ቀጥታ, ቻይና፣ ሩሲያና ሌሎች የዓለማችን መሪዎች ማዱሮ ስለመያዛቸው ምን አሉ?

ቬኒዙዌላ ላይ ድንገተኛ የኮማንዶ ጥቃት በመፈጸም አገሪቱ መሪ በአሜሪካ እጅ መግባታቸውን በተመለከተ ፕሬዝንት ትራምፕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “አስተማማኝ፣ ተገቢ እና ሕጋዊ ሽግግር እስኪካሄድ ድረስ ቬንዙዌላን አሜሪካ ታስተዳድራለች” ሲሉ በኩራት ተናግረዋል። ማዱሮ መያዛቸውን ተከትሎ የዓለማችን መሪዎች የተደበላለቀ ምላሽ ሰጥተዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በናይጄሪያ አንድ መንደር ላይ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 30 ሰዎች ተገደሉ

    በናይጄሪያ ኒጀር ግዛት የደረሰ ቃጠሎ

    የፎቶው ባለመብት, Zakari Kontagora

    በናይጄሪያ ኒጀር ግዛት ውስጥ በሚገኝ መንደር የታጠቁ ኃይሎች በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ 30 ሰዎችን መገደላቸውን እና ንብረት መዘረፉን የክልሉ ባለስልጣናት ተናገሩ።

    ጥቃት ፈጻሚዎቹ ቅዳሜ ዕለት ከካሱዋን-ዳጂ መንደር አቅራቢያ ከሚገኝ ጫካ ወጥተው የአካባቢውን ገበያ ማቃጠላቸውን፣ ሱቆችን መዝረፋቸውን እና ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎችን አፍነው መውሰዳቸውን ፖሊስ አስታውቋል።

    "ታጣቂዎቹ በሞተር ሳይክሎች መሳሪያ ይዘው ወደ ከተማው ከገቡ በኋላ ሰዎችን በመክበብ ረሽነዋቸዋል፤ ሌሎቹ ደግሞ በጥይት ተመትተው ሞተዋል።" ሲል የአካባቢው ነዋሪ ለቢቢሲ ሃውሳ ተናግሯል።

    ናይጄሪያ ውስጥ ሽፍቶች በመባል የሚታወቁት የታጠቁ የወንጀል ቡድኖች የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች እና አፈናዎች ለዓመታት እንደቀጠሉ ናቸው።

    የኒጀር ግዛት የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ኤጀንሲ ባለሥልጣን የሆኑት አብዱላሂ ሮፊያ የነዋሪዎችን እማኝነት በመጥቀስ የመንደሩ ነዋሪዎች ከበባ ከተፈጸመባቸው በኋላ መገደላቸውን አረጋግጠዋል።

    የአካባቢው ማኅበረሰብ ጥቃቱን ተከትሎ በጣም ፈርቶ እንደነበር የተናገሩት ባለሥልጣኑ "ተደብቀው ነው ያሉት፤ ከማንም ጋር ለመነጋገር በጣም ይፈራሉ" ሲሉ አክለዋል።

    የኒጀር ግዛት የፖሊስ ቃል አቀባይ ዋሲዩ አቢዮዱን ጉዳት የደረሰባቸውን ነዋሪዎች ለመርዳት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ወደ አካባቢው መሰማራታቸውን እና የጸጥታ ኃይሎች የታገቱትን ለማስለቀቅ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

    ናይጄሪያ ውስጥ መንግሥት አሸባሪ ብሎ በፈረጃቸው የወንጀል ቡድኖች የታገቱ ሰዎችን ለማስለቀቅ ገንዘብ መክፈል ሕገ-ወጥ ድርጊት ነው።

  2. የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን በተመለከተ "ማስፈራራታቸውን" እንዲያቆሙ ጠየቁ

    በግሪንላንድ የሚገኙ ቤቶች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን ስለመቆጣጠር "የሚሰነዝሩትን ዛቻ እንዲያቆሙ" ጠየቁ።

    ሜቴ ፍሬድሪክሰን “ዩናይትድ ስቴትስ ግሪንላንድን ለመጠቅለል ስላላት ፍላጎቷ ማውራቷ ፈጽሞ ትርጉም የለውም” ሲሉ ተናግረዋል። “አሜሪካ በዴንማርክ መንግሥት ውስጥ ካሉት ሦስት ግዛቶች አንዱን የመገንጠል መብት የላትም” ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሯ ይህንን አስተያየት የሰጡት ከትራምፕ ረዳቶች አንዱ የሆኑት የስቴፈን ሚለር ባለቤት ኬቲ ሚለር በግሪንላንድ ካርታ ላይ የአሜሪካን ባንዲራ ያስቀመጠ እና "በቅርቡ" የሚል ጽሁፍን የያዘ ልጥፍ በትዊተር ገጻቸው ላይ ካጋሩ በኋላ ነው።

    ትራምፕ ግሪንላንድ ያላትን ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ እና የማዕድን ሀብቷን በመጥቀስ ከአሜሪካ ጋር ልትቀላቀል እንደምትችል በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ፍሬደሪክሰን አስተያየት ከሰጡ በኋላ ደግሞ ትራምፕ ግዛቲቱ ለአሜሪካ ትገባለች የሚለውን ንግግራቸውን አጠንክረው ቀጥለዋል።

    ፍሬደሪክሰን በዴንማርክ መንግሥት ድረ ገጽ ላይ ባሰፈሩት መግለጫ ለአሜሪካ “በቀጥታ” መልዕክት እያስተላለፉ እንደሆነ ተናግረዋል።

    “አሜሪካ ታሪካዊ የቅርብ አጋሯ በሆነች አገር ላይ እንዲሁም ሌላ አገር እና ሌላ ሕዝብ በግልጽ ለሽያጭ አይቀርብም እያለ ባለበት ማስፈራራቷን እንድታቆም አበክሬ እጠይቃለሁ።”

    ጠቅላይ ሚኒስትሯ ይህንን ካሉ ከሰዓታት በኋላ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በኤርፎርስ ዋን ላይ ሆነው “ግሪንላንድን የምንፈልገው ከብሔራዊ ደህንነት አንጻር ነው። ዴንማርክ ደግሞ ያንን ማድረግ አትችልም” ብለዋል።

