በኢትዮጵያ ሴቶች ለወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ከፍተኛ ወጪ እንደሚያወጡ ጥናት አመለከተ

የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኢትዮጵያ ሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ለመግዛት ከሚያገኙት ገቢ አንጻር ከፍተኛ ወጪ እንደሚያወጡ የቢቢሲ ጥናት አመለከተ።

ቢቢሲ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ዋጋ ምን ያህል ተመጣጣኝ እንደሆነ ለማየት አፍሪካ ውስጥ በሚገኙ ዘጠኝ አገራት ላይ በሰራው ጥናት ከጋና በመቀጠል ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሴቶች ከፍተኛ ወጪ እንደሚያወጡ አመልክቷል።

ጥናቱ ዝቅተኛ ወርሃዊ ገቢን ከርካሽ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን ዋጋ ጋር ያነጻጸረ ሲሆን፣ በዚህም የምርቶቹ ዋጋ የበርካታ ሴቶችን አቅም ያገናዘቡ አለመሆናቸውን ደርሶበታል።

ጋና፣ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ኡጋንዳ ፣ ናይጄሪያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኬንያን የዳሰሰው ጥናቱ፣ በጋና ዝቅተኛ ደመወዝ ያላቸው ሴቶች ከሚያገኙት ገቢ ከፍተኛ የተባለውን ወጪ የሚያወጡ ሲሆን ኬንያ ደግሞ በአንጻሩ ምርቶቹ ርካሽ የሆነባት አገር ሆናለች።

ቢቢሲ ጥናቱን ካካሄደባቸው ዘጠኝ አገራት መካከል በስድስቱ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሴቶች በየወሩ እያንዳንዳቸው ስምንት ነጠላ ሞዴሶችን የያዙ ሁለት እሽግ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን ለመግዛት ከደመወዛቸው ከ3 እስከ 13 በመቶ የሚሆነውን ማውጣት ይጠበቅባቸዋል።

እንደ ጥናቱ ከሆነ በጋና አንዲት ሴት ከምታገኘው ዝቅተኛ ደመወዝ ተብሎ ከተቀመጠው 26 ዶላር ውስጥ ሦስቱን ዶላር ወይም ከሚያገኙት 7 ዶላር ውስጥ አንዱን፣ ሁለት እሽግ የንጽህና መጠበቂያ ምርት ለመግዛት ታወጣለች።

ይህም በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም ካሉ ሴቶች ጋር ሲነጻጻር እጅግ ከፍተኛ ነው።

በአሜሪካ ሴቶች ከሚያገኙት 1 ሺህ 200 ዶላር ዝቅተኛ ገቢ የንጽህና መጠበቂያ ምርት ለመግዛት የሚያወጡት 3 ዶላር ብቻ ነው።

በኢትዮጵያ ደግሞ አንዲት ሴት ከምታገኘው ገንዘብ በአማካይ ስድስት በመቶውን ለሞዴስ ታወጣለች ብሏል ጥናቱ።

በአፍሪካ ያሉ ሴቶች በወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች እጦት እየተሰቃዩ ሲሆን ተሟጋቾችም ይህንን ለመቀየር እየጣሩ ነው።

በአፍሪካ ሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ለመግዛት ምን ያህል እንደሚያወጡ የሚያሳይ

የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ውድ በሆኑባቸው አገራት ልጃገረዶችና ሴቶች ጨርቆችን፣የሲሚንቶ ወረቀት ከረጢት እና የደረቀ የሙዝ ግንድ ለመጠቀም ይገደዳሉ።

በርካታ የወር አበባ ጤና ተሟጋቾችም በንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ላይ የሚጣለው ቀረጥ መነሳት ሴቶች አቅማቸው በሚፈቅደው መጠን ምርቶቹን መግዛት እንዲችሉ ያስችላል ሲሉ ይሟገታሉ።

በኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት በመሰረታዊ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ላይ የቀረጥና የታክስ ማሻሻያ ማድረጓን የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር።

