የንጽህና አጠባበቅን የቀየሩ አምስት አፍሪካዊ ፈጠራዎች

የናይጄሪያው በፀሐይ ብርሃን (ሶላር) የሚሠራው የውሃ ጉድጓድ
የምስሉ መግለጫ, የናይጄሪያው በፀሐይ ብርሃን (ሶላር) የሚሠራው የውሃ ጉድጓድ

ንጹህ ውሃ፣ የንጽህና አጠባበቅ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የአህጉሪቷ ሕዝቦች መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው።

ቢቢሲ በተለያዩ ማኅበረሰቦች ውስጥ ያሉ በንጽህና አጠባበቅ ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶችን በሚችሉት ለመቅረፍ እየሠሩ ያሉ ፈጠራዎችን ዳሷል።

ይህ ሪፖርት ከቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተዘጋጀ ነው።

የናይጄሪያ በፀሐይ ሃይል (ሶላር) የሚሠራው የውሃ ጉድጓድ

በዓለም አቀፍ ደረጃ 2.2 ቢሊዮን የሚሆኑ የዓለማችን ሕዝቦች የንጹህ መጠጥ ውሃ እንደማያገኙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ይፋ አድርጓል።

ንጹህ ውሃ ከጤና እና ከምጣኔ ሀብት በረከቶቹ በተጨማሪ ማኅበረሰቦች እንዲበለጽጉ እና የፆታ እኩልነትን በማጎልበት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል።

በበርካታ ማኅበረሶች ውስጥ ውሃ የመቅዳት ኃላፊነት በታዳጊዎች እና በሴቶች ጫንቃ ላይ ከመውደቁ ጋር ተያይዞ ከሥራቸው እና ከትምህርታቸው ያስተጓጉላቸዋል። ንጹህ ውሃ በአቅራቢያ መገኘት ይህንን ክፍተት ይቀርፋል።

በገጠሪቷ ናይጄሪያ በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ የውሃ ጉድጓዶችን በማምጣት የማኅበረሰቡን ሕይወት እየቀየሩ ያሉት የጂኦሎጂ ባለሙያው ኦንያዲካቺ ኤሬቴ ናቸው።

የኤሌክትሪክ ኃይል ውድ በሆነበት ወይም ተደራሽነቱ በተመናመነት አካባቢ የሚገኘው ይህ የፀሐይ ብርሃን ኃይልን በመጠቀም ውሃ የሚያመነጨው የውሃ ጉድጓድ ለአካባቢው የውሃ እጥረት ዘላቂ መፍትሄ አምጥቷል።

እያንዳንዱ የውሃ ጉድጓድ እስከ 20 ሺህ ለሚሆኑ ነዋሪዎች አገልግሎት ይሰጣል። ፕሮጀክቱ ገና በጅምር ላይ እና ያልተጠናቀቀ ቢሆንም እስካሁን ያሉ የሶላር የውሃ ጉድጓዶች ከ70 ሺህ በላይ የሚሆኑ ናይጄሪያውያን ንጹህ ውሃ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።

የኡጋንዳ የሽንት ቤት ፍሳሽ ማስወገጃ መተግበሪያ

የኡጋንዳ የሽንት ቤት ፍሳሽ ማስወገጃ መተግበሪያ
የምስሉ መግለጫ, የኡጋንዳ የሽንት ቤት ፍሳሽ ማስወገጃ መተግበሪያ

በአንድ ከባቢ ውስጥ መሠረታዊ የሆነ የንጽህና አጠባበቅ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ከሌለ ብክለትን ያስከትላል። እንዲሁም የሕብረተሰቡን ጤና እና ደኅንነት አደጋ ላይ ይጥላል።

በኡጋንዳ መዲና ካምፓላ አብዛኛው ማኅበረሰብ የሚኖርባቸው መኖሪያ ቤቶች ከማዕከላዊው የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ሥርዓት ጋር የተገናኙ አይደሉም። ነገር ግን ‘ዌዮንጄ’ የተሰኘ መተግበሪያ ነዋሪዎች የሽንት ቤት ፍሳሻቸውን ለማስወገድ ሲፈልጉ የማስወገጃ መኪና የሚያዙበት ነው።

መኪናው የነዋሪዎችን የሽንት ቤት ፍሳሽን በማስወገድ የነዋሪዎችን ኑሮ እያቀለለ ይገኛል። ይህንን መተግበሪያውን የፈጠሩት በከተማዋ አስተዳደር ባለሥልጣን በሕዝብ ጤና ላይ የሚሠሩት ኡኒስ ናሚሬምቤ ናቸው። መተግበሪያው ሌሎች እንዲያሻሽሉት ተደርጎ ነው የተሠራው።

በማላዊ መጸዳጃ ቤቶችን በጋራ የሚገነቡት ሴቶች

በማላዊ መጸዳጃ ቤቶችን በጋራ የሚገነቡት ሴቶች
የምስሉ መግለጫ, በማላዊ መጸዳጃ ቤቶችን በጋራ የሚገነቡት ሴቶች

አብዛኛው የማላዊ የገጠር አካካቢ ንጹህ መጸዳጃ የሌላቸው በመሆናቸው በርካቶች ንጽህና በጎደላቸው ሁኔታዎች በክፍት ስፍራዎች ለመጸዳዳት ተገደዋል።