    ከዚህ አስቀድሞ በአሜሪካ የዴንማርክ አምባሳደር ሁለቱ አገራት የቅርብ አጋር መሆናቸውን “ማስታወስ እፈልጋለሁ” ካሉ በኋላ አሜሪካ የዴንማርክን የግዛት አንድነት አንድታከብር ጠይቀዋል።

    በሁለቱ አገራት መሪዎች መካከል ይህ የቃላት ምልልስ የተሰማው አሜሪካ ቅዳሜ ዕለት በቬንዚዌላ ወታደራዊ ዘመቻ ካካሄደች እና ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ እና ባለቤታቸውን በቁጥጥር ሥር ካዋለች በኋላ ነው።

    ትራምፕ በኋላ ላይ አሜሪካ ቬንዙዌላን "እንደምትመራ" እና የአሜሪካ የነዳጅ ኩባንያዎች "ለአገሪቱ ገንዘብ ማስገኘት እንደሚጀምሩ" ተናግረዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ቀደም ሲል በአርክቲክ ውስጥ የምትገኘውን ግዙፍ ደሴት፣ ግሪንላንድን ለመቆጣጠር ኃይል መጠቀምን እንደ አማራጭ እንደማይቀርብ በግልጽ አልተናገሩም ነበር።

    የትራምፕ አስተዳደር በቅርቡ ለግሪንላንድ ልዩ መልዕክተኛ የሾመ ሲሆን ይህም ዴንማርክን አስቆጥቷል።

    57 ሺህ ሕዝ ያላት ግሪንላንድ እአአ ከ1979 ጀምሮ ራሷን በራሷ ታስተዳድራለች።

    የውጭ ጉዳይ እና መከላከያን በሚመለከት ግን ሙሉ ኃላፊነት ያለበት የዴንማርክ መንግሥት ነው።

  3. ማዱሮ ወደ አስር ቤት፣ ትራምፕ ቬንዙዌላን ወደ “መምራት” እንዴት ደረሱ?

    ማዱሮ ተይዘው አሜሪካ በደረሱበት ጊዜ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ከእኩለ ሌሊት በኋላ የአሜሪካ ዴልታ ፎርስ ኮማንዶዎች በቬንዙዌላ ዘመቻ ከፍተው ፍንዳታዎች እና የሄሊኮፕተሮች ድምጽ በዋና ከተማዋ ካራካስ ውስጥ ከተሰማ ከሰዓታት በኋላ ለወራት ሲብላላ የነበረው የትራምፕ እና የማዱሮ ውዝግብ ፍጻሜ ሆነ።

    ቬንዙዌላውያን እና ቀሪው ዓለም ምን እንደተከሰተ በቅጡ ሳይረዳ ከቅዳሜ ዕኩለ ቀን በኋላ ጠንከር ያሉ እና በፍጥነት የሚቀያየሩ መረጃዎች ከአሜሪካ በኩል መውጣት ጀመሩ። ዋና ዋናዎቹ. . .

    • በቬንዙዌላዋ ዋና ከተማ ሰማይ ላይ እሳት እና ጭስ ሲታይ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ “መጠነ ሰፊ ዘመቻ” እያካሄደች እንደሆነ አረጋገጡ
    • ትሩዝ ሶሻል በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረካቸው የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ እና ሚስቸታው ሲሊያ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገለጹ
    • ይህንንም ተከትሎ የቬንዙዌላ መንግሥት አገር አቀፍ አስቸኳይ ጊዜ ሲያውጅ፣ የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር ጦር ሠራዊቱን በአስቸኳይ ለግዳጅ ማሰመራቱን አስታወቀ
    • ትራምፕ ኒኮላስ ማዱሮ የተያዙበትን ሁኔታ በተመለከተዝርዝር መረጃ ይፋ አደረጉ
    • የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፓም ቦዲ ማዱሮ ላይ ኒው ዮርክ ውስጥ የተለያዩ ከዕጽ እና ከጦር መሳሪያ ጋር የተያያዙ ክሶች እንደተከፈተባቸው ገለጹ
    • አመሻሽ ላይም ትራምፕ በቬንዙዌላ ሽግግር እስኪካሄድ ድረስ አገሪቱን አሜሪካ እንደምትመራ እና የነዳጅ ሀብቷንም እንደምታስተዳድር በይፋ ተናገሩ
    • የቬንዙዌላ ምክትል ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮዴሪጌዝ የአገሪቱን ሥልጣን ተረክበው በአሜሪካ የተፈጸመውን “ወረራ” በማውገዝ መንግሥታቸው አገሪቱን “ለመከላከል ዝግጁ” መሆኑን አሳወቁ
    • ቅዳሜ ዕኩለ ሌሊት አካባቢ ማዱሮ እና ሚስታቸው በአውሮፕላን ወደ ኒው ዮርክ ተወስደው ብሩክሊን ሜትሮፖሊታን እስር ቤት ውስጥ እንዲያርፉ ተደረገ
    • የአሜሪካ እርምጃ ግን በዓለም ዙሪያ መነጋገሪያ ከመሆን አልፎ ጠንካራ ተቃውሞ እየገጠመው ነው
  4. አሜሪካ የቬንዙዌላውን ፕሬዝዳንት የያዘችበት ዘመቻ እንዴት ተከናወነ?

    ትራምፕ የቬንዙዌላውን ፕሬዝደንት ለመያዝ የተደረገውን ዘመቻ ሲከታተሉ

    የፎቶው ባለመብት, US Government

    የ63 አመቱ ፕሬዝዳንት የት እንደሚተኙ፣ ምን እንደሚመገቡ፣ ምን እንደሚለብሱ እና "የቤት እንስሳቶቻቸውንም" ጭምር ክትትል ሲደረግባቸው ነበር።

    በታህሳስ መጀመሪያ "ኦፕሬሽን አብስሉት ሪዞልቭ" (Operation Absolute Resolve) የሚል ስያሜ የተሰጠው ዘመቻ እቅዱ ተነድፎ ተጠናቀቀ። ወራትን የፈጀው እቅድ፤ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጎበት የተዘጋጀ ነው።

    በእቅድ ዝግጅቱ ውስጥ የተሳተፉ የአሜሪካ 'ኤሊት' ወታደሮች፤ በቬንዙዌላ ዋና ከተማ ካራካስ የሚገኘውን የፕሬዝዳንቱን ደህንነቱ የተጠበቀ ማቆያ ( safe house) አስመስለው በመገንባት ጭምር በምን አይነት መንገድ ማዱሮን እንደሚይዙ ተለማምደዋል።

  5. ቬንዙዌላዊያን ማዱሮ በቁጥጥር ሥር ስለመዋላቸው ምን አሉ?

