ህወሓት በጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚደረግ ሹም ሽር ተፈጻሚ አይሆንም አለ

የህወሓት ጽ/ቤት ዋና ኃላፊ ተደርገው የተሾሙት ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር

የፎቶው ባለመብት, TPLF

የምስሉ መግለጫ, የህወሓት ጽ/ቤት ዋና ኃላፊ ተደርገው የተሾሙት ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር

በእነ ደብረጺዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራ የህወሓት ቡድን በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሚያደረግ ሹም ሽር ተፈጻሚ አይሆንም አለ።

በቅርቡ የህወሓት ፅ/ቤት ዋና ኃላፊ ተደርገው የተሾሙት ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር ለሁሉም የህወሓት የዞን እና ወረዳ ጽ/ቤቶች በላኩት ደብዳቤ "የፓርቲውን አሠራር እና ሕጋዊ አካሄድ ባልተከተለ መንገድ የስልጣን ሹምር ሽር እየተካሄ ነው" ብለዋል።

ፊትለወርቅ በደብዳቤያቸው ይህን ያሉት ከቀናት በፊት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የደቡባዊ ምስራቅ ዞን አስተዳዳሪ የነበሩትን ሊያ ካሳን ከሥልጣን ካሰናበቷቸው በኋላ ነው።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውስጥ ለበርካታ አስርት ዓመታት ጉልህ ሚና ሲጫወት በቆየው ህወሓት ውስጥ ባሉ አመራሮች መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠንከር ያለ ክፍፍል መፈጠሩ ይታወቃል።

በአመራሮቹ መካከል ልዩነት ከፈጠሩ ጉዳዮች መካከል የፓርቲው ዳግም ምዝገባ እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተካሄደው ጉባኤ ተጠቃሽ ናቸው።

በሊቀ-መንበሩ በእነ ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው ቡድን ከእነ አቶ ጌታቸው ረዳ ፍላጎት እና ዕውቅና ውጪ የፓርቲውን 14ኛ ጉባኤ ማካሄዱ፤ እንዲሁም ዳግም ሕጋዊ ሰውነቱን ለማስመለስ ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ አቅርቦ በቦርዱ ዳግም መመዝገቡ ይታወሳል።

የደቡብ ምስራቅ ዞን አስተዳዳሪ የነበሩት ሊያ ካሳ ብዙ ባወዛገበው በፓርቲው 14ኛ ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ተደርገው ተመርጠዋል።

ይህ በህወሓት አመራሮች መካከል መከፋፈል የፈጠረው ጉባኤ ደብረጺዮን ገብረ ሚካኤል የፓርቲው ሊቀ-መንበር አድርጎ መልሶ ሾሞ፤ አቶ ጌታቸውንን ጨምሮ ሌሎች የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ደግሞ ከፓርቲ ከፍተኛ ኃላፊነት ማንሳቱ ይታወሳል።

የህወሓት ጽ/ቤት ኃላፊ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር ለዞን እና ወረዳ የፓርቲ ጽ/ቤቶች በላኩት ደብዳቤ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ "ለረዥም ጊዜ ህወሓትን የማፍረስ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል" ሲሉ ከሰዋል።

“የፓርቲ አሠራርን ባልተከተለ እና ሕጋዊ ባልሆነ አካሄድ የዞን እና የወረዳ ኃላፊዎችን ከሥልጣን ለማንሳት” ጥረት ሲደረግ ቆይቷል ሲሉ ወቅሰው፤ ሹም ሽሩ “ህወሓትን ከሥሩ ለመንቀል እየተደረገ ያለን አሻጥር ነው” ብለዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ በዞንም ሆነ በወረዳ ደረጃ "ሕጋዊ አካሄዶችን ሳይከተል የሚሾማቸው ግለሶች ሥልጣን መረከብ እና መስራት እንደማይችሉ እናሳውቃለን" ይላል ፈትለወርቅ ያሰራጩት ደብዳቤ።

በሁለቱ ቡድኖች መካከል ልዩነት የፈጠረው ጉባኤ መጠናቀቂያ ገደማ አቶ ጌታቸው ረዳ የጠሩት “ህወሓትን የማዳን” ስብሰባ ተካሂዶ ነበር።

የዚህ ሰብሰባ መጠናቀቅን ተከትሎ በወጣ 10 ነጥብ የያዘ የአቋም መግለጫ ላይ የተካሄደው የህወሓት ጉባኤ ሕጋዊ አይደለም፣ በጉባኤው የሚተላለፉ ውሳኔዎች ሕጋዊ ተፈጻሚነት አይኖራቸውም፣ ህወሓት ዳግም እንዲመዘገብ መደረጉ ‘ቅርቃር ውስጥ’ ከትቶታል፣ የትግራይ ኃይሎች በክፍፍሉ ውስጥ ገለልተኛ እንዲሆኑ እና የትግራይ ሕዝብ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጎን እንዲቆም የሚጠይቁ ነጥቦች ተካተዋል።

ከዚህ በመቀጠል ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል በከፍተኛ አመራሮቹ ክፍፍል መካከል በተደረገው በ14ኛው የህወሓት ጉባኤ ያልተገኙ እና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ያሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና ስራ አስፈጻሚዎች ድርጅቱን እንደማይወክሉ በጠሩት መግለጫ መናገራቸው ይታወሳል።