በዚህ ውሳኔ መሠረትም እነዚህ የሴቶችና የህጻናት ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ከውጭ ተመርተው ሲገቡ ቀደም ሲል ተጥሎባቸው የነበረው የ30 በመቶ ከፍተኛ የታክስ ምጣኔ ተቀንሶ ወደ 10 በመቶ ብቻ እንዲሆን መደረጉን ሚኒስቴሩ መግለጹ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ እስካሁን ተግባራዊ አልተደረገም።

ጎረቤት አገር ኬንያ በወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን ከቀረጥ ነጻ በማድረግ ከዓለም የመጀመሪያዋ አገር የሆነችው እንደ አውሮፓውያኑ 2004 ነበር።

ከሁለት ዓመት በኋላም የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን ለማምረት የሚውሉ ጥሬ እቃዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲሆኑ አድርጋለች።

በዚህም ምክንያት በኬንያ ያለው የንጽህና መጠበቂያ ዋጋ ቀንሷል። አሁን ላይ ርካሹ የንጽህና መጠበቂያ (ሞዴስ) በ35 የአሜሪካ ሳንቲም ይሸጣል።

ሆኖም ሴት ፖለቲከኞች እና ተሟጋቾች ምርቶቹ ከዚህ ያነሰ ዋጋ ለተገልጋዮች እንዲቀርቡ አሁንም እየጠየቁ ነው።

ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, TOKO MASEMOLA/CHANGE.ORG

የምስሉ መግለጫ, ሴቶች በንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ዋጋ መወደድ ምክንያት በጋና እና በሌሎች አገራት ተቃውሞ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሌላ በኩል ምርቶቹን ከቀረጥ ነጻ ማድረግ ብቻ በቂ አይደለም፤ ምርቶቹ በርካሽ ለተጠቃሚዎች መቅረቡን ማረጋገጥ ያስፈልጋል የሚሉም አሉ።

በ2019 የታንዛኒያ መንግሥት በንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ላይ አንስቶት የነበረውን ቀረጥ መልሶ መጨመሩን አስታውቆ ነበር።

ምክንያቱ ደግሞ ተጠቃሚዎች ምርቶቹ በሱቆችና በገበያዎች ዋጋቸው አልቀነሰም ሲሉ ቅሬታ በማቅረባቸው ነው።

ተሟጋቾች ግን የምርቶቹ ዋጋ ያልቀነሰው የገበያው ሰንሰለት እንዲረጋጋ በቂ ጊዜ ሳይሰጥ መልሶ ቀረጥ ስለተጣለባቸው ነው ይላሉ።

በአፍሪካ እንዲሁም በዓለም በንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ዋጋ ከፍተኛ መሆን አሊያም በገጠራማ አካባቢዎች አለመድረስ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሴቶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አስከትሏል።

ምን ያህል ሴት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንደሚያቋርጡ የሚያሳይ ዓለም አቀፋዊ ጥናት ባይኖርም፣ የተለያዩ አገራት በሰሩት ጥናት በዓመት በሺዎች የሚቆጠሩ ሴት ተማሪዎች በርካታ ቀናት ከትምህርት ቤት ይቀራሉ።

በኬንያ 95 በመቶ የሚሆኑ ልጃ ገረዶች በወር ከአንድ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ከትምህርት ቤት የሚቀሩ ሲሆን ሌሎች 70 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በውጤታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረባቸው ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲሆኑ እና የሚታጠብ የንጽህና መጠበቂያዎችን ለማዳረስ የሚሰራው ጀግኒት ኢትዮጵያ መሥራች ማራኪ ተስፋዬ እንዳለችው በኢትዮጵያ በአንድ ዓመት አንዲት ልጃገረድ 100 ቀናት ከትምህርት ቤት ትቀራለች።

እንደ የዓለም ባንክ ከሆነ በዓለም 500 ሚሊዮን ሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን አያገኙም።

ከዚህም በተጨማሪ ንጽህናቸውን ለመጠበቅ የሚያስችሉ እንደ ውሃ እና መጸዳጃ ቤቶች ያሉ መሠረተ ልማቶችም እጦት አለባቸው።