    ቦጎታ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በቬንዙዌላ ዋና ከተማ ካራካስ ሁኔታዎች መረጋጋት ጀምረዋል። ፕሬዝደንት ማዱሮ በአሜሪካ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተከትሎ ተስፋ፣ ፍርሐት እና እርግጠኛ አለመሆን አየሩን የሞላው ይመስላል።

    የካራካስ ነዋሪዋ ዲና አሜሪካ “ማዱሮን ከዚህ ስለነቀለችልን” እናመሰግናለን ትላለች። አክላ አሁን ተስፋ እንደሰነቀች ትናገራለች።

    ነገር ግን የፖለቲካ ሁኔታው አሁን ውጥረት የተሞላበት ነው። ዲና ትክክለኛ ስሟን መናገር ያልፈለገችውም ለዚህ ነው።

    ሌላኛው የካራካስ ነዋሪ የሆነው ሆርጌ ለአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ “ምስጋና” አቅርቦ የሚመጡት ቀናት ግን ቀላል አይሆኑም ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።

    “ይህን ሰውየ ከወሰዱልን በኋላ ምንድነው የሚሆነው? ምንም ማረጋገጫ አልሰጡንም። በቀጣይ ቀናት ምን ሊሆን እንደሚችል አናውቅም” ይላል።

    የማዱሮ መንግሥት ደጋፊዎች በካራካስ ጎዳናዎች ወጥተው ድምፃቸውን አሰምተዋል። አሜሪካ መሪያቸውን እንድትለቅም ጠይቀዋል። የአሜሪካን ድርጊት “አፈና” ሲሉ የገለፁት የማዱሮ ደጋፊ የሆኑት የከተማዋ ከንቲባ ካርመን ሜሌንዴዝ ከሰልፈኞቹ መካከል ነበሩ።

    የአሜሪካ ኃይል በፕሬዝደንት ትራምፕ ትዕዛዝ መሠረት የቬንዙዌላውን መሪ በዋና ከተማዋ ካራካስ በቁጥጥር ሥር ያዋለው አርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ነው።

    በአውሮፓውያኑ 2024 የተደረገውን ምርጫ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ አሸንፈዋል ተብለው በተቃዋሚዎቻቸውና በምዕራባዊያን ሀገራት የሚወቀሱት ማዱሮ አደገኛ ዕፅ በማዘዋወርና የጦር መሣሪያ በመያዝ ክስ ቀርቦባቸዋል።

    የዩናይትድ ሶሻሊስት ፓርቲው መሪ ከአውሮፓውያኑ 2013 ጀምሮ የቬንዙዌላ ፕሬዝደንት ሆነው አገልግለዋል።

    ማዱሮ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ 8 ሚሊዮን ገደማ ቬንዙዌላዊያን ሀገራቸውን ጥለው እንደወጡ ይገመታል። በአሜሪካና በሌሎች ሀገራት የሚገኙ ቬንዙዌላዊያን የማዱሮን መታሰር ተከትሎ ደስታቸውን ሲገልፁ ታይተዋል።

  6. ኒኮላስ ማዱሮ በአሜሪካ ተይዘው እንዴት ከአገራቸው ተወሰዱ?

    ኒኮላስ ማዱሮ

    የፎቶው ባለመብት, Donald Trump

    የአሜሪካ ልዩ ኮማንዶዎች ወደ ቬንዙዌላ ዘልቀው በመግባት ጥቃት ፈጽመው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን በቁጥጥር ሥር በማዋል የወሰዱበትን ተልዕኮ በተመለከተ ጄነራል ዳን ኬይን ቅዳሜ ከሰዓት መግለጫ ሰጥተዋል።

    ከድንገተኛ ዘመቻ በፊት፣ በጥቃቱ ወቅት እና በኋላ የተከናወኑ እና የተከሰቱትን ጉዳዮች በተመለከተ ጄኔራሉ ከገለጹት መካከል ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው።

    • የአየር፣ የምድር፣ የህዋ፣ የባሕር እና የደኅንነት መረጃ ባለሙያዎች የተልዕኮውን ዕቅድ ሲያዘጋጁ እና ሲያቀናጁ ለወራት ቆይተዋል
    • አርብ ምሽት 4 ሰዓት ከ46 ደቂቃ ላይ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዘመቻው እንዲካሄድ ትዕዛዝ አስተላለፉ
    • ዘመቻ 'አብሶሉት ሪዞልቭ' የሚል ስያሜ የተሰጠው ተልዕኮ በምዕራቡ ንፍቀ ክበብ ከሚገኙ የተለያዩ 20 የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች 150 አውሮፕላኖችን ወደ ቬንዙዌላ በማንቀሳቀስ ተጀመረ
    • የምድር ኃይል እና ሄሊኮፕተሮችን ያካተተው ፕሬዝዳንቱን ነጥሎ የሚይዝ ኃይል ቅዳሜ ሌሊት ሰባት ሰዓት ላይ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ እና ሚስታቸው ወደሚኖሩበት ቅጥር ጊቢ አቀና
    • ይህ ኃይል በበርካታ ዘመና ተዋጊ የጦር ጄቶች፣ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች እና በድሮኖች ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገለት ነበር
    • ሄሊኮፕተሮች ላይ ተኩስ ተከፍቶባቸው አንደኛው ቢመታም በዘመቻው ወቅት ግዳጁን ለመፈጸም ከመብረር ያገደው አልነበረም
    • ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ እና ባለቤታቸው ከመኖሪያቸው ተይዘው በሄሊኮፕተር ከቬንዙዌላ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ ከሌሊቱ 9 ሰዓት ከ39 ደቂቃ በአሜሪካዋ የጦር መርከብ ዩኤስኤስ አይዋ ጂማ ላይ አረፉ
  7. የቬንዙዌላ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንቷን ጊዜያዊ መሪ አድርጎ ሾመ

    ዴልቺ ሮድሪጌዝ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ካራካስ የሚገኘው የቬንዙዌላ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ዴልሲ ሮድሪጌዝን የሀገሪቱ ጊዜያዊ መሪ ጊዜያዊ መሪ አድርጎ ሾሟል።

