ሂዩማን ራይትስ ዎች መንግሥት "ከምርጫው አስቀድሞ" ጋዜጠኞች ላይ "የሚያደርገው አፈና አጠናክሯል" አለ

የፎቶው ባለመብት, Human Rights Watch/Eduardo Soteras
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ከመጪው አጠቃላይ "ምርጫ አስቀድሞ ገለልተኛ ድምጾች ላይ" የሚያደርገውን "አፈና አጠናክሯል" ሲል ከሰሰ። የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከነሐሴ አንስቶ "በርካታ ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን በዘፈደቀ" እንዳሰሩም አስታውቋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ተቋም፤ ይህንን ክስ ያቀረበው በአገሪቱ "የጨመረውን የጋዜጠኞች እስር" በተመለከተ ሰኞ መስከረም 12/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ነው። የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ላቲሺያ ባደር፤ "የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ገለልተኛ ዘገባን ለማፈን እንደ አዲስ ጥረት የጀመሩት ተጠያቂነት ለማስቀረት ነው" በማለት እንደተናገሩ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከነሐሴ ወር ጀምሮ "በዘፈቀደ በርካታ ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን በዘፈቀደ እንዳሰሩ" ሂዩማን ራይትስ ዎች በመግለጫው አስረድቷል። "ቢያንስ ስድስት" የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች "በዘፈቀደ መታሰራቸውን" የገለጸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ተቋም፤ ከእነዚህ ውስጥ "ከሰው እንዳይገናኙ የተደረጉ ወይም ያለ ክስ ለረዥም ጊዜ የታሰሩ" እንዳሉ አስታውቋል።
ይህ ሁኔታ "በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት ላይ ስጋት እንዳስከተለ" በመግለጫው ጠቅሷል። "በ2018 ከሚካሄደውን አገራዊ ምርጫ አስቀድሞ ሁሉም ሰው ነፃ እና ንቁ የሆነ መገናኛ ብዙኃን የማግኘት መብቱ ይበልጥ ወሳኝ ነው" ሲልም አሳስቧል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ በነሐሴ ወር ለተፈጸሙ እስሮች በቀዳሚነት የጠቀሰው ማሳያ፤ "በፌደራል ፖሊስ እና ሲቪል በለበሱ የጸጥታ ኃይሎች" ለእስር የተዳረጉትን ሦስት የሸገር ሬዲዮ ጋዜጠኞች ጉዳይ ነው።
የሬዲዮ ጣቢያው ዋና አዘጋጅ የሆነው አንጋፋው ጋዜጠኛ እሸቴ አሰፋ በዕለቱ የተለቀቀ ቢሆንም አርታኢዋ ትዕግስት ዘሪሁን እና ዘጋቢዋ ምንታምር ፀጋው ላለፉት 20 ቀናት በእስር ላይ ናቸው። ጋዜጠኞቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የሕክምና ባለሙያዎች ጥያቄዎችን በተመለከተ የሰሩት ዘገባ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ሸገር ሬዲዮ አርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ጋዜጠኞቹን በቁጥጥር ስር ያዋለው ፌደራል ፖሊስ "ያሰራጩት ዘገባ በሕግ የተከለከለ ይዘት ያለውና የሽብር ድርጊት ነው" በማለት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደገለጸም ይፋ አድርጓል። ፍርድ ቤት ጋዜጠኞቹ በ50 ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና እንዲለቀቁ ቢወስንም፤ መርማሪ ፖሊስ ይግባኝ በመጠየቁ ለዛሬ ሰኞ መስከረም 12 ቀጠሮ መሰጠቱንም ገልጾ ነበር።
ይህንን ሂደት በተመሳሳይ በመግለጫው ያብራራው ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ "የወታደር ዩኒፎርም ለብሰው ነበር በተባሉ ሰዎች" ከመኖሪያ ቤቱ የተወሰደውን የሪፖርተር ጋዜጣ ጋዜጠኛ ዮናስ አማረ ጉዳይንም አንስቷል። በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ ከሚገኘው ቤቱ በምሽት የተወሰደው ጋዜጠኛ ዮናስ፤ ለ10 ቀናት ያለበት ሳይታወቅ ከቆየ በኋላ መለቀቁን ሪፖርተር ጋዜጣ ማስታወቁ ይታወሳል።
