በተለያዩ አካላት ከተወሰዱ ቀናት ያለፋቸው ሁለት ጋዜጠኞች እስካሁን ያሉበት እንደማይታወቅ ባልደረቦቻቸው ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Kidame Gebeya/Ethiopian Reporter
የሪፖርተር ጋዜጣ ባልደረባ ዮናስ አማረ እና አንጋፋው ጋዜጠኛ አብዱልሰመድ መሀመድ በተለያዩ አካላት ከተወሰዱ ቀናት ቢያልፋቸውም እስካሁን ድረስ ያሉበት እንደማይታወቅ ባልደረቦቻቸው ተናገሩ።
ከጠፋ ሳምንት ገደማ የሆነው ጋዜጠኛ አብዱልሰመድ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሆኖ ቢታይም የት እንደታሰረ እንዳልታወቀ እንዲሁም ጠበቃም ሆነ ቤተሰቡም እንዲያገኝ እንዳልተደረገ ተገልጿል።
ረዕቡ ዕለት "ጭንብል በለበሱ እና የወታደር ዩኒፎርም ያደረጉ በሚመስሉ" ሰዎች ተወስዷል የተባለው ጋዜጠኛ ዮናስ ደግሞ፤ ያለበትም ሆነ በየትኛው አካል እንደተወሰደ በትክክል አለመታወቁን የሪፖርተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ሁለቱ ጋዜጠኞች እስካሁን ድረስ በጸጥታ አካላት ቁጥጥር ስር ስለመሆናቸውም ሆነ ፍርድ ቤትም እንዲቀርቡ ስለመደረጉ መረጃ አለመገኘቱንም ባልደረቦቻቸው ገልጸዋል።
በጋዜጠኝነት 30 ዓመት ገደማ ያሳለፈው አብዱልሰመድ፤ በአሃዱ ሬድዮ የሚተላለፉት 'ተረክ' እና 'ቅዳሜ ገበያ' ፕሮግራሞች ተባባሪ አዘጋጅ ነው።
በተለያዩ የዩትዩብ ቻናሎች ላይ በሚተላለፉ ፖለቲካ እና ታሪክ ነክ ዘገባዎች ላይም እንደሚሰራ አንድ ባልደረባው ለቢቢሲ ተናግሯል።
ባልደረባው እንደሚያስረዳው ጋዜጠኛው የጠፋው ከሰኞ ነሐሴ 5/2017 ዓ.ም. ከ11 በኋላ ነው። አብዱልሰመድ በዕለቱ የመንጃ ፈቃድ ፈተና እንደነበረው የገለጸው ባልደረባው፤ 11 ሰዓት ገደማ ላይ የፈተናውን ውጤት በተመለከተ ተነጋግረው እንደነበር ገልጿል።
ከዚህ በኋላም ጋዜጠኛው ቢሮው ወደሚገኝበት 22 አካባቢ ደርሶ እንደነበር በአካባቢው ከነበሩ ሰዎች መስማቱን ገልጿል።
"የፈተነው አስተማሪ ነው ከቃሊቲ መጥቶ 22 አካባቢ አውርዶት የሄደው። ከዛ ወደ ቢሮም አልገባም። 'አካባቢው ላይ ታይቷል' ተባለ፤ ግን አልተገኘም" ሲል በዕለቱ የነበረውን ሁኔታ አስታውሷል።
ጋዜጠኛው መጥፋቱን ያወቀው ሌሊት ላይ ከባለቤቱ ሲደወልለት መሆኑን የሚናገረው ባልደረባው፤ አብዱልሰመድ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ እንደሆነ ለማወቅ እንደ "ፌደራል ፖሊስ፣ማዕከላዊ" ባሉ ቦታዎች ማጣራት እንዳካሄዱም ጠቅሷል።
"ባለቤቱ የመጀመሪያው ቀን [ፖሊስ ጣቢያ] ስትጠይቅ 'አለ' ተብላ፤ በቀጣዩ ቀን ስትሄድ 'የለም እኛም እያፈላለግነው ነው፤ ማመልከቻ አስገቢ አሏት" ብሏል። እስካሁን ድረስም ጋዜጠኛው የት እንደሚገኝ አለመታወቁን አስረድቷል።