    ሮድሪጌዝ በአሜሪካ ተይዘው ወደ ኒው ዮርክ የተወሰዱት ኒኮላስ ማዱሮ ምክትል ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

    ፕሬዝደንት ትራምፕ በሰጡት መግለጫ ምክትል ፕሬዝደንቷ የሀገሪቱ መሪ ሆነው ቃለ መሐላ መፈፀማቸውንና "ቬንዙዌላን ድጋሚ ታላቅ ለማድረግ ለምናደርገው ነገር ለመተባበር ፈቃደኛ መሆናቸውን" ተናግረዋል።

    ማዱሮ ከዚህ ቀደም ሮድሪጌዘ ሶሻሊስት መንግሥታቸው ለመጠበቅ ላደረጉት ታጋድሎ "ነብር" ናቸው ሲሉ ገልፀዋቸዋል።

    የ56 ዓመቷ ሮድሪጌዝ ቅዳሜ የትራምፕ አስተዳደር ኒኮላስ ማዱሮን መያዙን ተከትሎ በሕይወት ስለመኖራቸው ማረጋገጫ እንፈልገኣለን ሲሉ ጠይቀው ነበር።

    በአውሮፓውያኑ 2018 ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው የተሾሙት ሮድሪጌዝ ከዚህ ሥልጣናቸው በተጨማሪ የሀገሪቱ የነዳጅ ሚኒስትር ሆነው ያገለግላሉ።

    ሮድሪጌዝ በአሜሪካ ቁጥጥር ስር የዋሉት ኒኮላስ ማዱሮ የቬንዙዌላ ብቸኛው ፕሬዝደንት ናቸው ሲሉ በሀገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው ንግግር አድርገዋል።

    “ቬንዙዌላ ውስጥ አንድ ፕሬዝደንት ብቻ ነው ያለው። ስሙም ኒኮላስ ማዱሮ ይባላል” ብለዋል።

    ምክትሏ አክለው መንግሥታቸው ቬንዙዌላን “ለመከላከል” ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል። ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ በኋላ ቬንዙዌላን “የምታስዳደረው” አሜሪካ መሆኗን ተናግረዋል።

    ሮድሪጌዝ በመላ ሀገሪቱ መረጋጋት እና አንድነት እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።

    በሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጊዜያዊ መሪ ሆነው የተሾሙት ሮድሪጌዝ “በሀገራችን ላይ የተቃጣ የትጥቅ ጥቃት” ሲሉ የአሜሪካን ድርጊት የኮነኑት ሲሆን የሀገራቸው መከላከለያ ምክር ቤት ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

    በሚቀጥሉ ቀናት መንግሥታቸው ለተፈጠረው ሁኔታ ምላሾች እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።

  8. ማዱሮ ብሩክሊን የሚገኝ እስር ቤት መግባታቸው ታወቀ

    ማዱሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሆነው

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ከሀገራቸው በአሜሪካ ተይዘው ወደ ኒው ዮርክ የመጡት የቬንዙዌላው ፕሬዝደንት ኒኮላስ ማዱሮ እና ሚስታቸው ብሩክሊን የሚገኝ እስር ቤት መድረሳቸው ታውቋል።

    እስር ቤቱ ትልቅ ስም ያላቸው ግሰለቦች የሚገቡበት ሲሆን ጂሌይን ማክስዌል እና ፒ ዲዲ ይጠቀሳሉ።

    የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ማዱሮ ቅዳሜ ከመጡ በኋላ ኒው ዮርክ በሚገኘው የአሜሪካ የዕፅ ቁጥጥር ቢሮ (ዲኢኤ) በዕፅ ዝውውር እና የጦር መሣሪያ በመያዝ ክስ ተመስሮባቸዋል።

    ማዱሮ ከዚህ ቀደም የዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን ኃላፊ ናቸው መባላቸውን ማስተባበላቸው ይታወሳል።

    ማዱሮ እና ሚስታቸው ኒው ዮርክ ፍርድ ቤት መቼ እንደሚቀርቡ አልታወቀም።

    ፕሬዝደንት ትራምፕ ቅዳሜ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "ደኅንነቱ የተጠበቀ ፍትሐዊ ሽግግር ማካሄድ እስክንችል ድረስ ቬንዙዌላን የምታስዳድረው አሜሪካ ናት" ብለዋል።

    ቬንዙዌላ "ከባድ የውጭ ወታደራዊ ወረራ" በሚል የትራምፕን ድርጊት ኮንና በመላው ሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለች።

  9. ቻይና፣ ሩሲያና ሌሎች የዓለማችን መሪዎች ማዱሮ ስለመያዛቸው ምን አሉ?

    የማዱሮ ፎቶ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የዓለም ሀገራት መሪዎች የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የቬንዙዌላውን መሪ ስለመያዛቸው የሰጡት ምላሽ የተደበላለቀ ነው።

    ትራምፕ መጠነ ሰፊ ባሉት ቅዳሜ በተደረገ ጥቃት ማዱሮ እና ሚስታቸው በአሜሪካ ኃይሎች ተይዘው ወደ አሜሪካ እንዲመጡ ተደርገዋል። ጥንዶቹ ኒው ዮርክ ውስጥ በዕፅ ዝውውር ወንጀል ተከሰዋል።

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር መንግሥታቸው ለማዱሮ አገዛዝ "እንባ እንደማያፈስ" ተናግረዋል። ስታርመር ጥቃቱን ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ ነው ወይ በሚል የቀረበላቸውን ጥያቄ ሳይመልሱ ቀርተዋል።

    የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን "የሽግግር ሒደቱ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሊሆን ይገባል" ሲሉ በኤክስ ገፃቸው ፅፈዋል።

    የቬንዙዌላ ጎረቤቶች ጥቃቱን ሲያወግዙት የማዱሮ የረዥም ጊዜ አጋር የሆኑት ቻይና እና ሩሲያም እርምጃውን ተቃውመዋል።

    ቻይና በአንድ ሉዓላዊት ሀገር እና ፕሬዝደንቷ ላይ ጥቃት መድረሱን በተለመከተ "በጣም ደንግጠናል በፅኑም እንቃወማለን" የሚል አስተያየት ሰጥታለች።

