እስራኤል በሊባኖስ የሚገኙ የሄዝቦላ ዒላማዎችን በአየር መደብደብ ጀመረች

የፎቶው ባለመብት, AFP
የእስራኤል መንግሥት የአገሪቱ አየር ኃይል ተዋጊ ጄቶች በሊባኖስ በሚገኙ የሄዝቦላ ዒላማዎችን እየደበደቡ መሆኑን አስታወቀ።
በሌላ በኩል ሄዝቦላ የእስራኤል ወታደራዊ ጣቢያዎችን ዒላማ ያደረጉ በመቶች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ወደ ሰሜናዊ እስራኤል ማስወንጨፉን አስታውቋል።
የእስራኤል መካለከያ ሚኒስትሬ እሁድ ንጋት ነሐሴ 19/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ወደ እስራኤል ሚሳኤሎችን እና ሮኬቶችን ለመተኮስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መታየታቸውን ተከትሎ እራስን የመከላከል እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል ብሏል።
“ይህን ስጋት ለመቀልበስ በተደረገ እራስን የመከላከል ተግባር አይዲኤፍ (የእስራኤል መከላከያ ኃይል) አሸባሪዎችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት እየፈጸመ ይገኛል” ሲሉ የእስራኤል ጦር ቃል አበባይ ዳንኤል ሃጋሪ ተናግረዋል።
የእስራኤል መንግሥት ጥቃቱን መውሰድ ከመጀመሩ በፊት ሰላማዊ ሰዎች ሄዝቦላ ከሚገኝባቸው አካባቢዎች እንዲርቁ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል ብሏል።
በኢራን የሚደገፈው የሺዓ ሙስሊም ቡድን የሆነው ሄዝቦላ በበኩሉ መጠነ ሰፊ የሆነ የድሮን ጥቃት እስራኤል ላይ መክፈቱን አስታውቋል።
እስራኤል ከሳምንታት በፊት የቡድኑን ከፍተኛ የጦር መኮንን መግደሏን ተከትሎ ሄዝቦላ የበቀል እርምጃ እንደሚወስድ ሲዝት መቆየቱ ይታወሳል።
ከዚህ በተጨማሪ እስራኤል የሐማስ የፖለቲካ ቢሮ ኃላፊ የሆኑትን እስማኤል ሃኒዬን በኢራን መዲና ቴህራን መግደሏን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ሰፊ የሆነ ጦርነት መቀስቀሱ አይቀሬ ነው ሲባል ቆይቷል።
የሄዝቦላን የድሮን ጥቃቶችን ተከትሎ እሁድ ንጋት ላይ በሰሜናዊ እስራኤል በሚገኙ አካባቢዎች የማስጠንቀቂያ ደውሎች ሲሰሙ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, EPA
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ወደ 100 የሚጠጉ የጦር ጀቶቹ እየተሳፉ በሚገኙበት የአየር ድብደባ በ40 ቦታዎች የነበሩ በሺዎቹ የሚቆጠሩ የሄዝቦላ የሮኬት ማስወንጨፊያዎችን ማውደሙን አስታውቋል።
የእስራኤል የጦር ጀቶች የሄዝቦላን ሰው አልባ አውሮፕላን አየር ላይ ሲያወድሙ የሚያሳዩ ምስሎች ጭምር እየወጡ ነው።
ሁለቱ ኃይሎች የወሰዷቸውን ወታደራዊ እርምጃዎች ተከትሎ በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን እስካሁን ድረስ አልታወቀም።
እንደ የእስራኤል መከላከያ ኃይል ከሆነ ሄዝቦላ ከ150 በላይ ተተኳሾችን ከሊባኖስ ድንበር ሆኖ ወደ እስራኤል ተኩሷል።

የፎቶው ባለመብት, EVN
የጦሩ ቃል አቀባይ ሃጋሪ እንዳሉት በምላሹ የእስራኤል አየር ኃይል በደቡባዊ ሊባኖስ በሚገኙ ዒላማዎች ላይ ድበደባዎችን እየፈጸመ ይገኛል።
ሄዝቦላ እስካሁን ድረስ 11 የእስራኤል ወታደራዊ ጣቢያዎችን ዒላማ ያደረጉ 320 ሮኬቶችን ማስወንጨፉን አስታውቋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ የደኅንነት ካቢኔያቸውን አስቸኳይ ስብሰባ መጥራታቸውን አስታውቀዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ኔታኒያሁ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮአቭ ጋላንት “ሁኔታዎችን በቴል አቪቭ ሆነው እየመሩ ነው” ብሏል።
ከእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት በኋላ በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ ውጥረት መከሰቱን ተከትሎ እስራኤል እና ሊባኖስ የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ምዕራባውያን እና በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ አገራት ቀጠናውን ወደለየት ጦርነት ሊያስገባ ከሚችል እንቅስቃሴ እስራኤል እና ሄዝቦላ እንዲታቀቡ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
የእስራኤል እና የሄዝቦላ ጦርነት አይቀሬ ነው መባሉን ተከትሎ እንደ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ፣ ጀርመን እና ፈረንሳይ ያሉ ምዕራባውያን አገራት ዜጎቻቸውን ከሌባኖስ ሲያስወጡ ቆይተዋል።












