የሶማሊያውን ፕሬዝዳንት ተከትለው የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ወደ አዲስ አበባ ማምራታቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Foreign Affairs - Somaliland
ነጻ አገርነቷን ያወጀችው የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዱራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ የካቢኔ አባሎቻቸውን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ዛሬ ረፋዱ ላይ ማቅናታቸውን የጽህፈት ቤታቸው አስታወቀ።
ሶማሊያ የግዛቷ አካል አድርጋ የምትመለከታት የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ወደ ኢትዮጵያ ማምራታቸው የተነገረው የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በአዲስ አበባ ጉብኝት ካደረጉ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
ከፕሬዝዳንቱ ጋር የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የገንዘብ ሚኒስትር፣ የአገሪቱ ጦር አዛዥ እንዲሁም የብሔራዊ ደኅንነት ኃላፊዎች አብረው ወደ አዲስ አበባ ያቀኑ መሆናቸው ተገልጿል።
ማክሰኞ ጥቅምት 4 2018 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ከሐርጌሳ በተነሳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ ሲሳፈሩ የታዩት የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት የአዲሰ አበባ ጉዞ በተመለከተ እስካሁን ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩለ የተባለ ነገር የለም።
የሶማሊላንድ መንግሥት ቃል አቀባይ ባወጣት መግለጫ ላይ የፕሬዝዳንቱ ጉዞ የሁለቱ አገራትን ግንኙነት በተለይ በደኅንነት፣ በምጣኔ ኃብት፣ በንግድ እና በትራንስፖርት መስኮች ለማጠናከር ያለመ ነው ብሏል።
ፕሬዝዳንት አብዱራሀማን ሞሐመድ አብዱላሂ ወደ አዲስ አበባ ሲሄዱ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር አወዛጋቢ የተባለ የወደብ ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ በአዲሱ የአገሪቱ መሪ የተደረገ የመጀመሪያ ጉዞ ነው።
የፕሬዝዳንቱ የአዲስ አበባ ጉብኝት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ አዲስ አበባን ጎብኝተው በተመለሱ በኋላ የተሰማ ነው።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተነጥላ ነፃ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ታኅሳስ 22/2016 ዓ.ም. የባሕር በር ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፤ ስምምነቱ ውዝግብ እና ተቃውሞ ገጥሞታል።
ስምምነቱ ለኢትዮጵያ "የኅልውና ጉዳይ ነው" የተባለውን የወደብ ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ሲሆን፤ በዚህ ስምምነት ኢትዮጵያ "የሰጥቶ መቀበል" መርኅ እንደምትከተል ባለሥልጣናት በወቅቱ ተናግረዋል።
በወደቡ ፋንታ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ በመጠን ያልተገለፀ ድርሻ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደምትሰጥ ተዘግቦ ነበር።
ከዚህም ባሻገር የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች ኢትዮጵያ ለአገሪቱ ከየትኛውም አገር ያላገኘችውን የአገርነት እውቅና እንደምትሰጥ ሲናገሩ ነበር።
ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ከሶማሊያ ተነጥላ ነጻ አገርነቷን በማወጅ የአገርነት ሥርዓትን የገነባቸው ሶማሊላንድ በዓለም አገራት ዘንድ ዕውቅናን ለማግኘት ጥረት እያደረገች ነው።
ሶማሊያ ግን ሶማሊላንድ የግዛቷ አካል በመሆኗ ነጻ አገርነቷን አትቀበለውም።ከኢትዮጵያ ጋር የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነትንም አጥብቃ ተቃውመዋለች።
በዚህ የመግባቢያ ስምምነት ኢትዮጵያ 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ እንደምታገኝ የተገለፀ ሲሆን፤ በወቅቱ መንግሥት ኢትዮጵያ "የወደብ ባለቤት" መሆኗን በእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ማብሰሩ አይዘነጋም።
ይሁን እንጂ የስምምነቱ ይዘት ከሁለት ዓመታት ገደማ በኋላም በግልፅ አይታወቅም።
ስምምነቱ በተለይም ሶማሊላንድ የግዛቴ አካል ናት በምትለው በሶማሊያ እና በቀጣናው ውጥረት እንዲነግስ ያደረገ ሲሆን፤ የሁለቱ አገራት ወዳጅ የሆነችው ቱርክ ውጥረቱን ለማርገብ አደራድራ ከስምምነት እንዲደርሱ አድርጋለች።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ እሁድ ዕለት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር "በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች" ላይ መወያየታቸው ብቻ የተነገረ ሲሆን፣ ስለውይይታቸው ዝርዝር ይዘት በይፋ አልተደረገም።
ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 4/2018 ዓ.ም. የሶማሊላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፕሬዝዳንት አብዱላሂ በኢትዮጵያ አገር መንገድ አውሮፕላን ተሳፍረው ወደ አዲስ አበባ ጉዞ መጀመራቸውን አስታውቋል።
የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሰው ፕሬዝዳንቱ በቀረበላቸው ይፋዊ ግብዣ ወደ አዲስ አበባ ማቅናታቸውን እና ጉብኝቱ ከሁለት እስከ ሦስት ቀናት እንደሚቆይ ጠቁመዋል።
የሶማሊላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማኅበራዊ የትስስር ገፁ የጉብኝቱ ዓላማ የአገራቱን ትብብር እና ግንኙነት ለማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።
የሶማሊላንድ አዲሱ ፕሬዝዳንት የተመረጡ ሰሞን አገራቸው እና ኢትዮጵያ የተፈራረሙትን ስምምነት በሚመለከት መንግሥታቸው ጊዜ ወስዶ እንደሚመለከተው ተናግረው ነበር።
በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል የተባለው የመግባቢያ ስምምነት ለሁለት ዓመታት ገደማ የዘገየው በጫና ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ይታመናል።
መዘግየቱን በሚመለከት ስምምነቱን የተፈራረሙት እና በተቀናቃኛቸው በምርጫ ተሸንፈው የተሰናበቱት የሶማሊላንድ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሙሳ ቢሂ "ምንም ነገር ሳይቀየር በነበረበት እንዳለ ነው። በመግባባት ደረጃ ላይ ነው ያለው። ሁሉም ወገን የተግባራዊነት ሰነዱ መቼ እንሚፈረም እየተጠባበቀ ነው" ብለው ነበር።