    ሩሲያ በበኩሏ አሜሪካ "የወረራ ድርጊት ፈፅማለች" ስትል ከሳለች። ከትራምፕ መንግሥት ጋር አለመግባባት ውስጥ የምትገኘው ኢራን ደግሞ ጥቃቱ "የሀገሪቱን ብሔራዊ ሉዓላዊነት የገፈፈ ነው" ብላለች።

    የብራዚሉ ፕሬዝደንት ሉላ ዳ ሲልቫ በኤክስ ገፃቸው የአሜሪካ ድርጊት "የማይታለፍ መስመር የጣሰ ነው" ብለው የትራምፕ አስተዳደር "ዓለም አቀፍ ሕግን በጣሰ ሁኔታ ሀገራትን ዓለማችንን ማጥቃት ግጭት፣ ብጥብጥ እና አለመረጋጋት ውስጥ ይከታታል" ብለዋል።

    የኮሎምቢያው ፕሬዝደንት ጉስታቮ ፔትሮ ድርጊቱ የላቲን አሜሪካ "ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው" ሲሉ የኩባው አቻቸው ሚገል ዲያዝ-ካኔ ደግሞ "የወንጀል ጥቃት" ሲሉ ከሰውታል። የቺሌው ፕሬዝደንትም "ስጋት" እንደገባቸው አሳስበው ጥቃቱን ኮንነዋል።

    የትራምፕ አስተዳደር ከዚህ ቀደም ኩባን "እየወደቀች ያለች ሀገር" ሲሉ መጥራታቸው ይታወሳል።

  10. ‘አስተማማኝ ሽግግር እስኪካሄድ ድረስ አሜሪካ ቬንዙዌላን ትመራለች’ ፕሬዝዳን ትራምፕ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ትራምፕ፣ ከውጭ ጉዳይ እና ከመከላከያ ሚኒስትሮቻቸው ጋር

    ቬንዙዌላ ውስጥ ጥቃት እንዲፈጸም አዝዘው ፕሬዝዳንቱን በቁጥጥር ሥር ያዋሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተማማኝ ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ አሜሪካ አገሪቱን እንደምትመራ ተናገሩ።

    ቬኒዙዌላ ላይ ድንገተኛ የኮማንዶ ጥቃት በመፈጸም አገሪቱ መሪ በአሜሪካ እጅ መግባታቸውን በተመለከተ ፕሬዝንት ትራምፕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “አስተማማኝ፣ ተገቢ እና ሕጋዊ ሽግግር እስኪካሄድ ድረስ ቬንዙዌላን አሜሪካ ታስተዳድራለች” ሲሉ በኩራት ተናግረዋል።

    በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ትራምፕ የአገሪቱን የነዳጅ ሀብት በተመለከተም ትላልቅ የአሜሪካ ኩባንያዎች ወደ ቬንዙዌላ በመግባት መሠረተ ልማቶቿን መልሶ በመጠገን “ለአገሪቱ ገቢ ማስገኘት ይጀምራሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

    ከፍተኛ የነዳጅ ዘይት ሀብት ያላት ቬንዙዌላ ባለፉት ሳምንታት ምርቷን ወደ ውጭ እንዳትልክ በአሜሪካ እንቅፋት ተፈጥሮባት ቆይቷል። ነዳጅ ጫኝ መርከቦችም ከነጭነታቸው በአሜሪካ ቁጥጥር ሥር ወድቀዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በወታደሮቻቸው ቁጥጥር ሥር የገቡትን የፕሬዝዳንት ማዱሮን ምሥል አጋርተዋል።

    ምንጮች በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ እንዳረጋገጡት ማዱሮን ያሳፈረው የአሜሪካ ጦር ሠራዊት አውሮፕላን በሰዓታት ውስጥ ኒው ዮርክ ያርፋል።

    በዕጽ እና በጦር መሳሪያ ወንጀሎች ክስ የተመሠረተባቸው ኒኮላስ ማዱሮ አሜሪካ እንደደረሱ ጦር ሠራዊቱ ለፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት አሳልፈው እንደሚሰጧቸው እና በሚቀጥለው ሳምንትም ኒው ዮርክ ውስጥ ከሚገኝ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    ፕሬዝዳንት ማዱሮ

    የፎቶው ባለመብት, Truth Social

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ማዱሮ በአሜሪካ ቁጥጥር ሥር ሆነው
  11. ዩኬ በቬንዙዌላ ላይ በተፈጸመው ጥቃት አለመሳተፏን ጠቅላይ ሚኒስትሯ ተናገሩ

    ኪር ስታርመር

    ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) በቬንዙዌላ በተፈጸመው የአሜሪካ ዘመቻ ላይ "በምንም መልኩ አልተሳተፈችም" አሉ።

    ነገር ግን አስተያየት ከመስጠታቸው በፊት ተጨማሪ መረጃ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

    ስታርመር ኒኮላስ ማዱሮ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በተመለከተ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር እንዳልተነጋገሩም አስረድተዋል።

    “ጉዳዩ በፍጥነት የሚለዋወጥ ነው፤ ​​እናም ሁሉንም መረጃዎች ማረጋገጥ አለብን” ሲሉ ለዩኬ መገናኛ ብዙኃን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም "እኔ የምለው ዩኬ በዚህ ዘመቻ ውስጥ በምንም መልኩ አልተሳተፈችም ነው።"

    ስታርመር በርካታ የዩኬ የፓርላማ አባላት እንዳደረጉት ድርጊቱን ያወግዙ እንደሆን ተጠይቀው “እውነታዎቹን መጀመሪያ ማረጋገጥ እፈልጋለሁ። ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር መነጋገር እፈልጋለሁ። ከአጋሮቻችን ጋር መነጋገር እፈልጋለሁ። እኔ የማረጋግጥላችሁ በዚህ ውስጥ እንዳልተሳተፍን ብቻ ነው” ብለዋል።

    "እንደምታውቁት ሁልጊዜም ዓለም አቀፍ ሕግን ማክበር እንዳለብን እናገራለሁ እናም አምናለሁ" ሲሉ አክለዋል።

    "ግን በዚህ ደረጃ፣ በፍጥነት የሚለዋወጥ ሁኔታ ስለሆነ፣ እውነታውን እናረጋግጥ እና ከዚያ በኋላ እንነጋገራለን።"

