ትራምፕ በቬንዜዌላ ጥቃት ከተፈፀመ በኋላ ፕሬዚዳንቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናገሩ

የቬንዚዌላ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ (በስተግራ) እና መከላከያ ሚኒስትር ቭላድሚር ፓድሪኖ ሎፔዝ (በስተቀኝ)

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የቬንዚዌላ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ (በስተግራ) እና መከላከያ ሚኒስትር ቭላድሚር ፓድሪኖ ሎፔዝ (በስተቀኝ)

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋሽንግተን "ቬንዙዌላ ላይ ሰፊ ጥቃት" መፈፀሟን እና መሪውን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን እና ባለቤታቸውን መያዟን አስታወቁ።

ትራምፕ በትሩዝ ማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው "ዩናይትድ ስቴትስ ውጤታማ የሆነ ሰፊ ጥቃት በቬንዙዌላ እና በመሪዋ ላይ ፈፅማለች። ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ከባለቤታቸው ጋር ተይዘው ከአገሪ ውጭ እንዲወጡ ተደርጓል" ብለዋል።

በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ የአሜሪካ ፀረ ሽብር ጦር ፕሬዚዳንቱን እና ባለቤታቸወን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ዘግቧል።

ትራምፕ በማኅበራዊ ድረገጻቸው ላይ "ተልዕኮው በአሜሪካ የህግ ማስከበር መሰረት ተካሂዷል። ዝርዝሮች መውጣታቸውን ይቀጥላሉ. . . በማለት በመኖሪያ ቤታቸው መግለጫ እንደሚሰጡ ጠቅመዋል።

የቬንዙዌላ መንግሥት እስካሁን የፕሬዝዳንቱን መያዝ በሚመለከት ማረጋገጫ አልሰጠም።

አሜሪካ ቬንዚዌላ ላይ ጥቃት የፈጸመችው ለሊቱን ሲሆን አገሪቱን ለረዥም ጊዜ ያስተዳደሩትን ኒኮላስ ማዱሮን በቁጥጥር ሥር ማዋሏን ተናግራለች።

አሜሪካ ላለፉት ጥቂት ወራት የቬንዚዌላው ፕሬዚዳንቱ በአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር እና ሕገወጥ በሆነ መልኩ ሥልጣንን በመያዝ ስትከስ ነበር።

ዋሺንግተን በላቲን አሜሪካ እአአ በ1989 ወታደራዊውን ፕሬዚዳንት ማኑኤል ኖሪዬጋን ከሥልጣን ለማውረድ በፓናማ ወረራ ከፈጸመች ወዲህ በቀጥታ ጦሯን አሳትፋ አታውቅም።

ቅዳሜ ጠዋት ከቬንዙዌላ ዋና ከተማ ጭስ ሲወጣ ከታየ በኋላ የአሜሪካ ባለሥልጣናት በከተማዋ በሚገኙ ወታደራዊ ሠፈሮች ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር ትዕዛዝ እንደተሰጠ አረጋግጠዋል።

የቬንዙዌላ መንግሥት ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።

አሜሪካ ኒኮላስ ማዱሮ ዓለም አቀፍ አደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪ ድርጅትን ይመራሉ የሚል ክስ ለረጅም ጊዜ ስታቀርብ ቆይታለች።

ዋሽንግተን ፕሬዝዳንቱን በቁጥጥር ስር ማዋል የሚያስችል መረጃ ለሚሰጡ ሰዎች የ50 ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ አውጥታ ነበር።

ትራምፕ በቬንዚዌላ የተካሄደውን ዘመቻ "ከአሜሪካ የሕግ አስከባሪዎች ጋር በጥምረት" ማካሄዳቸውን ገልጸዋል።

ማዱሮ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በልዩ የፀረ ሽብር ጦር መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።

የቬንዙዌላ መከላከያ ሚኒስቴር ቭላድሚር ፓድሪኖ "ነጻ፣ ገልልተኛ እና ሉዓላዊ የሆነችው ቬንዙዌላ የውጭ ጦር መገኘትን ትቃወማለች። ይህም በወራሪው ኃይል ላይ ሞት ፣ ሕመም እና ውድመት ብቻ የሚያመጣ ነው" ብለዋል።

"ዛሬ ክንዳችንን እናፈርጥም። አንድ እንሁን፤ በሕዝባችን አንድነት ውስጥ ለመታገል እና ለማሸነፍ ጥንካሬ እናገኛለን" ብለዋል።

የአሜሪካ ጦር በቬንዚዌላ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቬንዙዌላ መከላከያ ሚኒስቴር በመላ አገሪቱ የጦር ኃይሉ እንደሚሰማራ አስታውቀዋል።

ቭላድሚር ፓድሪኖ ሎፔዝ በቪዲዮ ባስተላላፉት መልዕክት ቬንዙዌላ አይታ የማታውቀው "አስከፊ ጥቃት" ተከትሎ "በማዱሮ ትዕዛዝ" የጦር ኃይሉ በመላ አገሪቱ ይሰማራል ብለዋል።

"አጥቅተውናል ነገር ግን እንድንበረከክ ግን አያደርጉንም" ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሩ ጨምረው ተናግረዋል።

የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሪስቶፈር ላንዳው ትራምፕ የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት በቁጥጥር ስር ውለዋል ካሉ በኋላ ማዱሮ "በመጨረሻም ለፈጸሙት ወንጀሎች ፍትህ ይጠብቃቸዋል" ብለዋል።

ትራምፕ ማዱሮ እና ባለቤታቸው "በቁጥጥር ስር ውለው ከአገር እንደወጡ" ቀደም ብለው አስታውቀዋል።

ይህ የፕሬዝዳንቱ ንግግር በብሔራዊ ሉዓላዊነት እና በዓለም አቀፍ ሕጎች ላይ ጥያቄዎችን አስነስቷል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ዓመት ምርጫ በማጭበርበር ወደ ሥልጣን ተመለሱ የሚል ክስ የቀረበባቸው የማዱሮ የረጅም ጊዜ ተቺ ናቸው።

የምርጫው ውጤት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሰፊው ተቀባይነት አላገኘም።

የአሜሪካ ጠቅላይ ዓቃቢ ሕግ ፓም ቦንዲ ዋሽንግተን ከዚህ ቀደም ያወጣችውን የ25 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት በእጥፍ ማሳደጓን በማሳወቅ፤ ማዱሮ በዕፅ ማዘዋወር ተልዕኮዎች ቀጥታ ተሳትፎ አላቸው ብለዋል።

የቬንዙዌላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይቫን ጊል አዲሱን ሽልማት "አሳዛኝ" ያሉ ሲሆን እርምጃውን "የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ" ሲሉም ስም ሰጥተውታል።

የተባበሩት ሶሻሊስት ፓርቲ መሪ የሆኑት ማዱሮ የሥልጣን መንበሩን እ.አ.አ በ2013 ከሒጎ ቻቬዝ የተረከቡ ሲሆን፤ ተቃዋሚ ቡድኖችን በማፈን፣ በማሳደድ እና ሁከት በመፍጠር በተደጋጋሚ ክስ ይቀርብባቸዋል።