ከትንሿ የአውሮፓ አገር በቻይናውያን የሚንቀሳቀሰው የአጭበርባሪዎች ሰንሰለት

ሊያንግ የሚታይበት ምሥል

አይል ኦፍ ማን በተሰኘችው ደሴት ባሕር ዳርቻ ያለ አንድ ሆቴል በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን ከቻይናውያን የሚያጭበረብርበት የወንጀል መረብ እንዳለው የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ ያሳያል።

ዳግላስ የሚገኘው ሲቪው ሆቴል በቻይናውያን ሠራተኞች የተጨናነቀ መሆኑ ሲነገር ቆይቷል። ሠራተኞቹ የሚጠቀሙት ኮምፒውተር ፍጥነት ካላቸው የብሮድባንድ ገመዶች ጋር የተገናኘ ነው።

ከአውሮፓውያኑ ጥር 2022 እስከ ጥር 2023 ባለው ጊዜ የተካሄደው ማጭበርበር ‘ፒግ ቡቸሪንግ’ በተባለ መንገድ እንደሆነ የቻይና ችሎት መዛግብት ያሳያሉ።

ፒግ ቡቸሪንግ በግርድፉ ሲተረጎም አሳማ ማረድ ነው። ይህ ስያሜ የተሰጠው ‘ፒግ ፋትንኒንግ’ አሊያም አሳማ ማስባት ከሚለው ሐሳብ ነው። የተጭበርባሪዎችን እምነት መግዛት እንደማለት ነው።

ቢቢሲ አንድ ዓመት በፈጀው ምርመራው በብሪታኒያ ንጉሣውያን ከምትዳደረው ነገር ግን የራሷ ገለልተኛ መንግሥት ካላት ከትንሿ ደሴት እንዴት ማጭበርበር ሊካሄድ ቻለ የሚለውን ለማጣራት ሞክሯል።

የአጭበርባሪዎቹ አለቃዎች ዓላማቸው የነበረው እጅግ ዘመናዊ ለቢሮ አገልግሎት የሚውል ሕንፃ መገንባት ነበር።

ቢቢሲ በምርመራ ዘገባው ከፍርድ ቤት መዛግብት በተጨማሪ ሾልከው የወጡ ሰነዶች እና የኩባንያውን የውስጥ አዋቂዎች አናግሯል።

አይል ኦፍ ማን የሚገኘው ነጭ እና ቀይ ቀለም ያለው ሲቪው ሆቴል
የምስሉ መግለጫ, አይል ኦፍ ማን የሚገኘው ነጭ እና ቀይ ቀለም ያለው ሲቪው ሆቴል

ለዚህ ጽሑፍ ስሙ የተቀየረው ጆርዳን የኩባንያው የቀድሞ ሠራተኛ ነው። ጆርዳን እንደሚለው ወደ አይል ኦፍ ማን ሲመጣ እንዲህ ዓይነት ነገር ውስጥ እገባለሁ ብሎ አስቦ አይደለም። እሱ እንደሚለው አብዛኞቹ ቻይናውያን የሥራ አጋሮቹ በማጭበርበር ወንጀል የተካኑ ናቸው።

እሱ ሲቀጠር እንዳስተዋለው አሠሪዎቹ በጣም ምሥጢረኛ ናቸው። ለምሳሌ እሱ እና ሌሎች የሥራ አጋሮቹ በኩባንያው ቅጥር ግቢ ውስጥ ሳሉ ፎቶ ማንሳት አይፈቅዳላቸውም። አክሎ እሱ እና ቻይናውያን አጋሮቹ አጭበርባሪ መሆናቸውን እንኳ እንደማያውቁ ያስረዳል።

በአውሮፓውያኑ 2021 መጨረሻ 100 ገደማ ሠራተኞች ለኩባንያው ለመሥራት ወደ አይል ኦፍ ማን መጥተዋል። የፍርድ ቤት መዛግብት ኩባንያውን “ኤምአይሲ” ሲሉ ነው የሚጠሩት።

እነዚህ 100 ሠራተኞች ከዚህ ቀደም ፊሊፒንስ ውስጥ ለሚገኝ ሌላ አጭበርባሪ ኩባንያ ነበር የሚሠሩት። ቢቢሲ ባጣራው መሠረት ኤምአይሲ ማለት ማንክስ ኢንተርኔት ኮሜርስ ማለት ነው።

አይል ኦፍ ማን ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ኤምአይሲ የኩባንያዎች ጥምረት ሲሆን፣ ባለቤቱ ግን አንድ ነው።