    ስታርመር በደቡብ አሜሪካ አገር ውስጥ የሚገኙ የዩኬ ዜጎችን በሚመለከት "በቬንዙዌላ ውስጥ ወደ አምስት መቶ የሚጠጉ ዜጎች አሉ፤ እና ከኤምባሲው ጋር ስለደኅንነታቸው እየተነጋገርን ነው፤ ጥበቃ እየተደረገላቸው እና ተገቢውን ምክር እንዲያገኙ እየሠራን ነው። አነስተኛ ቁጥር ነው፣ ግን አስፈላጊ ቁጥር ነው፣ ስለዚህ እዚያ እያደረግነው ያለነው ይህንኑ ነው" ብለዋል።

  12. ፕሬዝዳንት ማዱሮ እና ባለቤታቸው አሜሪካ ውስጥ በዕጽ እና በጦር መሳሪያ ዝውውር ተከሰሱ

    ማዱሮ እና ሚስታቸው

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ ቅዳሜ ማለዳ በደቡብ አሜሪካዊቷ አገር ቬንዙዌላ ላይ ጥቃት ፈጽማ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን በቁጥጥር ሥር ማዋሏን ካሳወቀች በኋላ ክስ እንደመሠረተችባቸው ገለጸች።

    የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፓም ቦንዲ፣ ኒኮላስ ማዱሮ እና ባለቤታቸው በኒው ዮርክ ከተማ ክስ ተመሥርቶባቸዋል።

    ዐቃቤ ሕጓ ጨምረውም በማዱሮ ላይ "ከዕጽ ምርት እና ዝውውር ጋር የተያያዘ ሴራ፣ ኮኬይን ወደ አሜሪካ በማስገባት ሴራ፣ መትረየሶች እና አውዳሚ መሳሪያዎችን በአሜሪካ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ለመያዝ በማሴር” የሚሉ ክሶች ቀርበውባቸዋል።

    ፕሬዝዳንቱ እና ባለቤታቸው በአሜሪካ ውስጥ "በአሜሪካ ምድር፣ በአሜሪካ ፍርድ ቤት የአሜሪካንን የፍትሕ አቅም ሙሉ ለሙሉ በቅርቡ ይጋፈጡታል” ሲሉም አክለዋል።

    ነገር ግን ፓም ቦንዲ የፕሬዝዳንት ማዱሮ ሚስት ከባለቤታቸው ጋር እንደሚከሰሱ ቢናገሩም ስለቀረበባቸው ክስ ዝርዝር አልተናገሩም።

    "እነዚህን ሁለት ዓለም አቀፍ የዕጽ አዘዋዋሪ ናቸው የሚባሉትን ጥንዶች ለመያዝ አስደናቂ እና እጅግ ስኬታማ ተልዕኮን የፈጸሙትን ጀግኖች ወታደሮቻችንን አመሰግናለሁ” ብለዋል ዐቃቤ ሕጓ።

  13. በአሜሪካ ጥርስ ውስጥ ስለገባችው ቬንዙዌላ አንዳንድ እውነታዎች

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ በቬንዙዌላ ላይ ከፍተኛ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ የአገሪቱን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን በቁጥጥር ሥር አውላለች ብለዋል።

    በአውሮፓውኑ 1989 የፓናማ ወታደራዊ መሪ የነበሩትን ማኑኤል ኑሬጋን ከሥልጣን ካባረረችበት ወረራ ወዲህ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነትን ላቲን አሜሪካ ውስጥ ፈጽማ አታውቅም ነበር።

    ትራምፕ እንዳሉት ፕሬዝዳንት ማዱሮን ከሥልጣን ካስወገዱ በአስተደዳራቸው ውስጥ በቬንዙዌላ የመንግሥት ለውጥ እንዲደረግ ሲወተውቱ ለነበሩ ነውጠኛ ባለሥልጣናት አስደሳች ድል ነው።

    አሜሪካ ኒኮላስ ማዱሮ ወንጀለኛ የእጽ አዘዋዋሪ ድርጅትን ይመራሉ ስትል በተደጋጋሚ ብትከስም እሳቸው ግን ሲያስተባብሉ ነበር። በተጨማሪም ከፍተኛ መጭበርበር ተፈጽሞበታል በተባለው የ2024 ምርጫ ማሸነፋቸውን አሜሪካ አትቀበልም።

    በቬንዙዌላ ባለሥልጣናት በኩልም አሜሪካ እንዲህ በጠላትነት ጠምዳ የያዘቻቸው በዓለም የተረጋገጠ ትልቁን የነዳጅ ክምችቷን ለመቆጣጠር በመፈለግ ነው በማለት ይከስሳሉ።

    ካርታ
    ካርታ
    ካርታ
    ካርታ
    ካርታ
    ማዱሮ
  14. ኮሎምቢያ ከቬንዚዌላ ጋር በምትዋሰንበት አካባቢ ጦሯን አሰማራች

    የኮሎምቢያ ፕሬዚዳንት ጉስታቮ ፔትሮ

    የፎቶው ባለመብት, CARLOS ORTEGA/EPA/Shutterstock

    የኮሎምቢያ ፕሬዚዳንት ጉስታቮ ፔትሮ ከብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤታቸው ጋር ከተሰበሰቡ በኋላ በቬንዚዌላ ድንበር የጦር ኃይላቸው መሰማራቱን ተናገሩ።

    አሜሪካ ካራካስን እና ሌሎች አካባቢዎች ላይ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ከቬንዚዌላ ከፍተኛ የሆነ የተፈናቃዮች ፍልሰት ይኖራል በሚል ቦጎታ እየተዘጋጀች መሆኑ ተሰምቷል።

    የቬንዚዌላ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ እና ባለቤታቸው ሲሊያ ፍሎረስ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይፋ ካደረጉ በኋላ ጠናው በከፍተኛ ስጋት ውስጥ በተጠንቀቅ ይገኛል።

    ፔትሮ በካራካስ ላይ የመጀመርያው ጥቃት ከተፈጸመበት ጊዜ አንስቶ በተደጋጋሚ ሰላም እንዲሰፍን እና ውይይት እንዲደረግ ሲጠይቁ ነበር።

    ኮሎምቢያ እና ቬንዚዌላ ከ2000 ኪሎ ሜትር በላይ ድንበር ይጋራሉ።

    ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱ አገራት በታሪክ፣ በምጣኔ ኃላብት እና የፀጥታ እና ደህንነት ጉዳዮች የተሳሰሩ ናቸው።

