በመቶዎች የሚቆጠሩ የቪኦኤ ጋዜጠኞች ከስራቸው ተባረሩ

የአሜሪካን ድምፅ (ቪኦኤ) አርማ የሚታይበት መግቢያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በተቋሙ ውስጥ ከቀሩት ሠራተኞች አብዛኛዎቹ የሆኑትን በመቶዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካን ድምፅ (ቪኦኤ) ጋዜጠኞችን በማባረር፤ በአሜሪካ መንግሥት የሚደገፈውን የዜና አውታር ሙሉ በሙሉ እንዲዘጋ አደረገ።

የትራምፕ አስተዳደር፤ ሠራተኞቹን ያባረረው ኤጀንሲው "በብልሹነት፣ በአድልዎ እና ብክነት የተሞላ" በመሆኑ እንደሆነ ገልጿል።

የቪኦኤ ዋና ብሔራዊ ዘጋቢ የሆነው ስቲቭ ኸርማን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የናዚ ፕሮፓጋንዳን ለመመከት የተቋቋመውን የዜና አውታር ማፍረስን፤ "ታሪካዊ የራስ አፈና ተግባር" ሲል ጠርቶታል።

ከተባረሩት መካከል በአስተዳደራዊ ፈቃድ ላይ የነበሩ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከፈፀመች በኋላ ባለፈው ሳምንት ወደ ስራቸው እንዲመለሱ የተደረጉ የፐርሺያን ቋንቋ ጋዜጠኞች ይገኙበታል።

አሶሺዬትድ ፕሬስ የዜና ወኪል እንደዘገበው የፐርሺያን ጋዜጠኞች ትናንት አርብ ሲጋራ ለማጨስ ከቢሮው በወጡበት ሰዓት የሥራ ውል ማቋረጥ ማስታወቂያዎች በመለጠፋ ወደ ህንፃው እንዳይገቡ ተከልክለዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ድምፅን እንድትመራ የሾሟት ካሪ ሌክ 639 ሠራተኞችን መሰናበታቸውን ይፋ ባደረጉበት አርብ ዕለት መግለጫ፤ "ዛሬ የፕሬዝዳንት ትራምፕን አጀንዳ የሆነውን፤ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የፌዴራል ቢሮክራሲን የመቀነስ ተግባር ለመፈጸም ቆራጥ እርምጃ ወስደናል" ብለዋል።

ከመጋቢት ጀምሮ፤ 1,400 ገደማ ሠራተኞች ወይም ከኤጀንሲው ሰራተኞች ከ 85 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሥራቸውን አጥተዋል።

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ በቪኦኤ፣ በኩባ ብሮድካስቲንግ ቢሮ እና የቪኦኤ እናት ኩባንያ በሆነው 'ዩኤስ ኤጀንሲ ፎር ግሎባል ሚዲያ' (USAGM) ውስጥ 50 ሰራተኞች በቅጥር ላይ ይቆያሉ።

የተቋሙን መፍረስ ለማስቆም ክስ የመሰረቱ ሶስት የቪኦኤ ጋዜጠኞች አዲሱን ሰራተኞች የማባረር እርምጃን በተመለከተ ባወጡት መግለጫ፤ "በዓለም ዙሪያ የአሜሪካን የዴሞክራሲ እና የነፃነት እሳቤዎች የሚደግፍ የ83 ዓመት ነፃ ጋዜጠኝነት መሞቱን ያመለክታል" ብለዋል።

ትራምፕ፤ ቪኦኤን እንዲሁም ቪኦኤን የሚቆጣጠረው እና እንደ ራዲዮ ፍሪ ኢሮፕ እና ራዲዮ ፍሪ ኤዠያ ላሉ የዜና አውታሮች የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርገው ዩኤስኤጂኤም "ከተገቢው ሕግ በተጣጣመ መልኩ በተቻለ መጠን እንዲወገዱ" ትእዛዝ ከሰጡበት ከመጋቢት ወር ጀምሮ ይህ እርምጃ ይጠበቅ ነበር።

ኤጀንሲዎቹ ከቻይና እና ከካምቦዲያ እስከ ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ድረስ የፕሬስ ነጻነት በከፍተኛ ሁኔታ በተገደበ ወይም በማይኖርባቸው አካባቢዎች ለሪፖርታቸው ምስጋና እና ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝተዋል.

የቀድሞው የቪኦኤ ዘጋቢ የሆነው ዳን ሮቢንሰን ባለፈው ዓመት በጻፈው የአስተያየት መጣጥፍ፤ ተቋሙ "በትዕቢት ተሞላ፣ የማይታመን፣ ብዙውን ግዜ ከግራ ዘመም ወገንተኝነት ጋር የሚጣመር ብሔራዊ መገናኛ ብዙሃን" ሆኗል በማለት ተችቷል።

ትራምፕ፤ ቪኦኤ ላይ የሚያቀርቡት ትችት በአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ላይ እያካሄዱ ያሉት ሰፊ ጥቃት አካል ነው። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አሜሪካውያን ዜና አውታሮቹን እጅጉን የተከፋፈሉ እንደሆኑ ያምናሉ።

ፕሬዚዳንቱ በተጨማሪም ለናሽናል ፐብሊክ ራዲዮ (NPR) እና ለፐብሊክ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (PBS) የሚደረገው የፌዴራል የገንዘብ ድጋፍ እንዲነሳ ሪፐብሊካን ባልደረቦቻቸውን አሳስበዋል።