የፎቶው ባለመብት, handout
ቢቢሲ ከአብዱልሰመድ ባለቤት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ጋዜጠኛው ተባባሪ አዘጋጅ የሆነበትን 'ቅዳሜ ገበያ' የሬድዮ ፕሮግራም የሚያዘጋጀው 'ሰለንዳ ኤቨንትስ እና ኮሚኒኬሽን' ትናንት ቅዳሜ ነሐሴ 10 ቀን ባወጣው መግለጫ፤ አብዱልሰመድ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሊሆን እንደሚችል አመልክቷል።
መግለጫው፤ አብዱልሰመድ ከጠፋ ከሦስት ቀናት በኋላ ሐሙስ ዕለት በቢሮው ላይ ፍተሻ በተደረገበት ወቅት "በፖሊስ ታጅቦ" መምጣቱን እንደተረዳ ገልጿል።
ድርጅቱ፤ "የሰመድን በሕይወት መኖር የተረዳነው ሐሙስ ምሽት 22 የሚገኘው ቢሮውን ለማስበርበር በፖሊስ ታጅቦ መምጣቱን ከጥበቃ ሠራተኞች በመስማታችን ነው" ሲል በመግለጫው ላይ አስፍሯል።
እስካሁን ድረስ ጋዜጠኛው ፍርድ ቤት እንዳልቀረበ እንዲሁም ጠበቃ እና ቤተሰብ እንዲያገኝ አለመደረጉን መግለጫው ጠቅሷል።
በተመሳሳይ መልኩ ያለበት ያልታወቀው የሪፖርተር ጋዜጣ ባልደረባው ዮናስ ደግሞ የጠፋው ከረዕቡ ነሐሴ 7/2017 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ታምሩ ጽጌ ለቢቢሲ ተናግሯል።
በሪፖርተር ጋዜጣ የፖለቲካ አምድ ፀሀፊ የሆነውን ዮናስ ለመጨረሻ ጊዜ የታየው ረቡዕ ዕለት መሆኑን ዋና አዘጋጁ ገልጿል። ከረቡዕ በኋላ ባሉት ቀናት ጀምሮ ወደ ቢሮ አለመምጣቱንም አክሏል።
ዮናስ ስልክ "ሲጠራ እና ሲዘጋ" ቀናትን ማሳለፉን የጠቀሰው ታምሩ፤ ጋዜጠኛውን ለማግኘት በተለያየ መንገድ የተደረጉ ጥረቶችም ሳይሳኩ መቆየታቸውን አስታውሷል።
ዮናስ በጸጥታ አካላት ቁጥጥር ስር ውሎ ሊሆን እንደሚችል የሚያመለክት ፍንጭ የተገኘው ትናንት ቅዳሜ ጋዜጠኛው ወደሚኖርበት ሸገር ከተማ ኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየም በመሄድ ካጠያየቁ በኋላ መሆኑን ገልጿል።
መጀመሪያ ወደ አካባቢው የሄዱ ሰዎች፤"ፖሊሶች ወስደውታል" የሚል መረጃ "ከጥበቃ ሠራተኞች" ማግኘታቸውን ተናግሯል።
"ማን ይሁን፣ የትነው የወሰዱት? የሚሉትን ምንም ነገር ሊናገሩ አልፈለጉም" ሲል ዝርዝር መረጃ አለመገኘቱን አስረድቷል።
የጋዜጣው ባልደረቦች በድጋሚ ወደ ቦታው በመሄድ ነዋሪዎችን ማጠያየቃቸውን የገለጸው ታምሩ፤ "ረብዕ ዕለት ማታ ጭንብል በለበሱ ሰዎች" መወሰዱን የሚያመለክት መረጃ ማግኘታቸውን ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, The reporter
"ጭንብል የለበሱ ሰዎች ረቡዕ ዕለት ማታ መጥተው እንደወሰዱት፣ የወታደር ዩኒፎርም የለበሱ ይመስላሉ እንጂ ፊታቸው አይታም" ሲል ዮናስ በሚኖርበት ኮንዶሚኒየም የሚገኙ ነዋሪዎች እንደተናገሩ አስረድቷል።