  15. የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በቬንዙዌላ ላይ ተጨማሪ ጥቃት አይጠብቁም- የአሜሪካ ሴናተር

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ፕሬዝዳንት የኒኮላስ ማዱሮን መያዝ ተከትሎ ተጨማሪ ጥቃት ቬንዙዌላ ላይ እንደማይጠብቁ የሪፐብሊካን ሴናተር ተናገሩ።

    ሴናተር ማይክ ሊ ከማርኮ ሩቢዮ ጋር በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ የማዱሮን በቁጥጥር ስር መዋል አረጋግጠዋል።

    “[ሩቢዮ] ማዱሮ በአሜሪካ ቁጥጥር ስር በመዋሉ አሁን ተጨማሪ ጥቃት ቬንዙዌላ ላይ አይጠብቁም” ብለዋል።

    የአሜሪካ ጥቃት “የእስር ማዘዣውን ለማስፈፀም” እንደሆነም አክለው ተናግረዋል።

    ቀደምሲል ሊ በኤክስ ገጻቸው በለጠፉት ጽሑፍ “ጦርነት ማወጅን ወይም ወታደራዊ ኃይል ለመጠቀም ፈቃድ የማይጠይቅ ሕገመንግሥት ካለ ለመማር ዝግጁ ነኝ” ብለው ነበር።

  16. የቬንዚዌላ መከላከያ ሚኒስትር በመላ አገሪቱ ጦሩ እንደሚሰማራ ተናገሩ

    በስተግራ ማዱሮ በስተቀኝ የመከላከያ ሚኒስትሩ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የቬንዚዌላ መከላከያ ሚኒስቴር በመላ አገሪቱ የጦር ኃይሉ እንደሚሰማራ አስታወቁ።

    ቭላድሚር ፓድሪኖ ሎፔዝ በቪዲዮ ባስተላላፉት መልዕክት ቬንዚዌላ አይታ የማታውቀው “አስከፊ ጥቃት” ገጥሟታል፤ በ“ማዱሮ ትዕዛዝ” የጦር ኃይሉ በመላ አገሪቱ ይሰማራል ብለዋል።

    “አጥቅተውናል ነገር ግን እንድንበረከክ ግን አያደርጉንም” ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሩ ጨምረው ተናግረዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በቬንዚዌላ ወታደራዊ የጦር ካምፖች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን እና የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ከእነባለቤታቸው በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ተናግረዋል።

    ፕሬዚዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ማዱሮ እና ባለቤታቸው በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ከአገር አንዲወጡ ተደርገዋል ብለዋል።

  17. ትራምፕ አሜሪካ የቬንዙዌላውን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን በቁጥጥር ስር ማዋሏን አስታወቁ

    ወታደራዊ ጥቃቱን የሚያሳይ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋሽንግተን “ቬንዙዌላ ላይ ሰፊ ጥቃት” መፈፀሟን እና መሪውን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን እና ባለቤታቸውን መያዟን አስታወቁ።

    ትራምፕ በትሩዝ ማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው “ዩናይትድ ስቴትስ ውጤታማ የሆነ ሰፊ ጥቃት በቬንዙዌላ እና በመሪዋ ላይ ፈፅማለች። ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ከባለቤታቸው ጋር ተይዘው ከአገሪ ውጭ እንዲወጡ ተደርጓል” ብለዋል።

    ትራምፕ ፕሬዝዳንቱ እንዴት እንደተያዙ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

    “ተልዕኮው በአሜሪካ የህግ ማስከበር መሰረት ተካሂዷል። ዝርዝሮች መውጣታቸውን ይቀጥላሉ. . . በማለት በመኖሪያ ቤታቸው መግለጫ እንደሚሰጡ ጠቅመዋል።

    የቬንዙዌላ መንግሥት እስካሁን የፕሬዝዳንቱን መያዝ በሚመለከት ማረጋገጫ አልሰጠም።

    ቅዳሜ ጠዋት ከቬንዙዌላ ዋና ከተማ ጭስ ሲወጣ ከታየ በኋላ የአሜሪካ ባለሥልጣናት በከተማዋ በሚገኙ ወታደራዊ ሠፈሮች ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር ትዕዛዝ እንደተሰጠ አረጋግጠዋል።

    የቬንዙዌላ መንግሥት ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።

    አሜሪካ ኒኮላስ ማዱሮ ዓለም አቀፍ አደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪ ድርጅትን ይመራሉ የሚል ክስ ለረጅም ጊዜ ስታቀርብ ቆይታለች።

    ዋሽንግተን ፕሬዝዳንቱን በቁጥጥር ስር ማዋል የሚያስችል መረጃ ለሚሰጡ ሰዎች የ50 ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ አውጥታ ነበር።

  18. አሜሪካ በቬንዙዌላ ዋና ከተማ ላይ ጥቃት ሰነዘረች

    የአሜሪካን ጥቃት የሚያሳይ ምስል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካን ጥቃት የሚያሳይ ምስል

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት በቬንዙዌላ በሚገኙ ወታደራዊ ሠፈሮች ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር ትዕዛዝ መስጠታቸውን የቢቢሲ የአሜሪካ የዜና አጋር ሲቢኤስ ዘገበ።

    በርካታ ፍንዳታዎች ዋና ከተማዋን ካራካስን ካናወጡ በኋላ ዶናልድ ትራምፕ በቬንዙዌላ በሚገኙ ወታደራዊ ሠፈሮች ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

    ቅዳሜ ጠዋት ከቬንዙዌላ ዋና ከተማ ጭስ ሲወጣ ታይቷል።

    የአገሪቱ መንግሥት ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።

    የቬንዙዌላ መንግሥት ባወጣው መግለጫ የአሜሪካን ወታደራዊ ጥቃት ውድቅ አድርጎ አውግዟል።

    ዋይት ሐውስ እና ፔንታጎን እስካሁን በይፋ አስተያየት አልሰጡም። በካሪቢያን የባህር ኃይል ያሰማሩት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቬንዙዌላ የጥቃት እንደሚፈጸም በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል።

