በኮሪደር ልማት “ሽፋን ቤቶችን በማፍረስ” የተጠረጠሩት የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ያለመከሰስ መብት ተነሳ

የፎቶው ባለመብት, Lideta sub city communication
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት፤ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክትን ምክንያት በማድረግ አላግባብ “ስድስት የመኖሪያ እና አንድ የንግድ ቤት በማፍረስ” ቦታው “ለአፓርትመንት ገንቢ ባለሀብት” ተላልፎ እንዲሰጥ በማድረግ የተጠረጠሩ አባሉን ያለመከሰስ መብት አነሳ።
የምክር ቤት አባሉ አቶ ሰኢድ አሊ ከማል፤ ለዚህ ድርጊታቸው “ስድስት ሚሊዮን ብር ጉቦ” እንደተቀበሉም ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የአቶ ሰኢድ አሊን ያለመከሰስ መብት ያነሳው ማክሰኞ ህዳር 10/2016 ዓ.ም. እያደረገ ባለው መደበኛ ጉባኤው ላይ ነው።
ምክር ቤቱ በዛሬው ጉባኤው ከያዛቸው አራት አጀንዳዎች መካከል አንዱ ከፍትህ ሚኒስቴር በቀረበ ጥያቄ መሰረት የአንድ የምክር ቤት አባልን ያለመከሰስ መብትን የሚመለከተው ይገኝበታል።
የፍትህ ሚኒስቴር በቅርቡ የተሾሙትን ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሃና አርአያስላሴ ፊርማ በያዘ ደብዳቤ ይህንን ጥያቄ ለምክር ቤቱ ያቀረበው ትናንት ሰኞ ሕዳር 9/2017 ዓ.ም. እንደሆነ በጉባኤው ላይ በተነበበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ተጠቅሷል።
የውሳኔ ሀሳቡን በንባብ ያቀረቡት የሰላም፣ ፍትህ እና መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሙሉነህ ደሳለኝ፤ የምክር ቤት አባሉ አቶ ሰኢድ የተጠረጠሩበትን የሙስና ወንጀል ዝርዝር ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
አቶ ሰኢድ የተጠረጠሩበት የከባድ ሙስና ወንጀል ድርጊት የተፈጸመው፤ የምክር ቤት አባሉ የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው ይሰሩ በነበረበት ወቅት እንደሆነ ተገልጿል።
የቀድሞው ዋና ስራ አስፈጻሚ “እንዲፈርሱ አድርገዋል” ተብለው የተጠቀሱት ሰባት የመኖሪያ እና ንግድ ቤቶች የሚገኙት በክፍለ ከተማው ወረዳ አራት”ሳልቫቱሪ ደቬታ” በተባለ አካባቢ እንደሆነም ተጠቅሷል።
እንዲፈርሱ የተደረጉት ቤቶች “ንብረትነታቸው የመንግሥት ሆነው ነገር ግን በግለሰቦች ተከራይተው ያሉ” እንደሆነም ለምክር ቤቴ በቀረበው የወንጀል ድርጊት ዝርዝር ላይ ተነስቷል።
ዝርዝሩን በንባብ ያቀረቡት አቶ ሙሉነህ፤ የምክር ቤት አባሉ “ቤቶችን አፍርሰው ይዞታውን በቤቶቹ አጠገብ ለተሰራ ዋይልድ አፓርትመንት ህንጻ ባለቤት ለሆነው አራተኛ ተከሳሽ ምቹ በማድረግ ግንባታ እንዲገነባ እና የግሉ እንዲያደርገው ለማድረግ በማሰብ” መንቀሳቀሳቸውን በጉባኤው ላይ ተናግረዋል።
ለምክር ቤቱ የቀረበው የወንጀል ድርጊት ዝርዝር፤ አቶ ሰኢድ በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወነውን የኮሪደር ልማት “ሽፋን በማድረግ ቤቶቹ እንዲፈርሱ ማድረጋቸውን” ያስረዳል።
የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ሙሉነህ፤ “በልደታ ክፍለ ከተማ ውስጥ ከሜክሲኮ እስከ ቄራ ላለው ዋና መንገድ ማስፋፊያ የኮሪደር ልማት LDP ጥናት መሰረት የሚሰራውን የኮሪደር ልማት ሽፋን በማድረግ በዚህ የኮሪደር ልማት መስመር ፕሮጀክቱ ውጪ” ቤቶቹ መፍረሳቸውን ገልጸዋል።
በ503 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፉት እነዚህ ሰባት ቤቶች እንዲፈርሱ የተደረጉት “በውስጣቸው ግለቦች እየኖሩበት እና ንግድ እየተከናወነ ባለበት እንዲሁም የከተማው ካቢኔ ቤቶቹ እንዲፈርሱ ባልወሰነበት” ሁኔታ እንደሆነ ተጠቅሷል።
በቀድሞው የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ፤ የመኖሪያ እና ንግድ ቤቶቹ እንዲፈርሱ “ሰራተኞችን ሰብስበው ውሳኔ እና ትዕዛዝ እንደሰጡ” እንዲሁም ቦታው ላይ በአካል በመሄድ ጭምር እንዲፈርስ መመሪያ እና ትዕዛዝ” እንዳስተላለፉም ተነግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Mayor Office of Addis Ababa