ከኩባንያዎቹ መካከል ኪንግ ጌሚንግ ሊሚትድ የተባለው የበይነ መረብ የካዚኖ ድረ-ገፅ አንዱ እና ታዋቂው ነው።

ቻይና ውስጥ ቁማር በሕግ የተከለከለ ነው። ነገር ግን ከቻይና በርካታ ኪሎ ሜትሮች ርቆ አይል ኦፍ ማን ቢሮ ማቋቋሙ አንደኛ ቻይናውያንን ዒላማ ለማድረግ፤ ሁለተኛ ደግሞ ከደሴቷ የቁማር ግብር ለመጠቀም ይረዳዋል።

የቢል ሞርጋን/ሊያንግ ላንግፌይ የዶሚኒካን ፓስፖርት
የምስሉ መግለጫ, የቢል ሞርጋን/ሊያንግ ላንግፌይ የዶሚኒካን ፓስፖርት

የአይኤምሲ ሠራተኞች ወደ ዳግላስ መጥተው ሲቪው ሆቴል ለጥቂት ወራት ከከረሙ በኋላ በከተማዋ ምሥራቃዊ ክፍል ወደ ሚገኙ ቀድሞ ባንክ ሆነው ያገለግሉ ወደነበሩ ሕንፃዎች ተዘዋወሩ።

ጆርዳን እንደሚለው ወደእነዚህ ሕንፃዎች ከተዘዋወሩ በኋላ ነው አዳዲሶቹ የሥራ ባልደረቦቹ በደስታ ሲፈነጥዙ መስማት የጀመረው። አራት አራት ሆነው ተቀምጠው ነበር የሚሠሩት። አዳዲሶቹ ሠራተኞች ድንገት ተነስተው የሚጨፍሩት ካሉበት 5 ሺህ ማይል ርቀት ላይ ካሉ ሰዎች ገንዘብ ሲያጭበረብሩ ነው።

ለኤምአይሲ ይሠሩ የነበሩ 6 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ተፈርዶባቸዋል። በቁጥጥር ሥር የዋሉት ወደ ቻይና ሲመለሱ ሲሆን፣ ቻይናውያንን በማጭበርበር ወንጀል ነው ጥፋተኛ ሆነው የተገኙት።

ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት 2023 የተከፈተው የክስ መዝገብ እንዴት ገንዘብ እንዳጭበረበሩ በዝርዝር የሚያስቀምጥ ነው። የቻይና ችሎት መዛግብት እንደሚያሳዩት ቻይና እና ፊሊፒንስ ያሉ ሰዎች ናቸው ዒላማ የሚደረጉት።

አጭበርባሪዎቹ ኪውኪው ወደተባለው እንደ ዋትስአፕ ያለ የመልዕክት መለዋወጫ ቻይናውያን ኢንቨስተሮችን አታለው ካስገቡ በኋላ ነው ሥራቸውን የሚሠሩት። አንደኛው አጭበርባሪ የኢንቨስትመን “አስተማሪ” ሌሎች ደግሞ ትምህርቱን የሚከታተሉ ኢንቨስተሮች መስለው ይቀላቀላሉ።

ቢቢሲ የተመለከተው ማስረጃ እና የፍርድ ቤት መዛግብት እንደሚያሳዩት አጭበርባሪዎቹ ኮምፒውተር እና ኪውኪው የተባለውን የመልዕክት መላላኪያ የሚጠቀሙ ሲሆን፣ ከጥቂት ‘ማናጀሮች’ በቀር ሁሉም ተመሳሳይ የሥራ መጠሪያ ነው ያላቸው።

የቻይና ፍርድ ቤት የክስ መዝገብ
የምስሉ መግለጫ, የቻይና ፍርድ ቤት የክስ መዝገብ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አጭበርባሪዎቹ ኢንቨስተሮች “የአስተማሪውን” ትምህርት እየተከታተሉ በአድናቆት በተሞላ ቃል ሙገሳ ያቀርባሉ። ቀጥሎ ሰለባ የሚሆነውን ግለሰብ ኢንቨስት እንዲያደርግ የማሳመን ሥራ ይሠራሉ።

የቻይና ፍርድ ቤቶች መዛግብት እስካሁን ምን ያክል ገንዘብ እንዳጭበረበሩ ለማወቅ አዳጋች ነው ቢልም ቢያንስ ከ12 ሰለባዎች 5.3 ሚሊዮን ዶላር ወስደዋል ይላሉ።

ፍርድ ቤቱ የከሳሾችን ምስክርነት እንዲሁም ጉዞ እና የገንዘብ ዝውውር ታሪክ እንዲሁም የተለዋወጧቸውን መልዕክቶች በመመልከት ስድስቱ አጭበርባሪዎች ወንጀለኛ ናቸው ብሏል።