    በአሜሪካ ጥቃት የተፈጸመባቸው ቦታዎች መካከል በዋና ከተማዋ ካራካስ የሚገኝ ወታደራዊ አየር ማረፊያ እና የፉዌርቴ ቲውና ዋና ወታደራዊ ጦር ሠፈር ይገኙበታል።

    በአካባቢውየሚኖሩ በርካታማኅበረሰቦችየኃይል እጥረት አጋጥሟቸዋል።

    በካራካስ ሄሊኮፕተሮች ሲበሩ የሚያሳዩ እና ፍንዳታዎችን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችበማኅበራዊሚዲያ ላይ የተሰራጩ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም።።

    የቬንዙዌላመንግሥትየሚራንዳ፣ የአራጓ እና የላ ጓይራ ግዛቶችም ጥቃት እንደደረሰባቸው እና ጥቃቶቹ የቬንዙዌላ ነዳጅ እና ማዕድናትን ለመያዝ ያለሙ መሆናቸውን አስታውቆ ጥቃቱን አውግዟል።

    ኩባእና ኮሎምቢያም አሜሪካን ጥቃቶች አውግዘዋል።

    አሜሪካ በካሪቢያን አደንዛዥ ዕጽ ያመላልሳሉ ያለቻቸው መርከቦች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት ስትፈጽም ነበር።

  19. የኢራን ፖሊስ ተቃዋሚ ሠልፈኞችን አስጠነቀቀ

    የኢራን ፖሊስ ቃል አቀባይ የሕግ ጥሰት እና አለመረጋጋት መፍጠር አይፈቀድም ሲል ተቃዋሚ ሠልፈኞችን አስጠነቀቀ።

    የኢራን ባለሥልጣናት ዶናልድ ትራምፕ ተቃዋሚ ሠልፈኞችን ለመታደግ ጣልቃ እንደሚገቡ ማስጠንቀቂያ ቢሰጡም የጨጥታ አካላት ግን "የሚወስዱትን እርምጃ " እንደሚቀጥሉ ተናገሩ።

    የኢራን ብሔራዊ ደህንነት እዝ ቃል አቀባይ ሰኢድ ሞንታዘራል ማህዲ እንዳሉት የፖሊስ መኮንኖች ጠላቶች የሚሏቸው ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን ወደ ሰላም መደፍረስ እና ትርምስ እንዲቀይሩት አይፈቅዱም ብለዋል።

    ሐሙስ ዕለት ከባድ ግጭቶችን ያስተናገደው የሎሬስታን ክልል አቃቤ ሕግ ሕገወጥ ስብሰባዎች በሙሉ ቁርጠኝነት እንደሚታገሉ ተናግረዋል።

    በኢራን ባለው የኑሮ ውድነት እና የገንዘብ የመግዛት አቅም መውደቅ ጋር ተያይዞ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ተስፋፍቶ ለአንድ ሳምንት ቀትሏል።

    ለፕሬዚዳንት ትራምፕ ዛቻ ምላሽ የሰጡት የኢራን ባለሥልጣናት የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ቀጠናዊ ትርምስን ያስፋፋል ብለዋል።

    በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የተጋሩ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት አርብ ምሽት ተቃዋሚ ሠልፈኞች በበርካታ የቴህራን ወደ ጎዳና ወጥተው ፀረመንግሥት መፈክሮችን ሲያሰሙ ነበር።

    በኢራን የተለያዩ ከተሞች በምሽት የሚደረጉ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ቀጥለዋል።

    በቦራዝጃን፣ኢስፋሃን፣ማሽሃድ እና ሖራማባድ፣ ተቃዋሚዎች ጎዳና ላይ ያደሩባቸው አካባቢዎች ናቸው።

  20. በአሜሪካ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ሊፈጸም የነበረ የሽብር ጥቃት መክሸፉ ተነገረ

    የኤፍቢአይ አባላት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአዲስ ዓመት ዋዜማ በኖርዝ ካሮላይና ግዛት ውስጥ በአንድ የአይኤስ ደጋፊ ሊፈጸም የነበረ የሽብር ጥቃት መክሸፉን የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት አስታወቀ።

    ክሪስቲያን ስቱርዲቫንት የተባለው የ18 ዓመት ተጠርጣሪ በኤፍቢአይ መኮንኖች የተያዘው ረቡዕ በተከበረው የአዲስ ዋዜማ ላይ በአይኤስ አነሳሽነት ቢላ እና መዶሻን በመጠቀም በርካታ ሰዎችን ለመጉዳት ዕቅድ ነበረው በሚል ነው።

    የግዛቲቱ ዐቃቤ ሕግ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ወጣቱ ለአይኤስ ታማኝነቱን መግለጹን እና ጥቃቱን በሚኖርበት ከተማ ውስጥ በሚገኝ መደብር እና ምግብ ቤት ላይ ለመፈጸም አቅዶ ነበር።

    የኤፍቢአይ አባላት የወጣቱን ቤት በፈተሹበት ጊዜም “የ2026 አዲስ ዓመት ጥቃት” የሚል እና በዕቅዱ ውስጥ አስከ 20 የሚደርሱ ሰዎችን በስለት ለመውጋት እና ለመያዝ የሚመጡትን የፖሊስ መኮንኖችንም ለማጠቃት ተዘጋጅቶ እንደነበር የሚገልጽ ሰነድ እንዲሁም በመኝታ ክፍሉ ውስጥ ቢላዎች እና መዶሻዎችን አግኝተዋል።

    ጥቃቱን ለመፈጸም ለአንድ ዓመት ያህል ሲዘጋጅ እንደነበረ እና በታኅሣሥ ወር የመጀመሪያ ሳምንት የአይኤስ አባላት ናቸው ብሎ ካሰባቸው የኤፍቢአይ ስውር ተከታታዮች ጋር በኢንተርኔት አማካይነት ተገናኝቶ ስለዕቅዱ እና ስለሚጠቀምበት መሳሪያ ነግሯቸው ነበር።

    ከሦስት ዓመት ጀምሮ በኤፍቢአይ ክተትል ስር የነበረ ወጣቱ ከአሜሪካ ውጪ ከሚገኙ ማንነታቸው ካልተገለጸ የአይኤስ አባላት ጋር ግንኙነት እንደነበረውም ተገልጿል።

    አርብ ዕለት ፍርድ ቤት የቀረበው ወጣቱ ለውጭ የሽብር ድርጅት ድጋፍ በመስጠት ክስ ቀርቦበታል።