ይህም ሁኔታ አካባቢዎች እንዲበከሉ እንዲሁም በአቅራቢያ ያሉ ነዋሪዎች ጤናን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታን ፈጥሯል።

የመጸዳጃ ቤቶቹን እጥረት ለመቅረፍ በማዕከላዊ ማላዊ ነዋሪ የሆኑ ሴቶች በጋራ መጸዳጃ ቤቶችን መገንባት ጀምረዋል። ቾማ በሚል ስያሜ የተሰባሰቡት ሴቶች ጡብን በመጠቀም መጸዳጃ ቤቶችን በልዩ ዲዛይን እየገነቡ ነው።

መጸዳጃ ቤቶቹ ከመኖሪያ ቤቶች እና ከውሃ ምንጮች በቅርብ ርቀት ላይ በመገኘታቸው ከባህላዊ መጸዳጃ ቤቶች በበለጠ ዘላቂነት ያላቸው እና ንጽህናቸው የተጠበቀ ነው።

የሴቶቹ ግንባታ በአካባቢው የውሃ ወለድ በሽታዎች እንዲያሽቆለቁሉ ምክንያት እንደሆነም ተገልጿል።

ፋሽን ከተጣሉ የፕላስቲክ ምርቶች በጋና

ፋሽን ከተጣሉ የፕላስቲክ ምርቶች በጋና
የምስሉ መግለጫ, ፋሽን ከተጣሉ የፕላስቲክ ምርቶች በጋና

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚከተለው የጎርፍ መጥለቅለቅ በበርካታ አካባቢዎች ጨምሯል።

በጋና መዲና አክራ ዶም በተሰኝው ስፍራ ያሉ የውሃ መፋሰሻዎች ተዘግተዋል። ውሃ፣ ቆሻሻ እና የመጸዳጃ ፍሳሾች የተለያዩ ሰዎች መኖሪያ ቤቶችን እየበከሉ ነው።

ለዚህም ዋነኛው ምክንያቱ የፕላስቲክ ውሃ መያዣዎች ናቸው። እነዚህን የፕላስቲክ የውሃ መያዣዎች አጥበው እንደገና ወደ ቦርሳ የሚቀይሩ ጋናውያን ሴቶች ብቅ ብለዋል።

ይህ ፕሮጀክት ከባቢን ከማጽዳት ባለፈ ለሴቶቹም የሥራ ምንጭ ሆኖላቸዋል።

ይህንን ፕሮጀክት የጠነሰሱት ከአውሮፓውያኑ 2019 ጀምሮ የፕላስቲክ ብክለትን ለመከላከል ወደ ፋሽን ምርቶች እየለወጠ ያለው የራማፕላስት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አውራማ ኬና አሲየዱ ናቸው።

በሩዋንዳ የወር አበባ መገለልን ለመቅረፍ የሚጥረው ክለብ

በሩዋንዳ የወር አበባ መገለልን ለመቅረፍ እየሰራ ያለው ክለብ
የምስሉ መግለጫ, በሩዋንዳ የወር አበባ መገለልን ለመቅረፍ እየሰራ ያለው ክለብ

በበርካታ አፍሪካ አገራት የወር አበባ ነውር ነው፤ መገለልም ያመጣል። በአፍሪካ 20 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ትምህርት ቤት የሚቀሩበት እና ፈተና የማይፈተኑባቸው ምክንያት በወር አበባ የንጽህና መጠበቂያ እና መገልገያ እጥረት መሆኑን የዓለም ባንክ ገልጿል።

በሩዋንዳ ጂኤስ ንታራማ የተሰኘ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ይህንን ችግር ለመቅረፍ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

ከውሃ፣ ከአካባቢ ጽዳት እና ከግል ንጽሃና አጠባበቅ ጋር የተያያዘ ደብልዩ ኤስ ኤች የተሰኘ ክለብ በማቋቋም የወር አበባን በተመለከተ የሬድዮ ድራማዎችን በማዘጋጀት ግልጽ ውይይት እንዲኖር እያበረታቱ ይገኛሉ።

እነዚህ ፕሮግራሞች ድጋፍ እንዲያገኙ ያደረጉ ሲሆን፣ ለሴት ተማሪዎች አዲስ ሽንት ቤት፣ ሻወር፣ እና የሚያርፉባቸው አልጋዎች እና ደኅንነታቸው የተጠበቁ ቦታዎች እንዲኖሯቸው አድርገዋል።

የእነዚህ ደኅንነታቸው የተጠበቁ ቦታዎች መኖር ሴት ተማሪዎች ትምህርት ቤት እንዳይቀሩ አድርጓቸዋል። በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎችም ይህንኑ ለመተግበር እየተሞከረ ይገኛል።