ከለንደን እስከ ኒው ዮርክ 2.5 ሚሊዮን ፓዎንድ ያጭበረበረው ወጣት

የፎቶው ባለመብት, Two Rivers Media/BBC
ኢሊየት ካስትሮ በግላስጎው ከተማ በአንድ ሞባይል መሸጫ ሱቅ በሚሠራበት ወቅት ከአንድ ደንበኛው የግል የባንክ መረጃ አጭበርብሮ ሲቀበል ገና የ16 ዓመት ታዳጊ ነበር።
ከዚያች ዕለት በኋላ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ውድ ጫማ መጫመት፣ ቅንጡ የእጅ ሰዓቶችን መግዛት እና በቢዝነስ ክፍል በረራ ከአውሮፓ ወደ አሜሪካ ለሽርሽር መጓዝ በየዕለቱ የሚያደርገው የሕይወቱ አካል ሆነ።
ካስትሮ ገና በልጅነት ዕድሜው የገባበት ሰዎችን የማጭበርበር ወንጀል ከ2.5 ሚሊዮን ፓዎንድ በላይ ገንዘብ ቢያስገኝለትም በሕግ ከመጠየቅ ግን አላመለጠም።
በአሁኑ ወቅት የ42 ዓመት ጎልማሳ የሆነው ካስትሮ በልጅነት ዕድሜው በፈጸመው ወንጀል እንደሚጸጸት ይናገራል። አሁን ላይ አጭበርባሪዎችን የሚከላከል አማካሪ ሆኖ እየሠራ ይገኛል።
ካስትሮ የ16 ዓመት ጎረምሳ ሳለ የሞባይል ስልክ ለመግዛት የመጡ ደንበኞች የባንክ ካርድ ችግር እንዳለበት በመንገር ከባንካቸው ጋር በስልክ እየተነጋገር አስመስሎ ነበር ሙሉ የባንክ መረጃቸውን በመቀበል የማጭበርበር ሥራው አንድ ብሎ የጀመረው።
“ይህን ማድረግ እችል ይሆን ብዬ አንድ ጊዜ ለመሞከር ያደረኩት ነበር” ይላል።
ለሙከራ ብሎ የጀመረው የማጭበርበር ድርጊት ግን በሙከራ አልቆመም።
በማጭበርበር ተግባሩ ቀጠለ። “ከ16 ዓመቴ ጀምሮ እስከ 21 ወይም 22 ዓመት እስኪሞላኝ ድረስ ማመን የማይቻሉ አምስት ዓመታትን አሰለፍኩ” ሲል ካስትሮ ለቢቢሲ ሁኔታውን ያስታወሳል።
በአውሮፓውያኑ 1982 የተወለደው ካስትሮ በቤተሰቦቹ የሥራ ባህሪ ምክንያት በልጅነት ዕድሜው በተለያዩ ከተሞች መኖሩን ይናገራል።
በሕይወቴ ብዙ ነገሮችን የማሳካት ጽኑ ፍላጎት ነበረኝ የሚለው ካስትሮ፤ የመጀመሪያ ሥራውን ሲቀጠር እንኳ ዕድሜ ገና 16 እያለ በሥራ ቅጥር ማመልከቻ ላይ በሐሰት ዕድሜው 18 መሆኑን ጠቅሶ ነበር ሥራ ያገኘው።
ከቺሊ እና ዩናይትድ ኪንግደም ወላጆች የተገኘው ካስትሮ “አስገራሚ የሆነ ሕይወት እንደሚኖረኝ ቀድሞውንም ይታወቀኝ ነበር” ይላል።
ካስትሮ 20 ዓመት ሳይሞላው ከፍተኛ ገንዘብ በሚጠየቅባቸው ሽርሽሮች ተዝናንቷል። በባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ውስጥ ፓርቲዎችን ደግሷል። በሚከራያቸው ሊሞዚኖች ሽር ብትን ብሏል።
‘ሆም አሎን’ የተሰኘው የአሜሪካ ፊልም አድናቂ የሆነው ካስትሮ፤ ፊልሙ በተቀረጸበት የኒው ዮርኩ ፕላዛ ሆቴል ለመቆየት 8 ሺህ ፓዎንድ አውጥቶ ወደ አሜሪካ ተጉዟል።
በዚያ ጉዞ ላይ በሦስት ቀናት ግብይት 15 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወጪ አድርጓል።
