪካ ኢኮኖሚ ተቀዛቅዟል፤ የዋጋ ግሽበት አለ። የትራምፕ አስተዳደር ይሄንን ይቀይረዋል ብዬ አስባለሁ። የምርጫ ውጤቱ በታወቀ በሰዓታት ውስጥ የአክስዮን ገበያው የማንሰራራት አዝማሚያ አሳይቷል” ብሏል።

እንደ አሸናፊ ከሆነ ትራምፕ በአገሪቱ ያለውን ግሽበት በመቆጣጠር ዓለም አቀፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሰላምን በማምጣት እንዲሁም እውነተኛ ድርድሮችን በማድረግ “የአሜሪካን ኢኮኖሚ ያነቃቃዋል ብዬ አስባለሁ” ይላል።

በሜክሲኮ በኩል ወደ አሜሪካ ለመግባት ለሚሞክሩ ስደተኞች ስጋት ሊሆን እንደሚችል የሚጠቅሰው አሸናፊ ይህም ቢሆን “አንድ አገር ድንበር ከሌላት አገር አትሆንም። ድንበሯን መጠበቅ ያስፈልጋታል። ከዚያ በኋላ በሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ለሌላውም ይተርፋል” ይላል

ወሳኝ ግዛት ከሆኑት አንዷ በሆነችው ዊስኮንሰን ነዋሪ የሆነው የሻምበልም በትራምፕ መመረጥ ደስተኛ ነው።

“ትራምፕ ስላሸነፈ ደስ ብሎኛል። የእኔ ድምጽም ቦታ አግኝቷል። በዓለም ላይ ጦርነቶች ቆመው ሰላም ማየት እፈልጋለሁ። የኑሮ ውድነት ከፍ ብሏል እሱ ተስተካክሎ አራት ዓመቱን በተረጋጋ ሁኔታ እንደማሳልፍ እጠብቃለሁ” ብሏል።

ትራምፕ ለምን አሸነፉ?

የዋጋ ንረት፣ የኑሮ ውድነት፣ የኢኮኖሚው ማሽቆልቆል በባለፉት ዓመታት ውስጥ የታየ እንደሆነ የሚናገሩት ፐሮፌሰሩ ትራምፕ ከመፍትሄ ይልቅ ችግሮቹን ነቅሰው በማውጣት የህዝቡን የልብ ትርታ ማዳመጥ እንደቻሉ ይጠቅሳሉ።

“በዚህም ነጥብ ማስቆጠር ችሏል” ይላሉ።

ሌኛው በትራምፕ የምርጫ ዘመቻዎች ላይ “የጅምላ ማባረሮችን” የሚያበረታቱ መፈክሮች ደምቀው የታዩ ሲሆን ከተመረጡ በአገሪቱ ውስጥ ለመቆየት ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸውን ስደተኞች በጅምላ እንደሚያባርሩ እየተናገሩ ነበር።

ትራምፕ ምን ያህል ስደተኞች እንደሚባረሩ የተለያዩ መልሶች ቢሰጡም፣ በምክትል ፕሬዚዳንትነት አብረዋቸው በዕጩነት የቀረቡት ጄዲ ቫንስ “ከአንድ ሚሊዮን እንጀምር” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

ትራምፕ በድንበሮች በኩል የሚገቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች “የአገሪቷን ምጣኔ ኃብት እያዳከሙ ነው፤ ስራችሁን እየወሰዱባችሁ ነው” በሚሉ ማስፈራሪያ ነጥቦች በማንሳት የህዝቡን ቀልብ ይዘው እንደነበር ፕሮፌሰር ሔኖክ መታዘብ ችለዋል።

ሌላኛው ለማሸነፋቸው የሚጠቅሱት ምክንያቶች ዴሞክራቶች በባለፉት አራት ዓመታት የታዩባቸውን ክፍተቶችን መጠቀም ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ሄኖክ የሚጠቅሱት የአሜሪካ ህዝብ ሴት ፕሬዚዳንት ለማየት ተዘጋጅቷል በተለይም ጥቁር ሴት ፕሬዚዳንት የሚለውን እንደ ምክንያትነት ይጠቅሳሉ።

ከስምንት ዓመታት በፊት ሂላሪ ክሊንተን ከትራምፕ ጋር በተወዳደሩበት ወቅት “ተጨባጭ የሆኑ መፍትሄዎች” ቢያቀርቡም ሊመረጡ እንዳልቻሉ ይገልጻሉ።

“ላለመረጣቸው አንዱ ምክንያት ሴት በመሆናቸው ነው። በአሁኑ ምርጫ ካማላ ሴት ከመሆናቸው ባሻገር ጥቁርነትም አለባቸው። አሜሪካ ለሴት እና ለጥቁር ፕሬዚዳንት ዝግጁ ናት ወይ?” ሲሉ ይጠይቃሉ።