በቤቶቹ ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ግለሰቦች 3.37 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ስድስት የጋራ መኖሪያ ቤቶች “እንዲሰጥ ማድረጋቸውም” ከምክር ቤት አባሉ ድርጊቶች መካከል ተጠቅሷል።
ቤቶቹ ይገኙ የነበሩበት ቦታ በአንጻሩ “ሀጂ በገን ሀይሩ ነጋሽ ለተባለ እና በአካባቢው አፓርትመንት ላለው ግለሰብ እንዲሰጥ እና ግንባታ እንዲገነባበት” እንደተደረገ ተገልጿል።
የቀድሞው የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ለዚህ ድርጊታቸው “ሀጂ በገን ሀይሩ” ከተባሉት ባለሀብት “ስድስት ሚሊዮን ብር ጉቦ በባለቤታቸው ስም” በመቀበል ተወንጅለዋል።
አቶ ሙሉነህ፤ “[የምክር ቤት አባሉ] የተቀበለውን ስድስት ሚሊዮን ብር ከሌላ ግለሰብ ከተላለፈው ስምንት ሚሊዮን ጋር በመቀላቀል በባንክ ብድር ለገዛው እና ግምቱ 30 ሚሊዮን ለሚያወጣው ቤት 14 ሚሊዮን ለቤቱ ግዢ ብድር ክፍያ በመፈጸም የሙስና እና ሕገ ወጥ ገንዘቡን ሕጋዊ አድርጎ በማቅረብ ወንጀል መፈጸም ምርመራ እየተጣራበት ይገኛል” ሲሉ ገንዘቡ ምን ላይ እንደዋለ አብራርተዋል።
ይህንን ምርመራ ያከናወነው የፍትህ ሚኒስቴር፤ “ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች እና ሀጂ በገን ሀይሩ ነጋሽ የተባሉት ባለሀብት” ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት አንደኛ ፀረ ሙስና ወንጀል ችሎት ክስ እንደመሰረተ ተገልጿል።
አቶ ሰኢድ ግን የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል በመሆናቸው በሚያገኙት ያለመከሰስ መብት ምክንያት “ክስ ለማቅረብ እንዳልተቻለ” የጠቀሰው የፍትህ ሚኒስቴር፤ የግለሰቡ ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ጠይቋል ተብሏል።
ለምክር ቤት የቀረበውን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ጥያቄ የመመልከት ኃላፊነት የተጣለበት የሰላም ፍትህ እና መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ የሕግ እና የማስረጀ ማጣራቶችን ማድረጉን ሰብሳቢው አቶ ሙሉነህ በጉባኤው ላይ ተናግረዋል።
ቋሚ ኮሚቴው፤ “በፍትህ ሚኒስቴር የተጠቀሱ መረጃዎች ከባድ የሙስና ወንጀል አመላካች” ሆነው ስላገኛቸው የምክር ቤት አባሉ አቶ ሰኢድ ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል።
ይህ የውሳኔ ሀሳብ የቀረበለት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳቡን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
አራተኛ የስራ ዘመኑ ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ምክር ቤት የአባሉን ያለመከሰስ መብት ሲያነሳ ይህ ለአራተኛ ጊዜ ነው። ከጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ አወጣጥ ሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩት የምክር ቤት አባሉ አቶ ሙሉቀን ሀብቱ በ2014 ዓ.ም. ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ ነበር።
በጥቅምት 2015 ዓ.ም. ደግሞ ወ/ሮ ሀቢባ ዑመር የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በነበሩበት ወቅት “አርሶ አደር እና የአርሶ አደር ልጅ ያልሆኑ ሰዎችን የመሬት ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ” ተጠርጥረው ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቷል።
ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው ሶስተኛው የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ዶ/ር ካሳ ተሻገር ናቸው።
ዶ/ር ካሳ ባለፈው ዓመት የካቲት ላይ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው “በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀስ ጸረ ሰላም ኃይል” በተያያዘ ተጠርጠረው ነበር።