ግለሰቦቹ ዮናስን በወሰዱበት ሰዓት "[ኮንዶሚኒየም] ውስጥ ያሉትን ሰዎች ስልካቸውን በሙሉ ተቀብለው፣ እንዳይቀርጹ፣ ምንም እንዳይሉ ሁሉንም አስፈራርተው፣ ከግቢ እንዳይወጡ አድርገው፣ መጨረሻ ላይ ሦስት ተኩል አካባቢ ይዘውት ሄዱ" የሚል መረጃም ከነዋሪዎቹ እንደተገኘ ገልጿል።
ጋዜጠኛ ዮናስ በአዲስ አበባ ፖሊስ ቁጥጥር ስር ይገኝ እንደሆነ ለማጣራት በተደረገው ጥረት "እኛ ጋር እንዲህ የሚባል ሰው የለም" የሚል ምላሽ መገኘቱንም ተናግሯል። ሌሎች ጥረቶችም አለመሳካታቸውን አክሏል።
"የወሰዱት የሕግ ሰዎች ከሆኑ ምናልባት ነገ [ሰኞ] ፍርድ ቤት ያቀርቡታል የሚል ተስፋ አለን። የሰራውም ነገር ካለ ወንጀልም ከሆነ፣ የተጠረጠረበት ጉዳይ ካለ የተሻለ የሚሆነው ወደ ሕግ ማቅረቡ ነው እንጂ እንደዚህ አፍኖ መውሰዱ ለማንም ምንም የሚጠቅመው ነገር አለ ብዬ አላስብም" በማለት ተናግሯል።
ቢቢሲ ሁለቱን ጋዜጠኞች በተመለከተ ከፌደራል እና አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች መረጃ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።
የአንጋፋው ሪፖርተር ጋዜጣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ሲያገጥመው የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ሚያዝያ ላይ የሪፖርተር ጋዜጠኛ የሆነው አበበ ፍቅር ለዘገባ ወደ ልደታ ክፍለ ከተማ ከሄደ በኋላ በፖለስ ቁጥጥር ስር ውሎ ነበር።
ጋዜጠኛው ከሁለት ቀናት እስር በኋላ ፍርድ ቤት ሲቀርብ "ሁከት እና ረብሻ ለመፍጠር ሲንቀሳቀስ" መያዙ ተገልጾ ነበር። ጉዳዩን የተመለከተው የአዲስ አበባ ከተማ ነክ ጉዳዮች ፍርድ ቤት ጋዜጠኛው በ10 ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና እንዲወጣ በመወሰኑ ተለቅቋል።
ከሁለት ወራት በፊት ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንሳይደር የበይነመረብ ሚዲያ መሥራች እና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ ከግዮን ሆቴል ተወስዶ ለስድስት ቀናት እስር ተዳርጎ ነበር።
ሰኔ 1/2017 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር የዋለው ጋዜጠኛ ተስፋለም "ሐሰተኛ መረጃ በማሠራጨት" መጠርጠሩ ተገልጾ ፍርድ ቤት ቀርቦ ነበር።
ጋዜጠኛው እስከ ሰበር ሰሚ ድረስ ባሉ የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች ቀርቦ በተደጋጋሚ በዋስትና እንዲወጣ ቢፈቀድም፤ፖሊስ ሳይለቀው ከቆየ በኋላ ሰኔ 6 ቀን ከእስር ተፈትቷል።















