በእስራኤል በኤርትራውያን ስደተኞች መካከል በተፈጠረ ግጭት ሁለት ሰዎች ተገደሉ

የእስራኤል ፖሊስ የተፈጠረውን ግርግር ለማረጋጋት ሲሞክር

የፎቶው ባለመብት, IL_police

በእስራኤል መዲና ቴል አቪቭ በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ሁለት ሰዎች ሲገደሉ ከአምስት ያላሱ ደግሞ ጉዳት ደረሰባቸው።

ትናንት ቅዳሜ ነሐሴ 18 2016 ዓ.ም. በተፈጠረው አምባጓሮ ኤርትራውያኑ ስደተኞች በድንጋይ እና በዱላ እርስ በእርስ መደባደባቸውን የእስራኤል ፖሊስ አስታውቋል።

ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ምስሎች በሁለት ጎራ የተከፈሉ በርካታ ወንዶች ድንጋይ ሲወራወሩ እና በዱላ ሲደባደቡ አሳይተዋል።

በማዕካላዊ ቴል አቪቭ የአውቶብስ መናኸሪያ አካባቢ በተፈጠረው ግጭት ከባድ ጉዳት ከደረሰባቸው አምስት ግለሰቦች መካከል የሁለቱ ሕይወት ማለፉ ተነግሯል።

በኤርትራውያኑ መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለመቆጣጠር የእስራኤል ፖሊስ ለማስጠንቀቅ ወደላይ ተኩሷል።

“በበርካታ ወንዶች መካከል ግጭት መቀስቀሱን የተመለከተ ሪፖርት ደረሰን። ግጭቱ ያለበት ቦታ ስንደርስ ከፍተኛ የሆነ ግጭት ተመለከትን” ሲሉ ሲምቻ ሲማንዶዬቭ የተባሉ የአደጋ ጊዜ ሠራተኛ ለታይምስ ኦፍ እስራኤል ተናግረዋል።

እስራኤልን ጨምሮ በአውሮፓ እና የሰሜን አሜሪካ ከተሞች በኤርትራውያን መካከል ደም አፋሳሽ የሆነ ግጭት ሲከሰት ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

በተለይ በእስራኤል ባለፉት ወራት ከኤርትራ የባሕል ፌስቲቫል ዝግጅት ጋር በተያያዘ በኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መካከል በሚከሰት ግጭት በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ባለፉት ወራት በጀርመን፣ በስዊድን፣ በኖርዌይ እና በካናዳ ብዙዎችን ለጉዳት የዳረገ ግጭት ተከስቷል።

ከአንድ ዓመት በፊት ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም. ም. ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች በቴል አቪቭ ከባድ ሁከት ፈጥረው በኤርትራዊያን፣ በእስራኤል ፖሊስ አባላት እና በንብረት ላይ ጉዳት ከባድ ጉዳት ደርሶ ነበር።

ከዚህ ከባድ አምባጓሮ በኋላ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ አፍሪካውያን ስደተኞች በሙሉ ‘በአስቸኳይ’ ከእስራኤል ለማባረር እቅድ እንዲወጣ ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር።

በተመሳሳይ ከትናንትው የቴል አቪቭ ሁከት በኋላ እንዲሁ የእስራኤል የብሔራዊ ደኅንት ሚኒስትር ኢራማር ቤን ጋቪር ኤርትራውያን ስደተኞች ከእስራኤል እንዲባረሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ከፍተኛ የእስራኤል ፖሊስ ኃላፊዎች እና ብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስቴር ውይይት አድርገው ከአንድ ዓመት በፊት መግባባት የተደረሰበትን ኤርትራውያን ስደተኞችን ከአገር ለማስወጣት የቀረበውን ጥያቄ የአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ እና የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ተግባራዊ እንዲያደርግ ጠይቋል።

በአሁኑ ወቅት ከ20 ሺህ የማያንሱ ኤርትራውያን ስደተኞች በእስራኤል ይኖራሉ።

እስራኤል ከእነዚህ መካከል ለጥቂቱ ብቻ የስደተኛነት እውቅና የሰጠች ሲሆን የተቀሩት ግን የኢኮኖሚ ጥገኛ ናቸው በማለት እነሱን ተቀብሎ የማኖር ሕጋዊ ግዴታ እንደሌላት ታምናለች።