“በወቅቱ የዕለተ ተዕለት ውሎዬ ጠዋት መነሳት፣ የሆነ ነገር ለምገዛት መውጣት፣ መብላት መጠጣት ከዚያ ሲመሽ ወደ ሆቴል ክፍል ገብቶ መተኛት። ከዚያ በቀጣይ ቀን ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ እኔን ለመያዝ የሆነ ሰው በሥራ ላይ እንዳለ ወይም ያ ሰው እየተከታተለኝ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር” በማለት ካስትሮ ሁኔታውን ያስታውሳል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እአአ 2001 ላይ ወደ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ስፔን ሽርሽር ሄዷል። በቀጣዩ ዓመት በአየርላንድ መዲና ደብሊን በሚገኘው ክላረንሰ ሆቴል ቆይቷል። በቆይታው ከሆቴሉ ባለቤቶች ጋር በተገናኘ ወቅት ለዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ኃይል እንደሚሠራ እንደነገራቸው ያስታወሳል።
በዚያው ዓመት ማብቂያ ላይ በፖሊስ ተያዘ። 18 ወራትንም በእስር እንዲያሳልፍ ተፈረደበት። ካስትሮ በእስር ቤት ቆይታው ከጥፋቱ ታርሞ ከመውጣት ይልቅ ግን ከእስር ሲወጣ አዲስ የማጭበርበሪያ መንገድን ማሰላሰል ያዘ።
ከእስር ቤት እንደወጣ በወቅቱ ለብዙዎች አዲስ የሆነውን ኢንተርኔት ተጠቅሞ በተሰረቁ የባንክ ካርዶች የአየር ቲኬቶችን መቁረጥ ጀመረ።
ከእስር በወጣ በዓመቱ ካናዳ ቶሮንቶ ላይ ተይዞ ለሦስት ወራት ታስሮ እአአ 2003 ላይ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ተጠርዞ ተላከ።
“ይሄ የማጭበርበር ተግባሬ መቆም አለበት ብዬ በጣም አስብ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ጓደኞች አፍርቼ ሕይወትን እንደ አዲስ መጀመር በጣም የምፈልግበት ጊዜ ላይ ደርሰርኩ።”
ካስትሮ በዚህ ስሜት ውስጥ እያለ በስኮትላንዷ ኤደንብራ ከተማ በተሰረቀ የባንክ ካርድ የ2ሺህ ፓዎንድ ኩፖን ይገዛል።

የፎቶው ባለመብት, James Burns
ግብይቱን ፈጽሞ ከሄደ በኋላ ግብይቱ የተፈጸመው በተሰረቀ የባንክ ክሬዲት ካርድ መሆኑ ተደርሶበት በቦታው ፖሊስ ይደርሳል።
“በጣም ትልቅ ስህተት ሰርቼ አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ተመልሼ ወደ ሱቁ ተመልስኩ። በሩን ከፍቼ ስገባ ፖሊሶች ስመለከት እንዳበቃለኝ ገባኝ።”
ያን ዕለት ዘብጥያ ወረደ። በቀጣይ ዓመት ፍርድ ቤት ቀርቦ 73 ሺህ ፓዎንድ በሚደርስ የማጭበርበር ወንጀል ጥፋተኝነቱን አምኖ ሁለት ዓመት በእስር አንዲያሳልፍ ተበየነበት።
ካስትሮ በማጭበርበር ድርጊት የተጠቀምኩት በሕግ አስካበሪዎች እና በባንኮች መካከል ያለው የግንኙነት መስመር የላላ መሆኑ ነው ይላል።
“በእነዚያ አምስት ዓመታት ጥሩ ግንኙነት ቢኖራቸው በፍጥነት ማስቆም በቻሉ ነበር” ይላል።
ዛሬ ላይ ካስትሮ ሌላ ሰው ሆኗል። ሰዎችን ባሳዘነ እና ባከሰረ ተግባሩ ይጸጸታል። ወንጀሎቹን ከፈጸመ ከ20 ዓመታት በኋላ ትክክል ብሎ ያሰበውን የእርምት እርምጃ እየወሰደ ይገኛል።
ከሕግ አስከባሪ አካላት ጋር በመተባበር ውስብስብ የሆኑ የማጨበርበሪያ መንገዶችን ለመለየት እና የክሬዲት ካርድ አጭበርባሪዎችን ለመያዝ አማካሪ ሆኖ ይሠራል።
“እንደ መታደገል ሆኖ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር፣ ከጉዞ ወኪሎች እና ከንግድ ድርጅቶች ጋር እንደማካሪ ሆኜ መሥራቴ ዕድለኛ እንዳደረገኝ ይሰማኛል” ይላል።