ይህ የማጭበርበር ወንጀል የተወሳሰበ ብቻ ሳይሆን በጣም አትራፊ እንደሆነ ነው የፍርድ ቤት ሰነዶች የሚያሳዩት።

ቢቢሲ ባደረገው ምርመራ የኩባንያውን ዋነኛ ተጠቃሚ ማንነት ማጣራት ችሏል። ግለሰቡ ስሙን ደብቆ ነው የሚንቀሳቀሰው። ኤምአይሲ እና አጋር ኩባንያዎቹ የተቋቋሙት ቢል ሞርጋን በተባለ ግለሰብ ስም ነው።

ይህ ግለሰብ ሊያንግ ሊንግፌይ የተባለ ሌላ ስም አለው። ጆርዳን እንደሚለው ሠራተኞች “ቦስ ሊያንግ” እያሉ ነው የሚጠሩት።

የቻይናው ፍርድ ቤት እንደገለጸው ሊያንግ ሊንግፌይ በአይል ኦፍ ማን የኤምአይሲ ኩባንያን ከመሠረቱ ግለሰቦች መካከል አንዱ ነው። ሊያንግ ብይን ሲሰጥ በሥፍራው አልነበረም፤ ፍርድም አልተሰጠበትም።

የፍርድ ቤት ወረቀቶች እንደሚጠቁሙት ሊያንግ ፊሊፒንስ ውስጥ የሚገኝ ሌላ የአጭበርባሪዎች ኩባንያ ከመሠረቱ ሰዎች መካከል ነው። ቢቢሲ እንዳጣራው ወደ አይል ኦፍ ማን ተዘዋውረው ከመጡ የኤምአይሲ ሠራተኞች መካከል አብዛኞቹ ፊሊፒንስ ይሠሩ ነበር።

የቢቢሲ ምርመራ ጨምሮ እንዳሳየው ሊያንግ ከአይል ኦፍ ማን የኢንቨስትመንት ቪዛ ያገኘ ሲሆን፣ ወደ ደሴቷ በተደጋጋሚ ይመጣል። ሚስቱ ደግሞ ባላሳል በተባለቸው ለአየር ማረፊያ ቀርባ በምትገኝ ሥፍራ ቤት አላት።

ባለፈው ዓመት ኩባንያው በደሴቷ ትልቁ ነው የተባለውን ለቢሮ አግልግሎት የሚውል ግዙፍ ሕንፃ ለማስገንባት ከአንድ የሥነ-ሕንፃ ኩባንያ ጋር ውል ተፈራርሟል። ሕንፃው መኖሪያ ቤቶች፣ የተለያዩ መጠጥ ቤቶች እና ላውንጅ እንደሚኖሩት ‘ፕላኑ’ ያሳያል።

ሕንፃው ሊገነባ የታሰበው የኤምአይሲ ሠራተኞች እንዲሁም የአጋር ኩባንያ ሠራተኞች እንዲገለገሉበት ነበር።

የኩባንያዎቹ ዋና መሥሪያ ቤት መግቢያ በር
የምስሉ መግለጫ, የኩባንያዎቹ ዋና መሥሪያ ቤት መግቢያ በር

በዓለማችን ‘ፒግ ቡቸሪንግ’ በተባለው መንገድ በየዓመቱ የሚጭበረበረው ገንዘብ ቢያንስ 60 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ይገመታል።

የተባበሩት መንግሥታት የተደራጀ ወንጀል ተቋም ባለሙያ የሆኑት ማሱድ ካሪሚፑር ለወትሮው ደቡብ እስያ ላይ አተኩረው ነበር የሚሠሩት። “ይህ በምዕራቡ ዓለም የታየ የመጀመሪያም” የፒግ ቡቸሪንግ ክስተት ነው ይላሉ።

የአይል ኦፍ ማን ፖሊስ ባለፈው ሚያዝያ የቀድሞ የባንክ ቢሮዎችን ፈትሸዋል። ሌሎችም የተጠረጠሩ ቢሮዎች ፍተሻ ተደርጎባቸዋል። ፖሊስ በሰጠው መግለጫ ድንገተኛ ፍተሻ እያደረገ ያለው ኪንግ ጌሚንግ ሊሚትድ በተሰኘው ኩባንያ ላይ በተከፈተው ምርመራ ምክንያት መሆኑን አስታውቋል።

ሰባት ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው በዋስ መለቀቃቸው ተገልጿል። ቀጥሎ ደግሞ ሦስት ተጨማሪ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተዘግቧል።

የደሴቷ የቁማር ተቆጣጣሪዎች ከኤምአይሲ ጋር ግንኙነት ያላቸው አቋማሪዎችን ፈቃድ ነጥቀዋል። ሊገነባ የታሰበውም ሕንፃ ለጊዜው እንዲቆም ተደርጓል።

ቢቢሲ በተደጋጋሚ በተለያዩ መንገዶች ኩባንያዎቹን እንዲሁም ቢል ሞርጋን አሊያም ሊያንግ ላንግፌይን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።