የቴሌግራም ዋና ሥራ አስኪያጅ ፈረንሳይ አየር ማረፊያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቴሌግራም የተባለው የማኅበራዊ ትስስር መተግበሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፓቬል ዱሮቭ ፈረንሳይ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋለ።
ፓቬል በፈረንሳይ ፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለው በፓሪስ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኝ አንድ አየር ማረፊያ ነው።
የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን እንደገለጡት ሥራ እስኪያጁ በቁጥጥር ሥር የዋለው ለ ቡርጌ በተሰኘው አየር ማረፊያ በግል አውሮፕላኑ ካረፈ በኋላ ነው።
ባለሥልጣናት እንዳሉት የ39 ዓመቱ ፓቬል በፖሊስ የተያዘው ከታዋቂው መልዕክት መላላኪያ መተግበሪያ ጋር በተያያዘ በተፈጸም ጥሰት በወጣበት የእስር ትዕዛዝ መሠረት ነው።
በሩሲያ የተወለደው ፓቬል የሩሲያ፣ የፈረንሳይ እና የአረብ ኤምሬትስ ጥምር ዜግነት ያለው ሲሆን ከ15 ቢሊዮን በላይ የተጣራ ንብረት እንዳለው ይገመታል።
በፈረንሳይ የሩሲያ ኤምባሲ ሁኔታውን ለማጣራት “አፋጣኝ እርምጃ” እየወሰደ እንደሆነ የሩሲያ መንግሥት የዜና ወኪል የሆነው ቲኤኤስኤስ ዘግቧል።
የፈረንሳዩ የተሌቪዥን ጣቢያ ቲኤፍ1 በድረ-ገፁ እንደፃፈው ፓቬል በግል አውሮፕላኑ ነበር ሲንቀሳቀስ የነበረው።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ቢሊየነሩ የቴሌግራም መሥራች ከአዘርባይጃን ተነስቶ የመጣ ሲሆን በቁጥጥር ሥር የዋለው ደግሞ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 2፡00 ነው።
ግለሰቡ እሑድ ዕለት ፍርድ ቤት ሊቀርብ እንደሚችል የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን መዘገባቸውን ሮይተርስ ፅፏል።
ሮይተርስ አክሎ ተሌግራም፣ የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር እና ፖሊስ እስካሁን ምንም ዓይነት መግለጫ አለመስጠታቸውን ዘግቧል።
ሩሲያ የተወለደው ፓቬል የሚኖረው የቴሌግራም ዋና መሥሪያ ቤት በሚገኝበት ዱባይ ሲሆን የፈረንሳይ እና የዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ዜግነት አለው።
ፎርብስ የተባለው መፅሔት ፓቬል 15.5 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሀብት አለው ሲል ይገምታል።
ቴሌግራም የተባለው የመልዕክት መላላኪያ ገፅ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሩሲያ እና ዩክሬን እንዲሁም በቀድሞው የሶቪየት ኅብረት ሀገራት በጣም ታዋቂ እና በርካቶች የሚጠቀሙት መተግበሪያ ነው።
ዋና ሥራ አስኪያጁ ፓቬል ዱሮቭ የተጠቃሚዎችን መረጃ ለመንግሥት አሳልፌ አልሰጥም በማለቱ ቴሌግራም በ2018 ሩሲያ ውስጥ ታግዶ ነበር።
ነገር ግን በ2021 ይህ ውሳኔ ተሽሮ መተግበሪያው ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል።
ቴለግራም ከፌስቡክ፣ ዩቲዩብ፣ ዋትስአፕ፣ ኢንስታግራም፣ ቲክቶክ እና ዊቻት ቀጥሎ በጣም በርካታ ተጠቃሚዎች ያሉት ማኅበራዊ ሚድያ ነው።
ቢሊየነሩ ፓቬል ዱሮቭ እና ወንድሙ ቴሌግራምን የመሠረቱት በአውሮፓውያኑ 2013 ሲሆን አሁን ቴሌግራም 900 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አሉት።
ፓቬል በ2014 ቪኮንታክቴ የተባለ ማኅበራዊ ሚድያው ላይ ያሉ ተቃዋሚዎችን ዝም እንዲያሰኝ ከሩሲያ መንግሥት የቀረበለትን ጥያቄ ባለመቀበሉ ሞስኮውን ጥሎ ከወጣ በኋላ ማኅበራዊ ሚድያውን ሸጦታል።