በዚያው ወቅት ታስሮ በተመሳሳይ ቀን የተለቀቀው ጋዜጠኛ አብዱልሰመድ መሀመድም ያለበት ሳይታወቅ 11 ቀናትን አሳልፏል።
የሶማሌ ክልል ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ የሆነው ከድር መሀመድ እስማኤልም "የነዋሪዎች በክልሉ መንግሥት ላይ ቅሬታ ሲያቀርቡ የሚያሳይ ቪድዮ በጣቢያው ማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ ከለጠፈ በኋላ" በቁጥጥር ሰር መዋሉን ገልጿል። ጋዜጠኛው ነሐሴ 3/2017 ዓ.ም. አንድ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርቦ የነበረ ቢሆንም "ከአንድ ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ በድጋሚ አለመቅረቡን" አስረድቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ባለሥልጣናት ያሰሩት ወይም የያዙት ሰው በቁጥጥር ስር እንደዋለ ማሳወቅ እንዳለባቸው በዛሬው መግለጫው ጠቅሷል። ባለሥልጣናት የያዙት ግለሰብ "ነፃነቱን እንዲያጣ ስለመደረጉ እውቅና ለመስጠት ፈቃደኛ የማይሆኑ ከሆነ ወይም እጣ ፋንታውን ወይም ያለበትን የደበቁ ከሆነ [ጉዳዩ] አስገድዶ መሰወር" እንደሆነም በመግለጫው አስፍሯል።
መንግሥት በጋዜጠኞች እና መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚፈጽመው "ማስፈራሪያ" ከጥር ወር ወዲህ መጨመሩን የገለጸው መግለጫው፤ መጋቢት ወር ላይ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (ኢቢኤስ) "ሰባት ጋዜጠኞች ታስረው" እንደነበር ጠቅሷል።
ሚያዝያ ወር ላይ ደግሞ የአዲስ አበባ ፖሊስ የአዲስ ስታንዳርድ "ቢሮን መበርበራቸውን"፣ "ሁለት ጋዜጠኞችን ለጥያቄ" መውሰዳቸውን እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃኑን "በርካታ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች መያዛቸውን" ገልጿል። አዲስ ስታንዳርድ፤ የኤክትሮኒክስ መሳሪያዎቹ ሲመለሱ "ውስብስብ የክትትል ማልዌር" እንደተገጠመባቸው መግለጹንም አንስቷል።
ሰኔ ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር መስራች እና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ "ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት" በሚል ለቀናት ለእስር ተዳርጎ እንደነበር አስታውሷል።
የሂዩማን ራይትስ ዎች፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመገናኛ ብዙኃን ላይ እየደረሰ ያለው አፈና የጀመረው ሰፊ ትችት የቀረበበት የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ማሻሻያ ከጸደቀ በኋላ እንደሆነ በመግለጫው ጠቅሷል። ማሻሻያው ከዚህ ቀደም ለመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ቦርድ ተሰጥተው የነበሩ ኃላፊነቶች በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ለሚሾሙት የመስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር የሰጠ መሆኑንም አስታውሷል።
የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋሙ፤ ይህ ሕግ እና በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ላይ ሊደረግ የሚችለው ማሻሻያ፤ "የመናገር እና የአስተሳሰብ ነጻነትን የሚያፍን አምባገነናዊ አሠራር መመለሱን ያመለክታል" ብሏል።
የተቋሙ አፍሪካ ምክትል ዳይሬክተሯ ላቲሺያ ባደር፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን እና የሲቪል ማኅበረሰብ ለመጪው ምርጫ "የበኩላቸውን አስተዋጾ" እንዲያበረክቱ፤ "ለነጻ እና ፍትሃዊ" እንጂ "እስርን የሚፈሩ እና የራስ ሳንሱር ውስጥ የሚገቡ" መሆን እንደሌለባቸው ተናግረዋል።
"ባለሥልጣናት አሁንም አካሄዳቸውን ለመቀየር እና በጋዜጠኞች እና ገለልተኛ ድምፆች ላይ ያነጣጠሩትን ጥቃት ለማቆም ጊዜ አላቸው" እንዳሉም በመግለጫው ላይ ሰፍሯል።















